ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮ ቴሌኮም የቀድሞ የኦፕሬሽን ክፍል ዋና ሀላፊ እና የሜ/ጀ ክንፈ ዳኘው ወንድም የሆኑት ኢሳያስ ዳኘው ዛሬ የካቲት 19 -2011 ረፋድ ላይ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል፡፡


አቶ ኢሳያስ በኢትዮ ቴሌኮም የNGPO ዳይሬክተር በነበሩበት ወቅት የዩኒቨርሲቲ ኔትዎርክ ዝርጋታ ግንባታ ፕሮጀክትን ዜድ.ቲ.ኢ ለተባለ የቻይና ኩባንያ ያለጨረታ ሰጥተዋል በማለት የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የካቲት 12-2011 ዓም ክስ መመስረቱ ይታወሳል፡፡


ከባድ የሙስና ወንጀል በሚል ሁለት ክሶችን በውስጡ የያዘ መዝገብ የከፈተው አቃቤ ህግ ተከሳሹ ከዜድ.ቲ.ኢ ስራ አስኪያጅ እና ባለቤት ጋር በጥቅም በመመሳጠር የቴሌኮሙ የግዢ መመሪያ ከሚፈቅደው ውጪ የ44‚ 510‚ 971.44 ዶላር ውል እንዲያዝ አድርገዋል ብሏል፡፡


በዚህም ራሳቸውን እና የዜድ.ቲ.ኢ ስራ አስኪያጅ እና ባለቤትን ለመጥቀም ስልጣናቸውን ያለ አግባብ በመጠቀም በቴሌኮሙ እና በሀገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል በማለት አቃቤ ህግ ክሱን አቅርቦ ነበር፡፡


ተከሳሹ በበኩላቸው “ በክሱ ላይ ምንም አይነት መቃወሚያ የለኝም፤ እውነቱ እንዲወጣ ስለምፈልግ አጭር ቀጠሮ ተሰጥቶ በቀጥታ ምስክር ወደ ማሰማት ሂደት ይገባ” በማለት ዛሬ ለችሎቱ ቢገልፁም እንደ ባለሞያ ሊታለፉ የማይገባ ጉዳዮች በክሱ ውስጥ አሉ ያሉት ጠበቃቸው መቃወሚያቸውን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡


በቀዳሚነት ወንጀሉ ከነማን ጋር እንደተሰራ ሳይገለፅ በወንጀል ህጉ አንቀፅ 32(1)(ሀ) እና 33 መጠቀሱ አግባብ አይደለም በማለት መቃወሚያቸውን የጀመሩት ጠበቃው በክሱ ላይ የወንጀል አባሪ፣ የዜድ.ቲ.ኢ ስራ አስኪያጅና ባለቤት እየተባሉ የተገለፁትን ሰዎች ማንነት እና የወንጀል ተሳትፎ በግልፅ አለማወቃችን ለክርክር ይከብዳል ብለዋል፡፡


ጠበቃው አክለውም ዜድ.ቲ.ኢ የቻይና መንግስት ኩባንያ ነው ያሉ ሲሆን ከባለቤቱ ጋር በመመሳጠር የሚለው የአቃቤ ህግ ክስ ከቻይና መንግስት ጋር እንደሆነ ያመላክታል ሰለዚህም ባለጉዳዬ በምን አግባብ ከቻይና መንግስት ጋር በጥቅም እንደተመሳጠሩ በግልፅ ሊቀመጥ ይገባል ብለዋል፡፡


በሁለተኛነት አቃቤ ህግ በክሱ ውስጥ ሹመት፣ ስልጣን እና ከፍተኛ ሀላፊነት እያለ በተለዋጭነት የተጠቀማቸውን ቃላት የተከሳሽ ጠበቃ ተቃውመዋል፡፡ በፀረ ሙስና አዋጁ መሰረት እነዚህ ቃላት ተብራርተው መቀመጥ ያለባቸው ናቸው ያሉት ጠበቃው ግለሰቡ ተሸዋሚ ናቸው ወይንስ ባለስልጣን የሚለው ካልተብራራ ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም ከሚለው ክስ ጋር የሚቃረን ነው ብለዋል፡፡


ቀጥለውም የቀረበው ክስ የ44.5 ሚሊየን ዶላር ውል እንዲፈረም አደረጉ ከማለት በዘለለ በሀገር እና በቴሌኮሙ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አደረሱ ይበል እንጂ የደረሰው ጉዳት በገንዘብ ተተምኖ አልያም ኦዲት ተደርጎ የቀረበ ነገር የለም፤ በክስ ላይ ደግሞ በደፈናው ከፍተኛ ጉዳት የሚል አቀራረብ ሊኖር አይችልም በማለት ተቃውመዋል፡፡


ከዚህም በተጨማሪ የተከሳሽ ጠበቃ ክሱ ድርጊቱ የተፈፀመበትን ቀን እና ሁኔታ እንደማያስረዳ በመግለፅ ማስረጃዎች እንኳን ሳይታዩ ጉደለቱ በግልፅ የሚታይ ነው ብለዋል፡፡ ጥቅምን በተመለከተ ለራሳቸው እና ለሶስተኛ ወገን ጥቅም አስገኙ ተብሎ በክሱ ቢጠቀስም የተገኘው ጥቅም ምን እንደሆነ ግልፅ አይደለም በማለት ክሱ እንዲሻሻል መቃወሚያቸውን በዝረዝር አቅርበዋል፡፡


በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ አንቀፅ 130 መሰረት የተከሳሸ ጠበቃ ባቀረቡት የቃል መቃወሚያ ላይ አቃቤ ህግ ወዲያው ምላሽ መስጠት ያለበት ቢሆንም የቀረበው መቃወሚያ ሰፋ ያለ በመሆኑ ከስራ ባለደረቦቹ ጋር ተወያይቶ እና ዶክመንቶችን ተመልክቶ በፅሁፍ ለማቅረብ ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡


የተከሳሽ ጠበቃ ግን በእስር ላይ ያሉ ባለጉዳያቸውን የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብት ሚጋፋ በመሆኑ እና በህጉ መሰረት መቃወሚያ እና የአቃቤ ህግ ምላሽ በቃል ወዲያው ነው መቅረብ ያለበት በማለት ተከራክረዋል፡፡


የግራ ቀኙን ክርክር ሲከታተል የቆየው ችሎቱ የቀረበው መቃወሚያ ሰፊ በመሆኑ ተለዋጭ ቀጠሮ መሰጠት አለበት ብለዋል፡፡ በዚህም መሰረት አቃቤ ህግ ከ2 ቀናት በኋላ ምላሹን በቃል ይዞ እንዲቀርብ በማለት ለየካቲት 22 ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡


አቶ ኢሳያስ ከላይ ክስ የተመሰረተባቸውን የዩኒቨርሲቲ ኔትዎርክ ዝርጋታ ፕሮጀክት ጨምሮ ፣ ኢትዮ ቴሌኮም በሶማሌ ክልል ባደረገው የፓወር ፕላንት ፕሮጀክት እና ያለ ጨረታ የተቀጠረ የውጪ አማካሪ ድርጅትን በሚመለከት በሙስና ተጠርጥረው ከ3 ወራት በላይ ምርመራ ሲደረግባቸው ቆይቷል፡፡


ክስ እስኪመሰረት ባለው ጊዜም በከፍተኛው ፍርድ ቤት እና እና በጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኛ ሰሚ ችሎት በተደጋጋሚ ዋስትና ሲፈቀድላቸው እና በፖሊስ ይግባኝ ሲጠየቅባቸው ነበር፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]