• Map-SW-Shewa-and-W-Shewa-Oromiaነፋስ ስልክ ላፍቶና የሰበታ ከተማ አስተዳደር ተፋጠዋል

ዋዜማ ራዲዮ- ዋና ከተማዋን የሚያዋስኑ ልዩ የኦሮሚያ ዞኖች ከአዲስ አበባ አጎራባች ክፍለ ከተሞች ጋር አዳዲስ የመሬት ይገባኛል ዉዝግብ ዉስጥ መግባታቸውን ከዋዜማ ምንጮች ባለፉት ተከታታይ ሳምንታት የተሰበሰቡ መረጃዎች አመለከቱ፡፡

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የሰበታ ከተማ አስተዳደር ጀሞ ወረዳ አንድ ድንበር ላይ ይገኙ የነበሩና በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የተመዘገቡ አርባ አምስት ነባር የመሬት ባለይዞታዎችን ከመሬቴ ተነሱልኝ አላውቃችሁም  ብሏቸዋል፡፡

ነገሩ ያስደነገጣቸው ባለሐብቶች ይዞታቸው ለሚገኝበት የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለአቶ ፍጹም ካህሳይ አቤቱታቸውን ያቀረቡ ሲኾን ከአቤቱታ አቅራቢዎች ዉስጥ በኦሮሚያ ግብረኃይል መጋዘኖቻቸው የፈረሱባቸው ዜጎች እንደሚገኙበት ተመልክቷል፡፡

የክፍለ ከተማው ሥራ አስፈጻሚና አመራሮቻቸው በዚህ እንግዳ ክስተት ዙርያ አስቸኳይ ዝግ ስብሰባ ማካሄዳቸው የተሰማ ሲኾን በነገታው ባለይዞታዎቹን በመሰብሰብ ለአጭር ሰዓት አወያይተዋቸዋል፡፡ ችግሩ ፖለቲካዊ መልክ ስላለው በአጭር ጊዜ ሊቀረፍ የሚችል እንዳልሆነ ጠቆም የተደረጉት ባለጉዳዮቹ ችግሩን ለመፍታት  ከሰበታ አስተዳደር ጋር በተከታታይ መነጋገርን እንደሚጠይቅ ተብራርቶላቸዋል፡፡

ሥራ አስፈጻሚው አቶ ፍጹም ካህሳይ በበኩላቸው ጉዳዩን በግላቸው ይዘው ጊዜ ሳይሰጡ ከከንቲባው ጋር እንደሚነጋገሩበትና ባለይዞታዎቹ ለጊዜው በትዕግስት እንዲጠብቋቸው ተማጽነዋል ተብሏል፡፡ ነገሮች ካልተስተካከሉ ግን ሁሉም ባለይዞታዎች ተመጣጣኝ ቦታ በምትክነት እንደሚያገኙም ቃል ገብተውላቸዋል፡፡

ይዞታቸውን በይገባኛል ምክንያት በሰበታ ከተማ አስተዳደር የተቀሙ ባለይዞታዎች ዉስጥ ድርጅቶችና የሃይማኖት ተቋማት ይገኙበታል ፡፡ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለከፍተኛ ትምህርት ማዕከል ማሰሪያ በሚል የወሰደችው 15ሺ ካሬ ቦታም በሰበታ ከተማ አስተዳደር ከተወረሱት መሬቶች አንዱ ነው፡፡ ከድርጅቶቹና የሃይማኖት ተቋማት በተጨማሪ የአዲስ አበባ ሊዝ ጨረታን በማሸነፍ ቦታ የተረከቡ፣ ለግንባታ ጠጠርና አሸዋ በመድፋት ዝግጀት ሲያደርጉ የነበሩ፣ ለቁሳቁስ ማስቀመጫ መጋዘን የገነቡ፣ ለንግድና ኢንደስትሪ ቦታ የወሰዱ ባለሐብቶችና ቤት ገንቢ ነዋሪዎች ይገኙበታል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባልተለመደ ሁኔታ በአዲስ አበባ ዙርያ የሚገኙ የኦሮሚያ ልዩ ዞኖች በተለይም ባለፉት ሳምንታት በአዲስ አበባ የድንበር መሬት ላይ ተከታታይ የይገባኛል ጥያቄ በማንሳት ላይ ይገኛሉ፡፡ ጥያቄው ለምን በዚህ ጊዜ በተመሳሳይ ሁኔታ ተከሰተ ለሚለው አጥጋቢ ምላሽ ማግኘት ባይቻልም ከምሥራቃዊ አዲስ አበባ ዉጭ በሚገኙ በሁሉም የአዲስ አበባ አጎራባች የኦሮሚያ ልዩ ዞኖች ባለፉት ሦስት ሳምንታት ብቻ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ከሚያጎራብቷቸው ክፍለ ከተሞች ጋር በቁራሽ መሬት ዙርያ መለስተኛ እሰጥ አገባ ዉስጥ ገብተዋል፡፡

ዋዜማ ከአቃቂ ቃሊቲ፣ ከንፋስ ስልክና ከኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተሞች በሳምንታት ልዩነት የሰበሰበቻቸው መረጃዎች እንደሚያሳዩት ቡራዩ፣ ሱሉልታ፣ ገላን፣ ሰበታና ዓለም ገና በአጎራብቷቸው የከተማ ማዋቅሮች ላይ ጥያቄን አንስተዋል፡፡ ይህ የይገባኛል ጥያቄ እንዴት በተመሳሳይ ጊዜ ሊከሰት ቻለ? ነገሩ አጋጣሚ ነው ወይስ አይደለም? ለሚለው መላምት እርግጡን ምላሽ ማግኘት አዳጋች ኾኗል፡፡ 

ምናልባት ጉዳዩ በኦህዴድ ከፍተኛ አመራሮች ዘንድ ዉስጥ ዉስጡን ሲብሰለሰል የቆየና የኦሮሞ ብሔርተኝነትን ፈራ ተባ እያለም ቢኾን ማቀንቀን  በጀመረው የአቶ ለማ መገርሳ ካቢኔ የተቀነባበረ ሴራ ሊሆን እንደሚችል የሚገምቱ አልጠፉም፡፡ ይኸውም በቅርቡ ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ማግኘት በሚኖርባት ልዩ መብትና ጥቅም ላይ ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው ድርድር ላይ ተጨማሪ ጫና ለመፍጠር ታስቦ ሊሆን እንደሚችል የጠረጠሩም ጥቂት አይደሉም፡፡

የአዲስ አበባ ደቡባዊው ክፍል በተለይም አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ እንዲሁም ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ የሚገኘው የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ከሰበታና ከገላን የኦሮሚያ ልዩ ዞኖች ጋር የሚለየው ትክክለኛ ድንበር የት እንደሆነ አይታወቅም፡፡ በሰሜን አዲስ አበባም ተመሳሳይ ችግር ይስተዋላል፡፡ ከተማዋ የተሻለ ተፈጥሯዊ ድንበር አላት የሚባለው በምሥራቅ አቅጣጫ በጣፎ በኩል ከቦሌና ከየካ ክፍለ ከተሞች ጋር ያለው ሸለቆ ነው፡፡ በምዕራብ አቅጣጫ ኮልፌ ቀራንዮን የሚያዋስነው የኦሮሚያ ልዩ ዞንም ቢኾን የድንበር ጥያቄ ይነሳበታል፡፡ ቡራዩን ኮልፌ ቀራንዮ ዉዝግብ ተለይቷቸው አያውቅም፡፡

ከሰባት ዓመታት በፊት በምዕራብ አዲስ አበባ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ አንፎሜዳ በሚባል ሰፈር ተመሳሳይ የይገባኛል ጥያቄ በቡራዩና በኮልፌ ቀራንዮ  መሐል መነሳቱ ይታወሳል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎችም በየትኛው ክልል ዉስጥ እንደምንገኝ በግልጽ ይነገረን የሚል ጥያቄ ገፍተው ማንሳታቸውን ተከትሎ በአቶ ኩማ ደመቅሳና  በአቶ አባዱላ ገመዳ የሚመራ ልዩ ኮሚቴ በወርሃ ታኅሳስ 2002 ዓ. ም በአካባቢው በመገኘት ጉብኝት ማድረጉ ይታወሳል፡፡

ኾኖም በወቅቱ ይህ ነው የሚባል መፍትሄ ሳይሰጥ ቆይቷል፡፡

ከአካባቢው ነዋሪዎች መሐል ከፊሎቹ ፋይላቸው በኦሮሚያ ልዩ ዞን ሲገኝ ሌሎች ደግሞ ተጠሪነታቸው ለኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ነው፡፡ በርካታ የቤት ማኅበራት በከንቲባ ብርሃነ ደሬሳ ዘመን አንፎሜዳ አካባቢ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤቶችን ለመገንባት ቦታ ወስደው የነበረ ሲኾን ግንባታ ለመጀመር በዝግጅት ላይ ሳሉ ግን የቡራዩ ከተማ አስተዳደር በኦሮሚያ መሬት ላይ መገንባት አትችሉም በሚል ግንባታው እንዲቆም አድርጎ ነበር፡፡

በተመሳሳይ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ የሚተዳደረውና ሰፊ የቆዳ ስፋት እንዳለው የሚነገረው ኤርቶሞጆ የሚባለው ሰፈር የኦሮሚያ እንደኾነ ቢታመንም የአዲስ አበባ መስተዳደር ትልቁን የ20/80 የጋራ መኖርያ ቤት እውን ሊያደርግበት እየተዘጋጀ ያለ ቦታ ኾኖ ቆይቷል፡፡ ኾኖም ከሰሞኑ እንደተሰማው ከኾነ የኦሮሚያ ክልል የኤርቶሞጆ የቤቶች ፕሮጀክት ጉዳይ የአዲስ አበባ መስተዳደር በይደር እንዲያቆየው ጥያቄ ማቅረቡ ተሰምቷል፡፡

ሪፖርተር ጋዜጣ ከአንድ ወር በፊት በሠራው ዘገባ ከአዲስ አበባ መስተዳደር መሬት የወሰዱ 38 ባለሐብቶች የተረኩቡት ቦታ በሰበታና ገላን ከተሞች የይገባናል ጥያቄ ስለተነሳበት ለዓመታት ሲጉላሉ መቆየታቸውን ጠቅሶ የድንበር ጉዳይ እልባት እስኪያገኝ ድረስ የሁሉም ባለሐብቶች ፋይል ወደ ኦሮሚያ እንዲዛወር መወሰኑን አስነብቦ ነበር፡፡

በአዲስ አበባ መስተዳደር መዋቅር ዉስጥ በመካከለኛ የኃላፊነት ደረጃ ላይ በማገልገል ላይ የሚገኙ አንድ የመሬት ልማት ባለሞያ ለዋዜማ እንደተናገሩት የማስተርፕላኑ እስከዛሬ ያለመጽደቅ ዋንኛው ምክንያት ተመሳሳይ የድንበር ጉዳዮች አልባት ባለማግኘታቸው እንደሆነ ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ እንደርሳቸው ገለጻማስተርፕላኑ የኦሮሚያ ያደረጋቸውና በአዲስ አበባ የሚተዳደሩ፣ ማስተርፕላኑ የአዲስ አበባ አካል ያደረጋቸውን በኦሮሚያ የሚተዳደሩ ወረዳዎች በርካታ ናቸው፡፡ “ይህ እልባት ሳያገኝ ማስተርፕላኑ የሚፀድቅ አይመስለኝም” ብለዋል፡፡

አዲስ አበባ ቀድሞ ከነበራት 54ሺ ሄክታር የቆዳ ስፋት ይጸድቃል ተብሎ በሚጠበቀው 10ኛው ማስተርፕላን 2ሺህ ሄክታር ያህል ቀንሳ መገኘቷን መዘገባችን ይታወሳል፡፡