FILE

ዋዜማ ራዲዮ- ዛሬ( ሰኞ) ኢትዮጵያ የዕዳ መክፈያ ሽግሽግ እንዲደረግላት ያቀረበችው ጥያቄ ላይ የአበዳሪዎች ኮሚቴ ውሳኔ ያሳልፋል። ይህ ውሳኔ በቀጣይ ወራት ሀገሪቱ ለሚኖራት የኢኮኖሚ ቁመና እጅግ ወሳኝ መሆኑን ባለሙያዎች ያስረዳሉ። መንግስት የሚችለውን ያህል ርቀት ተጉዞ የዕዳ ሽግሽግ ለማግኘት ሙከራ አድርጓል። የሰሜኑ ጦርነትን በሰላም መቋጨት ከአበዳሪዎች ይሁንታ ለማግኘት ወሳኝ እርምጃ ሆኖ ብቅ ብሏል። ውጤቱ የሚወሰነው ግን ዛሬ በሚደረገው ስብሰባ ላይ ነው። ዋዜማ ጉዳዩን ተመልክታለች። አንብቡት

ኢትዮጵያ ለቡድን 20 ሀገራት የብድር አከፋፈሏ ላይ የጊዜ ማስተካከያ እንዲደረግላት ጥያቄ ካቀረበች ወዲህ የአበዳሪዎች ኮሚቴ ተቋቁሞ እስከዚህ አመት መጀመርያ ድረስ ሶስት ጊዜ ስብሰባዎችን አድርጎ ነበር። ሆኖም በሰሜኑ ጦርነት ሳቢያ ሂደቱ ተቋርጦ ቆይቷል።

ዛሬ(ሰኞ) አራተኛው በፈረንሳይና ቻይና የሚመራው የኢትዮጵያ የአበዳሪዎች ኮሚቴ ስብሰባ እንደሚካሄድ ይጠበቃል። አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ እና ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊ ለዋዜማ ራዲዮ እንደተናገሩት ከኢትዮጵያ አበዳሪዎች ስብሰባ ሀገሪቱ ያሉባትን ብድሮች የምትከፍልበትን ጊዜ ማራዘሙ እጅግ ወሳኙ ጉዳይ ነው።

“ሀገሪቱ አሁን ላይ በየዓመቱ የምትከፍለው ብድር ከሁለት ቢሊየን ዶላር ያላነሰ ነው ያሉት የስራ ሀላፊው “ኢትዮጵያ ከፊቷ መክፈል ያሉባት እዳዎች ከዚህም በላይ እየተቆለሉ እየመጡ ነው : በተለይም ከዓመት በኋላ መከፈል ካለበት የረጅም ጊዜ ዕዳ በተጨማሪ በዩሮ ቦንድ የተበደረችው አንድ ቢሊየን ዩሮም በአንድ ጊዜ እንዲከፈል ስለሚጠበቅ ጫናው ከዚህም ሊብስ ይችላል” ሲሉ ለዋዜማ ራዲዮ ገልጸዋል።

የአበዳሪዎቹ ስብሰባ ስኬት የሚገኝበት ከሆነም ከብድር ጊዜ ማራዘም ባለፈ ኢትዮጵያ ተጨማሪ ብድር የምታገኝበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላልም ብለውናል።

ከአበዳሪዎቹ ስብሰባ ስኬት እኩልም ሀገሪቱ ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት መስተካከልም እንዳለበት ያነሱት የዋዜማ ራዲዮ ምንጭ ከአሜሪካ ጋር ያለው ግንኙነት ሻክሮ መቆየቱ ከአለም ባንክ እና ከአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) መገኘት ያለበትን ብድር እንዳይገኝ እንቅፋት ሆኗል።

ኢትዮጵያ “ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ” የሚል ስያሜ የሰጠችውን መርሀ ግብር ስትጀምር ከሁለቱ ተቋማት በጥቅሉ  ስድስት ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚጠጋ ፣ የሌሎች ተቋማት ሲታከልበትም በድምሩ እስከ 10 ቢሊየን ዶላር የሚሆን ብድር ልታገኝ እንደምትችል ቃል ተገብቶላት ነበር። 

ሆኖም በሰሜኑ ጦርነትና ሌሎች ጉዳዮች ሳቢያ ከአሜሪካ ጋር ቅራኔ ውስጥ በመገባቱ እነዚህ ብድሮች ሳይገኙ ቀርተዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ዕዳ 29 ቢሊየን ዶላር እንደሚጠጋ የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል። ይህን ያክል መጠን ያለውን ዕዳ ለመክፈል እየተጣጣረች ያለውም ከውጭ የሚገኘው ብድር እና እርዳታ በቀነሰበትና የቱሪዝም ገቢም በኮሮና እና በጦርነት በተዳከመበት ወቅት ነው። 

ሁኔታውም የኢትዮጵያን የመጠባበቂያ የውጭ ምንዛሬ ክምችትን እንደጎዳው ታውቋል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ እቅድ የሶስት ወር የገቢ እቃዎችን የሚሸፍን የመጠባበቂያ የውጭ ምንዛሬ ክምችትን ማስጠበቅ ነበር። ሆኖም ያለው ክምችት ከእቅዱ በታች መሆኑን የማእከላዊ ባንኩ ምንጮቻችን ቁጥር ከመግለጽ ተቆጥበው ነግረውናል። 

ብሄራዊ ባንኩ ንግድ ባንኮች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሬ 70 በመቶውን እንዲሸጡለት አስገዳጅ ህግ ያወጣውም የውጭ ምንዛሬ ክምችቱን ለማስተካከል ነው። “ሆኖም በቂ የውጭ ምንዛሬ ክምችት እስኪገኝ እና ከሌሎች ምንጮች በቂ ምንዛሬ ማግኘት እስኪቻል ከንግድ ባንኮች የምንዛሬ ገቢ 70 በመቶውን መውሰዳችንን እንቀጥላለን” ብለውናል አንድ የብሄራዊ ባንክ ምንጫችን።

በሸቀጦች የወጪ ንግድ ላይ የተሻለ አፈጻጸም በዚህ አመት ታይቷል። በበጀት ዓመቱም ከወጪ ንግድ 4.12 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከሰሞኑ በማህበራዊ ድረገጹ ይፋ አድርጓል። የአለማቀፍ የሸቀጦች ዋጋ መወደድ በተለይም በቡና ላይ የታየው ከ25 በመቶ በላይ የዋጋ ጭማሬ አንዱ የገቢው መጨመር ምክንያት ነው። 

የወጪ ንግዱ እመርታ ለኢትዮጵያ የእዳ ጫና መቃለል እንደ አንድ መንገድ መወሰድ ቢኖርበትም የዛኑ ያክል ግን ለገቢ እቃዎችም የሚከፈለው ምንዛሬ ከፍ ማለቱ የንግድ ሚዛን መዛባቱን አሳድጎታል። 

የአመቱ የተጠቃለለ መረጃ ይፋ አይደረግ እንጂ በበጀት አመቱ ሁለተኛ ሩብ ማጠቃለያ ላይ እንኳ በሸቀጦች ገቢ እና ወጪ ንግድ ኢትዮጵያ የ3.4 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የንግድ ሚዛን ክፍተት አጋጥሟታል። በቅርቡም በአለም አቀፍ ደረጃ የሚታየው የሸቀጦች ዋጋ ንረት የንግድ ክፍተቱን እንደሚጨምረው ይጠበቃል።

ኤስ ኤንድ ፒ(S&P) የተባለው የሀገራት የዕዳ ከፋይነት ደረጃ አውጭ ለኢትዮጵያ መጋቢት ወር ላይ የ ሲሲሲ (CCC) ደረጃን ሰጥቷት እንደነበር የሚታወቅ ነው።ከዚህ ሁሉ አንጻርም ነው ለኢትዮጵያ የአበዳሪዎቿ ስብሰባ ውጤት ወሳኝ የሚሆነው። 

የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታው ኢዮብ ተካልኝ ከሰሞኑ በፓሪስ በተደረገ ስብሰባም ተገኝተው የተለያዩ አካላትን የማግባባት ስራን ሲያከናውኑ ነበር ። የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው ሚኒስትር ዲኤታው ኢዮብ ከቀናት በፊት በተሳተፉበት የፓሪስ ጉባኤ ከፓሪስ ክለብ ተባባሪ ሊቀመንበር ሚስተር ዊሊያም ሮስ ጋር ኢትዮጵያ ያቀረበችውን የብድር ሽግሽግ ጥያቄ መሰረት የአበዳሪ ሀገራት ኮሚቴ እስካሁን ስላከናወነው ተግባር ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ 

ሚስተር ዊሊያም ሮስ ኮሚቴው እስካሁን ሶስት ጊዜ ተገናኝቶ እንደመከረና አራተኛውን ስብሰባ በቅርቡ እንደሚያደርግና ከዚህ በፊት በተደረጉት ውይይቶች ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ መታየቱን ተናግረዋል። 

ከኢትዮጵያ ዩሮ ቦንድ ከገዙ ባለሀብቶች ጋር ሚኒስትር ዲኤታው መመካከራቸውንም ስምተናል። ሚኒስትር ዴኤታው ኢትዮጵያ አሁን ላይ የሚስተዋሉ የማክሮ ኢኮኖሚ ችግሮችን በመቅረፍ በቀጣይ ጊዜ ወደ ብድር ገበያ የመመለስ ፍላጎት እንዳላት ለባለሀብቹ ገልጸውላቸዋል።

የገንዘብ  ሚንስትር ዲኤታው ኢዮብ ተካልኝ ከአሜሪካ ትሬዥሪ ዲፓርትመንት ምክትል ኃላፊ ፓትሪሺያ ፖላርድ ጋርም በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ ተወያይተዋል።

የሰሜኑ ጦርነት ላይ የተጀመረው የሰላም መንገድ  በአበዳሪዎች በኩል ለሚኖረው ይሁንታ ዋና ጉዳይ ሆኖ ታይቷል። [ዋዜማ ራዲዮ]