Axum Obelisk
Axum Obelisk

(ዋዜማ ራዲዮ)-ኢትዮጵያውያንን እና ኢትዮጵያን የሚመለከቱትን መራር ቀልዶች የውጪ ዜጎች የሚያውቋቸውን ያህል ብዙ ኢትዮጵያውያን አያውቋቸውም። ያም ኾኖ በብዛት የውጪ ዜጎች የሚያውቋቸው እነዚህ ቀልዶች የኢትዮጵያውያንን የማንነትን ኩራት የሚነኩ ናቸው። እነኚህን ቀልዶች የተመለከተው መዝገቡ ኃይሉ የሚከተለውን ዘገባ አዘጋጅቷል። አድምጡት

 

ከጥቂት ወራት በፊት ዝነኛው የ ሂፖፕ አቅንቃኝ ታይሪስ ጊብሰን አንድ ኢትዮጵያዊ ጎልማሳ የሚያናግርበት ቪዲዮ በፌስቡክ ገጹ ላይተገኝቶ ነበር። ታይሪስ ጎልማሳውን አቅፎ በቪዲዮው ላይ ቤተሰቡን እንዲያናግር ግብዣ ሲያደርግለት ይታያል። እግረ መንገዱንም ታይሪስስለ ኢትዮጵያ የሚያውቀውን ለመናገር ሞክሯል። ስለኢትዮጵያ የሚያውቀው ግን በአገሩ የሚኮራ አንድ ኢትዮጵያዊ ታይሪስም ይኹንሌላው የውጪ ዜጋ ስለ ኢትዮጵያ እንዲያውቅለት ከሚፈልገው ይልቅ እንዲነሳበት የማይፈልገው ቁስሉ ነበር። “ምግብ አገኘህ? ሆድህሞላ?” የሚለው የታይሪስ ጥያቄ በእቅፉ ለነበረው ኢትዮጵያዊ ጎልማሳ ሚስጥሩ የተገለጠለት አይመስልም። በፈገግታ “አዎን!” ብሎሲመልስ የሚታየው ኢትዮጵያዊ ምናልባትም እንደ ብዙ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ዓለም ስለኢትዮጵያ ሲያስብ መጀመሪያ የሚመጣለት ምስልበረሃብ ደርቀው አጥንታቸው የገጠጠው ወገኖቻችን ምስል መኾኑ አልታወቀው ይኾናል። [ ምስሉን እዚህ ሊመለከቱት ይችላሉ- https://www.facebook.com/tyrese/videos/880929991934598/

ፈረንጅ ሁሉ በአክሱም ስልጣኔ፣ በላሊበላ ውበት፣ በአድዋ ድል የሚያውቀን አንዲመስለን የሚያደርገን ፈረንጆቹን አኛ ስናገኛቸውየሚነግሩን ዲፕሎማሲያዊ ንግግር ሳይኾን አይቅርም። በልባችን ያለው የማንነት ኩራታችን ምን ያህል ትልቅ እንደኾነ መረዳታቸውበሚፈጥርባቸው ተጸእኖ ምክንያት መስማት የምንፈልገውን ብቻ ስለሚነግሩን ስለኛ የሚያስቡትን እንዳናውቅ ምክንያት ኾኖ ጆሯችንንለእኛው ባዳ ያደርግብናል። እንደ ታይሪስ ያለ ግድ የለሽ እንዲህ ፊት ለፊት እስኪናገረውም ድረስ እኛ ብቻ የማናውቀው ምስጢር ኾኖመቆየቱ አይቀርም። ለብዙዎች የውጪ ዜጎች ግን በጣም የታወቀው ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን የሚወክለው ቅድመ ድመዳሜ(Prejudice)በአመዛኙ ደጋግሞ የደቆሰንን ድርቅና ርሃብ የሚመለከት ነው።

የድርቅ ታሪካችን እኛ እንደምንመኝው ሊላቀቀን አልቻለም።

እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2002 አካባቢ ተከስቶ የነበረውን ድርቅ አስመልክቶ Daily Trust የተሰኘ ጋዜጣ ‘Ethiopia, an embarrassment to Africa’ወይም “ኢትዮጵያ የአፍሪካ ማፈሪያ” የሚል ጽሑፍ አውጥቶ በወቅቱ ብዙዎችን አሳዝኖን ነበር።  ችግሩ ይህን በቀላሉየማይለቅ የአእምሮ ምስል ለማጥፋት የሚያስችለን አቋም ላይ አለመድረሳችን ነው። አሁንም ድርቅ ብዙዎችን እየጎዳ ባለባት አገር ስለገጽታ መጭነቅም አጉል ጉዳይ ሳይኾን አይቀርም።

ጉዳዩ ስር ከመስደዱ የተነሳም ለኛ ባያስቀንም ይህንኑ ቅድመ ድምዳሜ መሰረት ያደረጉ ብዙ ቀልዶች መኖራቸው ነው። አንድ ሰሞንኦክስፎርድ የእንግሊዘኛ መዝገበ ቃላት ኢትዮጵያን እንደምሳሌ የሚያነሳውን የድርቅ ትርጉም እንዲያሻሽል የሚጠይቅ መማጸኛ ሲፈረምነበር። አነኚህን መራር ቀልዶች ለሰማ ግን የኦክስፎርዱን ምሳሌ ገር ነው ሳያሰኘው አይቀርም።

ከነዚህ ቀልዶች መካከል በጣምየተለመዱትን  አነዳንዶቹን እንይ። ማንኛውም በሌላው ማንነት ላይ የቀረበ ቀልድ ለሰሚዎቹ አስቂኝ የሚኾነው ምክንያታዊነትንናመረጃን መሰረት አለማድረጉ ላይ ነው። ምክንያታዊነትና እውነታን ለማረጋገጥ የሚደረግ ሙከራ ስራን ከመጥየቁም ባሻገር የቀልዱንዓላማ ስለሚያበላሸው ያለ ዕውቀትም ቢኾን ቀልዱ ይቀርባል እኛን ያልኾነውም ይስቃል።

 

አብዛኞቹ ቀልዶች በምዕራቡ ዓለም እንደተለመደው በጥያቄና መልስ መልክ የቀረቡ ናቸው። አንዱ እንዲህ ይላል፤

“የኢትዮጵያ ምግብ በልተህ ታውቃለህ?” ይላል አንዱ ጠያቂ

“ኧረ እነርሱም አልበሉ!” ይላል መላሹ። እጅ የሚያስቆረጥመውን ምግባችንን የረሃቡ ምስል ቢያበላሽበት።

“አንድ መቶ ዝንቦችን በአንዴ ለመግደል ምን ታደርጋለህ?” ይላል ሌላው ጠያቂ ፤

“የአንዱን ኢትዮጵያዊ ፊት በመጥበሻ በመምታት ነዋ!” ይላል መላሹ።

ይህ እንግዲህ የተራድዖ ድርጅቶች እርዳታ ለማሰባሰብ ብለው ለምዕራቡ ዓለም ካሰራጩት ምስል የተገኘ ዕውቀት መኾኑ ነው። ይህንለመሰለው ቀልድ በአንድ ወቅት ትሬቨር ኖህ የሚባለው የደቡብ አፍሪካ ኮሜዲያን የቀልድ ምላሽ ሲሰጥ “ኧረ ዝንባችንን እሽ ማለትአላቀትንም!” ሲል የተናገረበት ጉዳይ ነበር። ቀልዱ ቀጥሏል።

“የረሃብ አድማ ላይ ያለን ኢትዮጵያዊ ምን ተብሎ ይጠራል?” ይላል ጠያቂ መላሹም “ኢትዮጵያዊ ነዋ!” ይላል።

“አንድ መቶ ኢትዮጵያውያንን ለመግደል ምን ታደርጋለህ?” ይላል ሌላው ጥያቄ ምላሹም “ከገደል አፋፍ ላይ ብስኩት እወረውራልሁ!”ነው።

ብዙ አገሮች እና ሕዝብ የረሀብም ባይኾን ሲነሳባቸው የማይወዱት ይህን የመሰለ ማንነት የሚነካ ቀልድ አላቸው። ለምሳሌ ያህልምጥቁር አሜሪካውያን ካለፈው ታሪካቸው ውስጥ ባርነትን አስመልክቶ የሚቀለዱ ቀልዶች ቁስላቸውን የሚያስታውሳቸው ጉዳይ ነው።አሁንም ድረስ ነጮቹም ይኹኑ የሌላው ዘር አባላት ይህን ጉዳይ አንስተው አይቀልዱም። ባርነትን በተመለከተ ቀልድ ሲቀልዱ ተቀባይነትያላቸው ራሳቸው ጥቁር አሜሪካውያን ብቻ ናቸው። አይሁዳውያንም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የደረሰባቸውን አሰቃቂ ግፍከራሳቸው በቀር ማንም ሲቀልድበት መስማት አይፈልጉም። ችግሩ ክልከላው የሚሰራው አነርሱ ባሉበት እና የሰውን ማንነት በቀልድም ቢኾን መንካት የማይዋጥላቸው ሰዎች አስካሉ ድረስ ብቻ ነው።  በዚህ የኢንተርኔት ዘመን ማንም ራሱን ደብቆ ማንንም ቢያንጓጥጥ የሚጠይቀው የለም።

Lalibela

የረሃቡ ቀልድ አሁን አሁን በኢትዮጵያ ላይ የተወሰነ ቢመስልም ይህን  የመሰለው መራር ቀልድ ዒላማ ከኾኑት ሕዝብ መካከልአየርላንዳውያንም ይገኙበታል። ቀልዱ በአየርላንዳውያን ላይ መኖሩ አስገራሚ የሚያደርገው ይህ የአየርላንድ ረሃብ ተከስቶ የነበረው ከ170ዓመት በላይ ማስቆጠሩ ነው። በዚህ ከባድ ረሃብ ወቅት  ወደ 1 ሚሊዮን የሚጠጉ አየርላንዳውያን በረሃብ ሲሞቱ ለሎች 1 ሚሊዮንየሚኾኑ ደግሞ አሁን ኤርትራውያን እና ኢትዮጵያውያን እንደሚያደርጉት አይነት አደገኛ የባህር ጉዞ ወደ አሜሪካ እንዲያደርጉአስገድዷቸው ነበር። የባሕር ራት ኾነው የቀሩም ብዙዎች ናቸው። ይህን የመሰለ ችግር የተከሰተባቸውና ስደትን የመረጡ ብዙዎችአውሮፓውያን በዚሁ ዘመን አካባቢ ነበሩ። ጥሩ ምሳሌ ከሚኾኑትም መካከል አሁን በሃብት ቁንጮ ላይ የሚገኙት ስዊድናውያን ከስደትየተረፋቸው ሲሶ የሚኾነው ሕዝባቸው ብቻ ነበር።

ባለፈው ዓመት የቢቢሲው ቻናል 4 ይህን የአየርላንድን ረሃብ የሚመለከት የቀልድ ፕሮግራም ማዘጋጀት ጀምሮ ነበር። ይህ ረሃብ ወይምጠኔ የሚባል ፕሮግራም አቅዱ ከተነገረ ጀምሮ በተሰበሰበ 50 ሺህ የአየርላንዳውያን አቤቱታ ፊርማ ምክንያት ሳይተላለፍ በውጥንቀርቷል። በሌላ ጉዳይ ላይ ሲቀልዱ ለከት የላቸውም የሚባሉት አየርላንዳውያን ይህ አሳዛኝ ታሪካቸው የቀልድ ምክንያት ሊኾንእንደማይገባ አጠንክረው መቃወማቸው “የቀልድ ልክ የት ድረስ መኾን አለበት?”የሚል ጥያቄ አንዲነሳና የንግግር ነጻነት የት ደረስመሔድ እንደሚገባው ያነጋገረ ጉዳይ ኾኖም አልፏል።

እንግዲህ ከተከሰተ 170 ዓመት ያህል ያለፈው የድርቅና የረሃብ ጉዳይ ላይረሳ የታተመ በሚመስልበት ዓለም አሁንም እየተራብን ለርዳታየዘረጋነው እጃችን አሁንም አለመታጠፉ ጉዳዩን እንደሚያብሰው መረዳት አያዳግትም። አሁንስ ቢኾን እየተራበ ያለውን ወገኑን መመገብያልቻለ ሕዝብ ምን ክብር ይኖረዋል?