Ethiopian delegation confer with Samantha Power of USAID – Photo USAID

ዋዜማ ራድዮ- ከአንድ ሳምንት በላይ በዩናይትድ ስቴትስ ቆይታ ያደረገው የኢትዮጵያ መንግስት የልዑካን ቡድን ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ የተቋረጠው የአበዳሪዎችና የለጋሾች ድጋፍ እንዲቀጥል ብርቱ ተማፅኖ ማቅረቡን ዋዜማ ለጉዳዩ ጋር ቅርብ ከሆኑ የለጋሽ ድርጅቶች ምንጮች ሰምታለች

በገንዘብ ሚንስትሩ አህመድ ሽዴ የተመራውን የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ የተካተቱበት የልዑካን ቡድን በዓለም ባንክና በዓለም የገንዘብ ድርጅት ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ከተካፈለ በኋላ ከተለያዩ የለጋሽና አበዳሪ ድርጅቶች ተወካዮችና ከአሜሪካ መንግስት የሕዝብ እንደራሴዎች ጋር ተወያይቷል። 

በውይይቶቹ  በኢትዮጵያ የተጀመረውን የኢኮኖሚና የፖለቲካ ተሀድሶ ከጫፍ ለማድረስ የለጋሾች ድጋፍ እጅጉን እንደሚያስፈልግና የተቋረጡ ብድሮችና ድጋፎች መለቀቃቸው ሀገሪቱን ወደተረጋጋ መንገድ ለመመለስ ትልቅ ድርሻ እንዳለው የልዑካን ቡድኑ አስረድቷል። 

የሰሜኑ ጦርነት በመንግስት ሳይፈልግ ተገዶ የገባበት እንደነበርና ጉዳዩን በሰላም ለመፍታት በመንግስት በኩል ዝግጁነት መኖሩን ገልጸዋል። ይህን የመንግስት ዝግጁነት ለማረጋገጥም የተኩስ አቁም መታወጁን አስታውሰዋል። 

ጦርነቱ ካስከተለው ስብዓዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ባሻገር በዓለማቀፍ ደረጃ የተፈጠረው የአቅርቦት መስተጓጎል ኢትዮጵያንም ክፉኛ የተጫናት መሆኑን አውስተዋል። 

መንግስት ከዚህ ቀደም የወሰደውን ዓለማቀፍ ብድር አከፋፈል በተመለከተም ሀገሪቱ ካለችበት ሁኔታ አንፃር ተመልክቶ የብድር አከፋፈሉን የጊዜ ሰሌዳ እንዲሻሻል (የዕዳ ሽግሽግ) የማግባባት ስራ የልዑካን ቡድኑ አንዱ የቤት ስራ እንደነበረም ስምተናል። 

የልዑካን ቡድኑ በተለይ ከአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት ሀላፊ ሳማንታ ፓወር ጋር በነበረው ውይይት መንግስት ለትግራይ ክልል የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦትንና ያለገደብ እንዲፈቅድ የባንክና የመገናኛ አውታሮችን ሙሉ በሙሉ እንዲከፍት ይህም የአሜሪካን መንግስትን ሙሉ ድጋፍ ለማግኘት መሟላት ያለበት ቅድመ ሁኔታ መሆኑ ተገልጦለታል። 

የልዑካን ቡድኑ የስብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦትን ለማሻሻል መንግስት ብርቱ ጥረት እያደረገ መሆኑን ይሁንና በሕወሓት አማፅያን በኩል ተደጋጋሚ ዕርዳታ ማስተጓጎል አጋጥሞ እንደነበረ አስረድተዋል። 

በመንግስት በኩል በትግራይ ክልል መስረታዊ አገልግሎቶችን ለማስቀጠል ፈቃደኝነቱ መኖሩንም ተናግረዋል። 

ውይይቱን የተከታተሉ የለጋሽ ድርጅት ወኪል እንደነገሩን የኢትዮጵያ መንግስት ከዚህ ቀደም አሻፈረኝ ያለባቸውን ጉዳዮች ሳይቀር በመቀበል በአስቸኳይ የብድርና ዕርዳታ ድጋፍ እንዲደረግለት ቀጥተኛ ጥያቄ አቅርቧል። 

ይህ ጥያቄ ከቀረበላቸው አንዷ የአለም የገንዘብ ድርጅት ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጄቫ  ናቸው።  

የአለም የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ከኢትዮጵያ ጋር አቋርጧቸው የነበሩ መርሀ ግብሮችን ሊቀጥል እንደሚችል ዋና ዳይሬክተሯ ክሪስታሊና ጆርጄቫ  በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ ፍንጭ ሰጥተዋል። 

የአለም የገንዘብ ድርጅት  (አይ ኤም ኤም) በ2012 አ.ም የኢትዮጵያ መንግስት የተለያዩ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች እንዲያደርግና ማሻሻያዎቹ ለሚፈጥሩት ጫና በምላሹ የ2.9 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የተራዘመ የብድር አቅርቦት(extended credit facility)እንደሚሰጥ ተስማምተው ነበር።

የብር የውጭ ምንዛሬ ተመንን በፍጥነት ማዳከምም አንዱ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የተወሰደ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ነው። ሆኖም ከ2.9 ቢሊየን ዶላሩ ውስጥ 300 ሚሊየን ዶላሩ በአፋጣኝ ከተለቀቀ በኋላ ቀሪው ብድር ሳይለቀቅ ቆይቷል።

የኢኮኖሚ ማሻሻያው እንደሚፈለገው አለመሄድን ለዚህ በምክንያትነት የሚያቀርቡ ቢኖሩም በሰሜኑ ጦርነት ሳቢያ አሜሪካ በአይ ኤም ኤፍ  ውስጥ ያላትን የድምጽ ብልጫ ተጠቅማ ጫና በማሳደሯ ነው ብድሩ የተቋረጠው የሚሉ አሉ። 

ነገሮች በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉ የተራዘመ የብድር አቅርቦት መርሀግብሩ የሚተገበርበት ጊዜ በዚህ አመት ከወራት በፊት በማለቁም አይኤምኤፍ ለወራት በኢትዮጵያ ምንም አይነት መርሀ ግብር ሳይኖረው ቆይቷል።በዚህም ሳቢያ የገንዘብ ተቋሙ ከወራት በፊት ከ2023 በሁዋላ የሚኖረውን የሀገራትን የኢኮኖሚ እድገት ትንበያ ሲያወጣ ኢትዮጵያን ዘሏት እንደነበር የሚታወስ ነው።

ባለፈው ሳምንት ግን የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ባወጣው ትንበያ ኢትዮጵያን አካቶ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በዚህኛው የፈረንጆቹ አመት 2022 የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የ3.8 በመቶ እድገት እንደሚያስመዘግብ ፣ የዋጋ ንረት አሁንም ከፍተኛ ሆኖ እንደሚቀጥል እንዲሁም የኢትዮጵያ ዕዳ ምጣኔ ከአመታዊ የሀገር ውስጥ አጠቃላይ ምርት አንጻር እየቀነሰ እንደሚመጣ የሚያሳይ ሪፖርት አውጥቷል። 

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የዋዜማ ራዲዮ ምንጮች እንደገለጹልን አይ ኤም ኤፍ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ አንድ ቡድን ልኮ ወቅታዊ የኢኮኖሚ ጉዳዮችን ገምግሞ የተለያዩ መርሀ ግብሮች የሚቀጥልበት ሁኔታን ያመቻቻል ተብሎ ይጠበቃል። 

በአቶ አሕመድ ሽዴ የተመራው የልዑካን ቡድኑ ምንም እንኳን በዋናነት የኢኮኖሚ ጉዳዮችን እንዲያስፈፅም የተላከ ቢሆንም በዋሽንግተን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል የተለያዩ የአሜሪካ የሕዝብ እንደራሴዎችን አግኝቶ ለመነጋገርና የመንግስትን አቋም ለማስረዳት ሞክሯል። [ዋዜማ ራዲዮ]