Flood rescue(ዋዜማ ራዲዮ)- መንግስታት ከሚወድቅባቸው ሀላፊነት አንዱ በተፈጥሮም ይሁን ሰው ሰራሽ አደጋዎች ወቅት የህዝባቸውን ደህንነት ማስጠበቅ ይገኝበታል። በተደጋጋሚ የድርቅና ረሀብ አደጋ የሚፈታተናት ኢትዮጵያ፣ አደጋ የመቋቋምና ቀድሞ የመከላከል አቅሟ ብዙ ጥያቄዎች ይነሱበታል።

ቻላቸው ታደሰ የሀገሪቱን አደጋ የመቋቋም አቅምና መዋቅራዊ ዝግጅት የተመለከተ ዘገባ አለው።

 

በማንኛዉም ሀገር አደጋዎች በማህበራዊና፣ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሃብት እድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድሩ ይታወቃል፡፡ በኢትዮጵያ በተደጋጋሚነቱ፣ በስፋቱ እና በሚያሳድረው ከባድ ጉዳት የሚጣወቀው ተፈጥሮ አደጋ ቀዳሚው ድርቅና ድርቅን ተከትሎ የሚመጣው ረሃብ ነው፡፡ ከድርቅ ባሻገርም ጎርፍ እና እሳት አደጋ በተደጋጋሚ ይከሰታሉ፡፡ ተፍጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የሚስከትሉት ማህበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ፖለቲካዊ እና ስነ ምህዳራዊ ተፅዕኖም ሰፊ ነው፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት አዲስ የአደጋ ክስተት ፖሊሲና ስትራቴጂ ስራ ላይ ካዋለ ሶስት ዓመታት አልፎታል፡፡ ፖሊሲው ስራ ላይ በዋለ በሶስት ዓመቱ በያዝነው ኣመት ከባድ ድርቅና ርሃብ ተክስቷል፡፡

በሀገራችን መንግስት ለአደጋዎች ተቋማዊ ምላሽ መስጠት ከጀመረ በርካታ አስርት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በሀገሪቱ ታሪክ መጀመሪያው ዕርዳታ እና መልሶ መቋቋሚያ ኮሚሽን የተቋቋመው በ1966ቱ ድርቅና ርሃብ በተከሰተ ጊዜ ነበር፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም የመንግስታቱ የአደጋ ክስተት ፖሊሲ፣ ተቋማዊ አደረጃጀትና ፍልስፍና በተወሰኑ ታሪካዊ ሂደቶችና ለውጦች ውስጥ አልፏል፡፡ ምንም እንኳ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ተፈጥሯዊ አደጋዎች ከፍተኛ ጉዳት ቢያስከትሉም እስካሁን ድረስ የአደጋ ክስተትን በመከላከል፣ ሀገሪቱ ለጉዳት ያላትን ተጋላጭነትና በመቀነስ ወይም ጉዳትን በመቋቋም ረገድ አበረታች ውጤት ሊመዘገብ እንዳልቻለ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ የአደጋዎቹ ተደጋጋሚነትም ሆነ የሚያስከትሉት መጠነ-ሰፊ ጉዳትም ከጊዜ ወደጊዜ ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አይታይም፡፡

ሀገሪቱ አደጋን እንዳትቋቋም ካደረጓት ዋና ዋነ ምክንቶች የመረጃ እጥረት፣ የማስተባበር ውስንነት፣ ባጀት፣ በእቅድ አለመመራት፣ በግብርና ላይ ጥገኛ መሆኗ፣ የስነ-ምህዳር መራቆት፣ ድህነት፣ የመሰረተ ልማት እጥረት፣ የተበታተነ የህዝብ አሰፋፈር፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የህዝብ ቁጥር መጨመር ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ለመጀመሪያ ጊዜ ብሄራዊ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት አመራር ፖሊሲ ያወጣው በ1986 ዓ.ም ነበር፡፡ ፖሊሲው በፍልስፍናው ከቀድሞው የሚለየው ቅድመ-ማስጠንቀቂያን፣ መከላከልንና አደጋ መቀነስን ማካተቱ ነው፡፡ በተቋም ረገድም በቀድሞው ዕርዳታ ማስተባበሪያና መቋቋሚያ ኮሚሽን ምትክ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን በአዋጅ መቋቋሙ ይታወሳል፡፡ መንግስት ይህንን ፖሊሲውን ለማሻሻል ሃያ ዓመታት ፈጅቶበታል፤ አሁን በስራ ላይ ያለውን አዲሱን የብሄራዊ አደጋ ክስተት ስጋት አመራር ፖሊሲና ስትራቴጂ ነድፎ ስራ ላይ ያዋለው ከሦስት ዓመታት በፊት በ2005 ዓ.ም ነው፡፡

መንግስት ፖሊሲውን የነደፈው እኤአ ከ2005 እስከ 2015 ድረስ በዓለም ላይ የአደጋ ክስተት ጉዳትን በከፍተኛ መጠነ ለመቀነስ ስምምነት የተደረሰበትን ዓለም ዓቀፉን የ”ሂዮጎ የተግባር ፍኖተ ካርታ” (Hyogo Framework for Action) መሰረት በማድረግ ነበር፡፡ ሆኖም የሂዮጎ ዓለም ዓቀፉ ማዕቀፍ በሚጠናቀቅበት በያዝነው ዓመት ኢትዮጵያ በዓይነቱ ታይቶ በማይታወቅ ድርቅ እየተጠቃች ትገኛለች፡፡

የሂዎጎ ዓለም ዓቀፍ ማዕቀፍን የሚተካው እና እኤአ ከ2015 እስከ 2030 የሚዘልቀው ማዕቀፍ ደግሞ ባለፈው መጋቢት በተባበሩት መንግስታት አማካኝነት በጃፓን ስምምነት ላይ የተደረሰበት ዓለም ዓቀፉ “የሰንዳይ የአደጋ ተጋላጭነት ቅነሳ ማዕቀፍ” ነው፡፡ “የሰንዳይ ማዕቀፍ” እንደሚለው ሀገሮች ትኩረታቸውን ቀድሞ ከነበረው የአደጋ አመራር ወይም አያያዝ በትኩረቱ በጣሙን ማስፋት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዓለም ላይ ከ2005 እስከ 2015 ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ በአደጋዎች ሳቢያ ከ700 ሺህ በላይ ህይወት የጠፋ ሲሆን ከ23 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ደግሞ መጠለያ አልባ እንደሆኑ ከተባበሩት መንግስታት የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

አዲሱ ፖሊሲ ከድርቅ ባሻገር ሌሎች ተፍጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን ያቀፈ ሲሆን በሀገር በቀል ተቋሞችና ሃብት እንዲሰራ ተደርጎ ተዘጋጅቷል፡፡ መንግስት ለአደጋ ጊዜ የሚውለውን ዕርዳታ ለማግኘት የታሰበው ከሀገሪቱ ስትራቴጂክ መጠባበቂያ ምግብ ክምችት ነው፡፡ የአደጋ ጊዜ ፈንድና ዓለም ዓቀፍ ርዳታ የሚያሰባስብ የፌደራል መዋቅርም እንደሚቋቋም ይገልፃል፡፡ በተጨማሪም በየደረጃው ቅደም-አደጋና በአደጋ ጊዜ የሚታዩ መረጃዎችን በዘመናዊ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አሰራር ይደገፋል፡፡ ባለፈው ዓመትም የወረዳ ኢንፎርሜሽን ማኔጅመንት ሲስተም ተዘጋጅቶ መጠናቀቁን መንግስት ገልጿል፡፡ እስካሁን ድረስም ከሦስት መቶ በላይ በሚሆኑ ወረዳዎች የአደጋ መንስዔዎች፣ ተጋላጭነት፣ ሰብዓዊና ቁሳዊ አቅም የመሳሰሉ ዝርዝር መረጃዎች ተጠናቅረው እንዳለቁ ታውቋል፡፡

ለዚህም በጠቅላይ ሚንስትሩ የሚመራው የፌደራል የአደጋ ክስተት ስጋት አመራር ምክር ቤት ሲሆን በየደረጃውም እስከ ወረዳ ድረስ አደጋ ክስተት ስጋት ማስተባበሪያ መዋቅር እንደሚፈጠር ፖሊሲው ይገልፃል፡፡ አዲሱ ፖሊሲ ያልተማከለ እና በቅድመ-አደጋ፣ በአደጋ እና ድህረ-አደጋ ትኩረት ላይ አድርጓል፡፡ እስካሁን አደጋ የሚያውጀው ፌደራል መንግስቱ ብቻ ሆኖ የቆየ ሲሆን በአዲሱ ፖሊሲ ግን በክልልና በዞንና በወረዳ ደረጃ በምን መልኩ በይፋ መታወጅ እንዳለበት ዝርዝር መመሪያ እንደሚነደፍ ይገልፃል፡፡

የዘንድሮው መጠነ-ሰፊ ርሃብ የተከሰተው ኢትዮጵያዊያንና ዓለም ዓቀፉ ህብረተሰብ እጅግ በተዘናጉበት ጊዜ ነው፤ በአሁኑ ጊዜ የምግብ ዋስትና እጥረት በሚታይባቸው ወረዳዎች ሲተገበር የኖረው “ፕሮዳክቲቭ ሴፍቲ ኔት ፕሮግራም” (Productive Safety Net Program) ተሻሽሎ እስከ 10 ሚሊዮን ገበሬዎችን እንዲያቅፍ ተደርጓል፡፡ ፕሮግራሙ በሀገራችን ከሚገኙ ከሰባት መቶ ሰባ ያህል የገጠርና ከተማ ወረዳዎች ውስጥ 411 የምግብ ዋስትና ዕጥረት ያለባቸውን ወረዳዎች ይሸፍናል፡፡

ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ የተረጅዎች ቁጥር ከ10 ሚሊዮን በላይ እንደሚሆን መንግስት መግለፁም ክስተቱን የመቀነስና ተጨማሪ እርዳታ ፈላጊዎች እንዳይኖሩ የማድረግ አቅሙ ውስን መሆኑን ያሳያል፡፡ ዓለም ዓቀፉ የህፃናት አድን ድርጅት “ሴቭ ዘ ችልድረን” ግን የለጋሽ ሀገሮች ምላሽ በጣም አነስተኛ መሆኑን በቅርቡ አሳውቋል፡፡ ያም ሆኖ ከድሮዎቹ ድርቆች ጋር ሲወዳደር መንግስት ሞትን በእጅጉ ማስወገድ መቻሉ የፖሊሲው ስኬት ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል ባለሙያች ያስረዳሉ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው ጥንታዊው ጣይቱ ሆቴልም ባለፈው ዓመት በእሳት አደጋ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል፡፡ ቂርቆስ እና መርካቶ የገበያ ማዕከሎችን ጨምሮ በሌሎችም በርካታ አካባቢዎች የተነሱትን ከባድ እሳት አደጋዎችም በጊዜው መቆጣጠር ባለመቻሉ መጠነ-ሰፊ ጉዳት ደርሷል፡፡

ከዓመታት በፊት የተከሰቱት የባሌ ተራሮች ደን ቃጠሎ እና የድሬዳዋ ከተማ ጎርፍ ከፍተኛ ስነምህዳራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳት እንዳስከተሉ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በድሬዳዋ በሐምሌ 1998 ዓ.ም በደረሰው ድንገተኛ ጎርፍ አደጋ ከ250 ሰዎች በላይ መሞታቸውና ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸው ይታወሳል፡፡ መሰረተ ልማቶችና በሺዎች የሚቆጠሩ መኖሪያ ቤቶችም ለመውደማቸው ምክንያት ሆኗል፡፡ ጎርፉ ያንን ያህል አደጋ ሊያደርስ የቻለው በስነምህዳር መራቆትና በመሬት አቀማመጧ ከተማዋ ድሮውንም ለድንገተኛ ጎርፍ አደጋ የተጋለጠች በመሆኗ እና መንግስት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራ መስራት ባለመቻሉ እንደሆነ ጥናቶች ይገልፃሉ፡፡

መንግስት ፖሊሲውንና ስትራቴጂውን ለመተግበር ብቃት ያለው የሰው ኃይል፣ የገንዘብ እና የዘመናዊ ቴክኖሎጂ እጥረት ከባድ ፈተና እንደሚሆንበት ታዛቢዎች ያስረዳሉ፡፡ በአደጋ ከተከሰተ በኋላም ስለሚደረገው ድጋፍም መንግስት ዝግጁነት ግልፅ አይደለም፡፡ በሌላ በኩል በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ሀገሪቱ ወደፊትም ለበርካታ ተፍጥሯዊ አደጋዎች ተጋላጭነቷ እየጨመረ እንደሚሄድ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ መንግስት መሬትን ጨምሮ የተፈጥሮ ሃብቶችን የሚይዝበት መንገድ ብሎም የአደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስና ለመቋቋም እየተሰሩ ያሉት ስራዎች ግን ከአደጋው መጠን አንፃር በቂ እንዳልሆኑ የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶችና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በማሳሰብ ላይ ናቸው፡፡