Workneh Gebeyehu -
Workneh Gebeyehu –

ዋዜማ ራዲዮ- የሳውዲ አረብያ መንግስት በሀገሪቱ የሚኖሩ እና ህጋዊ ወረቀት የሌላቸው ሰዎች ሀገሪቱን በ90 ቀናት ውስጥ ለቀው እንዲወጡ ባስቀመጠው ቀነ ገደብ መሰረት ኢትዬጵያዊያን የማይወጡና በእድሉ የማይጠቀሙ ከሆነ ከሚገጥማቸው ችግርና በሳውዲ መንግስት ከሚወሰድባቸው እርምጃ የኢትዮጵያ መንግስት ሊታደጋቸው እንደማይችል አስታወቀ።

የኢትዮጵያ መንግስት በጉዳዩ ላይ ድርድር ከማድረግና መፍትሄ ከማፈላለግ ይልቅ ዜጎቹ ሳዑዲ አረቢያን እንዲለቁ ከውሳኔ ላይ ደርሷል።

የዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም ጉዳዩን በተመለከተ ሀሞስ ዕለት (ዛሬ) በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መንግስት ዜጎች ከሳዑዲ አረቢያ በተገቢው የመንግስት ድጋፍ እንዲወጡ ለማስቻል ኮማንድ ፖስት አቋቁሞ እየሰራ ነው።
አቶ መለስ እንዳሉት በህገ ወጥ መንገድ ድንበር አቋርጠው የገቡ ስደተኞች፣ ቋሚ ቦታ ሳይኖራቸው በመዘዋወር በህገ ወጥ መንገድ የሚሰሩ ስደተኞች፣ የስራ እና የመኖሪያ ፍቃድ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ የውጭ ሃገራት ነዋሪዎች፣ የስራ ፍቃድ ኖሯቸው ነገር ግን የመኖሪያ ፍቃድ መታወቂያ ካርድ የሌላቸው፣ ለዑምራና ሃጂ ሄደው በዚያው የቀሩ ወይም የቆይታ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ነዋሪዎች እና ያለ ሃጂ ፍቃድ የተጓዙ አማኞች በሳዑዲ መንግስት ህገ ወጥ የሚባሉ ናቸው።

ለበርካታ አመታት ኑሯቸውን በሳውዲ አረብያ ያደረጉና ህጋዊ ወረቀት ያልተሰጣቸው ኢትዬጵያዊያን በተለይም በምንም አይነት ህገ ወጥ ተግባር ውስጥ ያልተሳተፉ ዜጎችን የሀገሩ መንግስት ጉዳያቸውን አይቶ ፍቃድ እንዲሰጣቸው በሳውዲ እና በሪያድ ለሚገኙ የኢ/ት ኤምባሲና የቆንፅላ ፅ/ቤትን ደጋግመው ቢጠይቁም ምንም አይነት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ባለመደረጉ ከዚህ ቀደም ብዙ ዜጎች ወደ ሀገር መመለሳቸው የሚታወስ ነው።

“የተሰጠውን የጊዜ ገደብ አክብረው የሚወጡ  ዜጎች፥ በሚኖሩበት አካባቢ በሚገኙ የኢሚግሬሽን ጽህፈት ቤቶች የመውጫ ቪዛ እንዲያገኙ የሚደረግ ሲሆን ያለ ቅጣት በራሳቸው ትራንስፖርት ወጭ በፈቃደኝነት ከሃገሪቱ እንዲወጡ ይደረጋል” አቶ መለስ እንዳስረዱት ።

የሳዑዲ አረቢያ መንግስት በስደተኞች ጉዳይ ላይ አዲስ አቋም መያዙን ተከትሎ በውጪ ሀገር ዜጎች ላይ ተከታታይ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ነው። ኣኢትዮጵያውያን ከሌሎች ዜጎች በተለየ የቆንስላ አገልግሎት ባለማግኘትና ከመንግስታቸው ጋር ባላቸው ደካማ ግንኙነት ለከፋ እንግልትና ስቃይ ተዳርገዋል።

ከ3 አመት በፊት በተመሳሳይ የሳውዲ መንግስት ከሀገሩ ካስወጣቸው ኢትዬጵያዊያን በተጨማሪ ከ2007 እስከ 2008 መስከረም ወር በነበረው አንድ አመት ብቻ ከ89 ሽህ የሚበልጡ ኢትዬጵያዊያን በሳውዲ መንግስት ተጠርዘው የተመለሱ ሲሆን በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው በሳውዲ እስር ቤቶች የሚገኙም በርካቶች መሆናቸው ይነገራል።