ዋዜማ ራዲዮ- በአማራ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን፣ አጣዬ ከተማ ልዩ ቦታው ኤፌሶን አካባቢ ቅዳሜ ዕለት የታጠቁ ኃይሎች በከፈቱት ተኩስ በአካባቢው አለመረጋጋት ፈጥሮ ነበር፡፡

ይሁንና ችግሩን ለማብረድ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና የፌደራል መከላከያ በጥምረት ጣልቃ ገብተው ማረጋጋታቸውን የአጣዬ ከተማ ከንቲባ አቶ ጌታቸው በቀለ ለዋዜማ ተናግረዋል። አስከ እሁድ ረፋድ ድረስ የተኩስ ድምፅ መስማታቸውን ነዋሪዎች ነግረውናል።

አካባቢው በአማራ ክልል የኦሮሚያ ብሄረሰብ አስተዳደር ስር ያለ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ግጭቱ ከዚህ ቀደም ከተፈጠረው አለመግባባት ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ነዋሪዎች ይናገራሉ።

በአካባቢው ከዚህ ቀደም ከነበረው አለመረጋጋት ጋር ተያይይዞ የአማራ ክልል ልዩ ሀይል በቅርበት መኖሩን የተቃወሙ ታጣቂዎች ልዩ ሀይሉ “ከአካባቢው ይውጣልን” የሚል ተቃውሞ ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወሳል።

በግጭቱ ስለደረሰው ጉዳት የተገለፀ ነገር የለም።