Frehiwor Tamiru, CEO EthioTelecom- FILE

ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ  ፍሬህይወት ታምሩ ሰሞኑን የቴሌኮም ዘርፍ ያለበትን ብድር አስመልክቶ ከአበዳሪዎቹ የቻይና ባንኮች ጋር ለመወያየት ቻይና ደርሰው ተመልሰዋል። 

ቻይና የመሄዳቸው ዋና ምክንያትም ኢትዮ ቴሌኮም ለኔትወርክ ማስፋፊያ ስራዎች ተበድሮት የነበረውን ገንዘብ አስመልክቶ ከቻይና ባንኮች ጋር ለመወያየት ነው።ዋና ስራ አስፈጻሚዋ በቻይናው ቆይታቸው ከሀገሪቱ ኤክስፖርት ኢምፖርት (exim) ባንክ ጋር ስለመወያየታቸው ከምንጮቻችን ሰምተናል።በዚህም የኢትዮ ቴሌኮምን ብድር ለመክፈል የተጨማሪ የሶስት አመት ማራዘምያ አበዳሪዎቹ መፍቀዳቸውን ሰምተናል።

 ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቅርቡ ለቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ስብሰባ ቤይጂንግ በነበሩት ጊዜ በቴሌኮም ዘርፉ ብድር አከፋፈል ላይ ጅምር ውይይት ያደረጉ ሲሆን  ዋናው ውይይት የተደረገው ግን የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬ ህይወት ታምሩ ቻይና በተጓዙበት ጊዜ የተፈጸመ ነው።

 ኢትዮ ቴሌኮም በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2010 በቻይናዎቹ ሁዋዌ እና ዜድቲኢ አማካይነት ሰፊ የቴሌኮም ኔት ወርክ ማስፋፊያ ሲሰራ በኩባንያዎቹ በኩል የቻይና ባንኮች ከሶስት ቢሊየን ዶላር በላይ ብድርን አቅርበዋል። የተሰራው የኔትወርክ ማስፋፊያም እስከ 80 ሚሊየን የሞባይል ስልክን ማስጠቀም የሚችልና የኢንተርኔት ተጠቃሚ ቁጥርንም እስከ ጉድለቱ ከፍ ያደረገ ነው። የዚህን ማስፋፊያ ተከትሎም ኢትዮ ቴሌኮም ቁጥር አንድ የኢትዮጵያ ትርፋማ ኩባንያ ሆኗል። እርግጥ የዘርፉ ብቸኛ አገልግሎት አቅራቢ መሆኑም ለትርፋማነቱ አስተዋጽኦ አድርጎለታል።

     ሆኖም ኩባንያው ብድር ከመክፈል አንጻር የውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግር ሆኖበት በመቆየቱ የኢትዮጵያን የውጭ ብድር ጫና ከፍተኛ እንዲሆን ካደረጉትና መንግስትም ለልማት ድርጅቶች የውጭ ብድር ዋስትና መስጠት እንዲያቆም ካደረጉት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ውስጥ ሆኗል። 

ሆኖም በቅርቡ ከተጠራቀመበት ብድር ውስጥ የተወሰነውን መክፈል ችሏል። ይህን ተከትሎ በተደረገ ድርድርም የሶስት አመት መክፈያ የማራዘሚያ ጊዜ ተሰጥቶታል ተብሏል።የሶስት አመት ማራዘሚያ አላነሰም ወይ በሚል ለምንጫችን ላነሳነው ጥያቄ “ ኩባንያው ከአሁን በሁዋላ ከፍተኛ ብድር የሚወስድበት እድል ጠባብ በመሆኑ ሶስት አመት ተጨማሪ ጊዜ በቂ ነው።  ኩባንያውም ከዚህ በላይ አልፈለገም” ብለዋል።

     ከቻይና በኩል የብድር መክፈያውን ጊዜ የማራዘም ፍቃደኝነት የመጣው ምናልባትም ኢትዮ ቴሌኮም እየሄደበት ካለው የፕራይቬታይዜሽን ሂደት ተጠቃሚ ለመሆን አስበው ሊሆን ይችላል። አሁን ላይ የኢትዮጵያ መንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዘዋወር ከጀመረው ስራ ውስጥ ኢትዮ ቴሌኮምን ቅድሚያ ሰጥቶታል።

ዋዜማ ራዲዮ ያገኘችው መረጃ እንደሚያሳየውም ኩባንያውን ወደ ግል ለማዞር እየተደረገ ባለ ጥረት ቢያንስ ወደ ሁለት ሊከፈል ይችላል። አንዱ መሰረተ ልማቱን የሚይዝና ሌላው ደግሞ ኔትወርክን ከመሰረተ ልማት ባለቤቱ እየገዛ አገልግሎት የሚሰጥ ሊሆን ይችላል። ወደ ግል የሚዞረው በብዛትም የአገልግሎት ዘርፉ ሊሆን እንደሚችል ሰምተናል። በዚህ ዘርፍ ላይ ደግሞ የቻይና ኩባንዮች ከወዲሁ ከፍተኛ ፍላጎትን እያሳዩ በመሆኑ ከብድር ጋር የተያያዘው ጉዳይ ላይ መለሳለስን ሳያሳዩ አልቀሩም ።

     ቻይና ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ለባቡር የተበደረቻትን ብድር የመክፈያ ጊዜ እ.አ.አ እስከ 2030 እንዳራዘመችላት ይታወሳል። [ዝርዝር የዋዜማ የድምፅ ዘገባን ከታች ይመልከቱ]

https://youtu.be/AYfRu0Erfsk