Africa Rising on global media outlets
Africa Rising on global media outlets

(ዋዜማ ራዲዮ) Africa Rising ወይም አፍሪካ እየተነሳች ነው የሚለው ተስፋ ያዘለ አባባል የአፍሪካን የኢኮኖሚ ኹኔታ የሚገልጽ መፈክር ኾኖ መሰማት ከጀመረ አመታት ተቆጥረዋል። በዚያም ልክ የለም አፍሪካ እየተነሳች አይደለም የሚሉ ተጠራጣሪዎች ይህንን መፈክር እየተቃወሙ መከራከሪያዎቻቸውን አቅርበዋል።

የአፍሪካ ትንሳዔ ምልክት ተደርገው ከተወሰዱት ተስፋ ሰጪ ነገሮች መካከል፤ የአፍሪካ አገራት በአመዛኙ ከቻይና ጋር ባላቸው ስምምነት ምክንያት እየተገነቡ ያሉ የመሰረተ ልማት አውታሮች እንደ መንገዶች፣ ድልድዮች፣ የኃይል ማመንጫዎች እና የቴሌኮም አገልግሎቶች መስፋፋት በአንድ በኩል ሲገኙ በሌላ በኩል ደግሞ እኤአ በ80ዎቹና በ90ዎቹ የነበሩት የፖለቲካ አለመረጋጋቶች እየቀነሱ መምጣታቸው ነው። ለመሆኑ እውነታው ከወዴት አለ ?

መዝገቡ ሀይሉ በጉዳዩ ዙሪያ ተከታዩን ዘገባ አሰናድቷል አድምጡት

Africa Rising ወይም አፍሪካ እየተነሳች ነው የሚለው ተስፋ ያዘለ አባባል የአፍሪካን የኢኮኖሚ ኹኔታ የሚገልጽ መፈክር ኾኖ መሰማት ከጀመረ አመታት ተቆጥረዋል። በዚያም ልክ የለም አፍሪካ እየተነሳች አይደለም የሚሉ ተጠራጣሪዎች ይህንን መፈክር እየተቃወሙ መከራከሪያዎቻቸውን አቅርበዋል።

የአፍሪካ ትንሳዔ ምልክት ተደርገው ከተወሰዱት ተስፋ ሰጪ ነገሮች መካከል፤ የአፍሪካ አገራት በአመዛኙ ከቻይና ጋር ባላቸው ስምምነት ምክንያት እየተገነቡ ያሉ የመሰረተ ልማት አውታሮች እንደ መንገዶች፣ ድልድዮች፣ የኃይል ማመንጫዎች እና የቴሌኮም አገልግሎቶች መስፋፋት በአንድ በኩል ሲገኙ በሌላ በኩል ደግሞ እኤአ በ80ዎቹና በ90ዎቹ የነበሩት የፖለቲካ አለመረጋጋቶች እየቀነሱ መምጣታቸው ነው።

በ80ዎቹና በ90ዎቹ የነበሩት ትላልቅ ጦርነቶች በእጅጉ ቀንሰዋል፣ የመንግስት ግልበጣዎችም እንደቀድሞው በተደጋጋሚ አይታዩም። ከዚህም በተጨማሪ የትምህርት እና የጤና አግልግሎት ቀድሞ ከነበረበት እየጨመረ መምጣቱ ለተስፈኞቹ ተንታኞች የመከራከሪያ ምክንያት ኾነው ሲቀርቡ ይስተዋላል።

አፍሪካ እየተነሳች ነው የሚለው አባባል የአፍሪካን ሰፊና የተወሳሰበ የፖለቲካና የማኅበራዊ ነባራዊ ኹኔታ ያላገናዘበ ነው የሚሉት ተጠራጣሪዎች አፍሪካ አንድ አገር አይደለችም። በመኾኑም በደምሳሳው አፍሪካ እየተነሳች ነው የሚለው አባባል በተወሰኑ የአፍሪካ አገራት እውን ቢኾን እንኳን ሁሉም የአፍሪካ አገራት ያሉበትን ነባራዊ ኹኔታ የሚገልጽ ሊኾን አይችልም ይላሉ። በስፋቷ በዓለም ሁለተኛ የኾነችው አፍሪካ በቆዳ ስፋት አውሮፓ፣ ዩኤስ አሜሪካ፣ ቻይና፣ ሕንድና ጃፓን በአንድ ላይ ካላቸው ስፋት ትበልጣለች። እንደ ቆዳ ስፋቷ ሁሉ አፍሪካ ውስጥ ያለው የማኅበራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ኹኔታ የተሰባጠረና በአንድነት ሊገለጽ የማይችል በመኾኑ አፍሪካን በአጠቃላይ በዚህ መፈክር ማጠቃለል ቀቢጸ ተስፋ አድርገው ይቆጥሩታል እነኚሁ ተንታኞች።

በኢንደስትሪ ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ካለችው ከደቡብ አፍሪካ አንስቶ አስተማማኝ መንግሥት እንኳን እስከሌላት ሶማሊያ ድረስ በዚህ መፈክር ጥላ ስር የተካተቱት አገራት ያሉበት የፖለቲካ ኹኔታም በእጅጉ የተለያየ ነው። በ80ዎቹና በ90ዎቹ የነበሩት አይነት ጦርነቶች መቀነሳቸው እውነት ቢኾንም አሁንም ግልጽ የኾነ የፖለቲካ አለመረጋጋት የሚታይባቸው አገሮች በርካታ ናቸው።

 

ሰብአዊ መብትና ዲሞክራሲ ያልተከበረባቸው እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ለጊዜው የተረጋጋ የፖለቲካ ኹኔታ ያለባቸው ቢመስሉም በሕዝባዊ አመጽም ይኹን በጦርነት ተመልሰው ወደ አለመረጋጋት እንደማይገቡም ዋስትና የሚኾን ነገር የለም። በተፈጥሮ ሐብታቸው ምክንያት ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮችን የሚስቡትም የአፍሪካ አገራት ይኸው ሀብታቸው ርግማን በመኾን በማያላውሳቸው የሙስና አዙሪት ውስጥ መዘፈቃቸው ናይጄሪያን ለመሳሰሉት አገራት ትልቅ መሰናክል እንደኾነባቸው ይገለጻል።

ይህን የአፍሪካ ትንሳዔ ክርክር በቅርቡ የተቀላቀለው በTom Burgis የተጻፈው The Looting Machine የተባለው መጽሐፍ ይህንኑ የትንሳዔውን እውነተኝነት ከሚጠራጠሩት መካከል አንዱ ነው። በነዳጅ ሀብቷ በአፍሪካ ቀዳሚ የኾነችውን ናይጄሪያ በርጊስ ከሚያነሳቸው ምሳሌዎቹ አንዷ ነች።

ቀደም ሲል በአፍሪካ የ Financil Times ዘጋቢ የነበረው ቶም በርጊስ ናይጄሪያ ይህ የነዳጅ ሀብቷ ያመጣባትን ችግር ያሳያል። ጸሐፊው ናይጄሪያ ያላት የነዳጅ ዘይት ገቢ የአገሪቱን የመገበያያ ገንዘብ ዋጋ ከፍ እንዲል አድርጓል ይላሉ። ይህም የአገሪቱ ገንዘብ ዋጋ መጨመር በሌሎቹ የአገሪቱ ምርቶች ላይ ተጽዕኖ አድርጓል። የገንዘቡ ጥንካሬ ማደግ ከ ወጪ ንግድ ይልቅ የገቢ ንግድን ስለሚያበረታታ የኢንደስትሪ ምርቶቿ እንኳን ለዓለም ገበያ ሊቀርቡ ከቻይና በሕገ ወጥ መንገድ የሚገቡትን ምርቶች ለመፎካከር አቅም ያንሳቸዋል። በዚህም ምክንያት የናይጄሪያ ኢኮኖሚ 90% በነዳጅ ዘይት ሽያጭ እና በነዳጅ ቀረጥ ላይ ብቻ ጥገኛ እንዲኾን አድርጎታል።

ይህ የነዳጅ ዘይት ሽያጭ የሚያስከትለው ሌላም ጣጣ አለ። ይህን የነዳጅ ሽያጭ ገቢ መሰረት ያደረገው ሙስና እንዲባክን የሚያደርገው የገንዘብ መጠን ግዙፍነት ኢኮኖሚዋን የሚያናጋ ነው። በርጊስ የጠቀሱት በ2012 የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው በ10 ዓመት ውስጥ ብቻ በሙስና ምክንያት የባከነው ገንዘብ 37 ቢሊዮን ዶላር እንደነበረ ነው። ይህም የገንዘብ መጠን የራሷን የናይጄሪያን ጨምሮ ግማሽ ያህሉን የ አፍሪካ አገራት የበጀት መጠን የሚበልጥ የገንዘብ መጠን ነው።

የቶም በርጊስ መጽሐፍ በአፍሪካ ውስጥ ላሉት ሕገወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች ዓለም አቀፍ የንግድ አጋሮቻቸውንም ጠቁሟል። ከሁሉም አስገራሚየኾነው ኢትዮጵያን ጨምሮ በብዙ የአፍሪካ አገሮች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ እጁ ያለበት China International Fund ወይም የቻይና ዓለም አቀፍ ፈንድ የተሰኘው ድርጅት ነው። ይህ ድርጅት 88 Queens Way በሚል ሌላ የኮድ ስሙም ይታወቃል። በውስጡም በርካታ የመሰረተ ልማት ግንባታ፣ የነዳጅ ዘይትና የማዕድን ማውጣት ስራ የሚሰሩ ድርጅቶችን ያቀፈ ነው። የድርጅቱ ባለቤት ሳሙኤል ፓ የተሰኙት ግለሰብ እስከ ስምንት የሚደርሱ የተለያዩ ስሞችና መታወቂያ ያሏቸው ተለዋዋጭ ግለሰብ ናቸው።

 

ምንም እንኳን የቻይና መንግሥት ቢክደውም ሳሙኤል ፓ ከቻይና መንግስትና ከስለላ መዋቅሩ ጋር አብረው እንደሚሰሩ መረጃ ሲወጣ ቆይቷል። እኚህ ግለሰብና ድርጅቶቻቸው አለመረጋጋትና ጦርነት ባለባቸው የአፍሪካ አገራት ውስጥ በሚያደርጉት የንግድ እንቅስቃሴ ይታወቃሉ። የፖለቲካ አለመረጋጋት ባለባቸው አገራት ውስጥ የሚገኙትን ነዳጅ፣ አልማዝና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች የሳሙኤል ፓ እና የድርጅቶቻቸው ትኩረቶች ናቸው።

 

አለመረጋጋት ባለባቸው አገሮች ውስጥ የጦር መሳሪያ ያሸጋግራሉ፣ የፖለቲካውም ሒደት ከንግድ አጋሮቻቸው እንዳይነጠቅ አጥብቀው ይሰራሉ። እንደ ምሳሌም ያህል የዚምባቡዌ የምርጫ ውጤት ከ ዛኑ ፒ ኤፍ ፓርቲ እንዳይወጣ ትልቅ ስራ እንደሰሩም ይነገርላቸዋል። በለውጡም በዚምባቡዌ የአልማዝ ምርት ውስጥ እጃቸውን እንዲያስገቡ እድል ተሰጥቷቸዋል።
ለ88 Queens Way ድርጅቶች የፖለቲካ መረጋጋት የሌለባቸው አገራት፣ አምባገነን መንግስታት እና ከሌላው ዓለም በማዕቀብ የተገለሉ አገራት ዋነኛ የንግድ አጋሮቻቸው ናቸው። የአሰራር ግልጽነት አለመኖርና የሙስና መብዛት ለሳሙኤል ፓና ለድርጅቶቻቸው እንደ መልካምአጋጣሚ የሚቆጠሩ የንግድ መንገዶች ናቸው። ያም ኾኖ ሳሙኤል ፓ ብቻ አይደሉም እንዲህ ባለ ጥቁር ( ህገወጥ) ንግድ የሚያተርፉት። ሌሎችም የእስራኤል ደላሎችና የአልማዝ ነጋዴዎች የዚህ አይነቱ ንግድ ተጠቃሚ እንደኾኑም በርጊስ በመጽሐፋቸው አሳይተዋል።
ይህ ሁሉ ችግር ያለበትም የአፍሪካ ኢኮኖሚ እንደሚነገርለት ትንሳዔው እየታየ ነው ወይስ የበለጠ እየወደቀ የሚለው ክርክር ቀጥሏል። የ ቶም በርጊስ መጽሐፍም የዚሁ ክርክር አንድ አካል ብቻ ነው።