CGF board members
CGF board members

ዋዜማ ራዲዮ- ኢትዮጵያ የአየር ንብረት አደጋን ለመቋቋም ለአለማቀፉ የአረንጓዴ ፈንድ (Green Climate Fund) ያቀረበችው የሁለት ነጥብ አምስት ቢሊየን ብር ፕሮጀክት ከስድስት ሀገሮች ተቃውሞ ቀርቦበት ተቀባይነት ሳያገገኝ ቀረ።
ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ከሁለት ሚሊየን በላይ ዝቅተኛ ኑሮ ላላቸውና ለአየር ንብረት አደጋ ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን ለመደገፍ የሚውል ነበር።
ባለፈው ሳምንት የመንግስታቱ ድርጅት የአረንጓዴ ፈንድ የቦርድ አባላት ባደረጉት ስብሰባ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ገምግመው ከሁለት ቢሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ የፈቀዱ ሲሆን በበርካቶች ተቀባይነት ያገኛል ተብሎ የተጠበቀው የኢትዮጵያ ጥያቄ ውድቅ ተደርጓል።

ታንዛኒያ ግብፅና ሞሮኮ ከአፍሪካ አህጉር ድጋፉን ያገኙ ሲሆን ታጃኪስታን ያረጀ የሀይል ማመንጫ ግድቧን ለማደስ የሁለት መቶ ስልሳ አምስት ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አግኝታለች።
በድርቅ አደጋ እየተጠቃች ያለችው ኢትዮጵያ ድጋፍ ማግኘት ይገባታል ብለው የተከራከሩ የቦርድ አባላት ቢኖሩም አሜሪካ፣ ካናዳ፣ስዊዘርላንድ፣ስዊድን፣ጀርመንና ጃፓን የኢትዮጵያ ጥያቄ መስፈርቱን አያሟላም በሚል ተቃውመውታል።
የአረንጓዴ ፈንድ ሀያ አራት የቦርድ አባላት ያሉት ሲሆን መቀመጫውን በደቡብ ኮርያ ያደረገ የመንግስታቱ ድርጅት  ተቋም ነው።
ለድርጅቱ መቋቋም ኢትዮጵያ የመሪነቱን ሚና የተጫወተች ሲሆን የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ለፈንዱ መመስረት ከፍ ያለ አስተዋፃኦ  አድርገዋል።
የፈንዱ የቦርድ አባላት የኢትዮጵያን ጥያቄ ያልተቀበሉበትን ምክንያት ከአራት ወራት በኋላ ሲሰበሰቡ ይፋ እንደሚያደርጉ ለዋዜማ ተናግረዋል።
በሂደቱ የተሳተፉ ኢትዮጵያውያንና የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች ግን ኢትዮጵያ ያቀረበችው ስነድ “የይድረሰ -ይድረስ” የተዘጋጀና የሚጠበቅበትን መስፈርት ያላሟላ ስለነበረ ነው ሲሉ ያስረዳሉ።
“ዘመኑ የሚጠይቀውን አዳዲስ መረጃና አለማቀፍ ሁኔታን ያላገናዘበ ሰነድ ነው። እኛ የባለሙያ ድጋፍ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆናችንን በተደጋጋሚ ገልፀን ነበር። የኢትዮጵያ መንግስት ግን ፈቃደኝነት አላሳየም”  ይላሉ በለንደን የአየር ንብረት ጉዳይ ጥናት የሚያደርግ ተቋም ባልደረባ።በሚቀጥለው ሁለት ሳምንታት ወደ አዲስ አበባ አቅንተው በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ሀሳብ እንዳላቸውም ነግረውናል።
በአዲስ አበባ ያለውና ከስልሳ በላይ ድርጅቶችን ያካተተው ሀገር አቀፍ መድረክ አባላትም ስለ ሰነዱ መረጃ እንደሌላቸውና ምክክር እንዳልተደረገበት ለዋዜማ ተናግረዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት የልማት ፕሮግራም UNDP  ስነዱን በውክልና ይዞ ለአረንጓዴ ፈንድ ተቋም ማስገባቱን በሰነዱ ይዘት ላይ ግን ማሻሻያ አለማድረጉን ተረድተናል።
በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃዎችን ከታች በድምፅ ያገኛሉ።

https://youtu.be/pW6nEP3QkP8