Workneh Gebeyehu -
Workneh Gebeyehu –

ዋዜማ ራዲዮ- ኢትዮጵያ ሁለት አስርተ አመታት ለሚጠጋ ጊዜ ስትመራበት የነበረውን የውጪ ጉዳይና ደህንነት ፖሊሲ ለመቀየር እየተዘጋጀች መሆኑን የዋዜማ ምንጮች ገልፀዋል።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ፖሊሲውን ለመከለስ የሚረዱ ሀሳቦችን በማሰባሰብ ላይ ያተኮረ ስራ ሲሰራ የቆየ ሲሆን፣ ረቂቅ ፖሊሲው በቅርቡ ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ፖሊሲው በተለይ በአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ የተከሰቱ ለውጦችን ታሳቢ አድርጎ እየተዘጋጀ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ያስረዳሉ።
ከአስራ ስባት አመታት በፊት የተዘጋጀውና በቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር እንደተፃፈ በሚነገርለት የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ የሀገሪቱ ዋነኛ የህልውና አደጋ ድህነት መሆኑን በማተት ድህነት ከተቀረፈ ሀገሪቱ ከዉጪ ሀይሎች የሚገጥማትን ፈተና በድል አድራጊነት መወጣት እንደምትችል ያትታል።
ፖሊሲው ከኤርትራ ወረራ ማግስት የተፃፈ ቢሆንም ብዙዎቹን ክፍለ አህጉራዊ ችግሮችን “በልማታዊ መነፅር” የሚመለከትና የሀገሪቱን የአደጋ ተጋላጭነት አቃሎ የሚመለከት በመሆኑ ሲተች ቆይቷል።
ሀገሪቱ ወደብ አልባ በመሆኗ የገጠማትን ቀላል የማይባል ፈተና በእጅጉ የሚያቃልለው ይህ ፖሊሲ በራሱ በገዥው ፓርቲ አንዳንድ አባላት ሳይቀር ትችት ይቀርብበት ነበር።
ከፖሊሲው መውጣት በኋላ ሀገሪቱ ከፖሊሲው ትርክት በተፃራሪ ወደ ሶማሊያ ጦሯን አዝምታለች።
በአሁኑ ወቅትም ቢያንስ አስራ ሁለት የታጠቁ ሀይሎች በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ለመጣል በጎረቤት ሀገራት ተጠልለው ይገኛሉ።
ምስራቅ አፍሪቃ በርካታ የአረብ ሀገራትንና የሀያሉን ሀገራት የጦር ሰፈር ማስተናገድ መጀመሩ፣ የደቡብ ሱዳን ነፃ ሀገር መሆንና ሌሎች አለማቀፍ ሁኔታዎችም ባለፉት አመታት የተከሰቱ ለውጦች ናቸው።
አዲሱ ፖሊሲ የአየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ የተለያዩ ለውጦችን ታሳቢ አድርጎ እንደሚዘጋጅ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

https://youtu.be/2DaamPaA2BM