Teddy Afro ዋዜማ ራዲዮ-ለሦስት ተከታታይ ጊዜያት ያህል ከተራዘመ በኋላ በመጪው ፋሲካ እንደሚለቀቅ በስፋት እየተነገረለት የሚገኘው የቴዲ አፍሮ አዲስ አልበም ለገበያ የሚቀርበው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እስካልተራዘመ ድረስ ብቻ መሆኑን ለድምጻዊው ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገለጹ፡፡ ቴዲ አገሪቱ ወደ ሙሉ መረጋጋት ሳትመለስ ሙዚቃውን የመልቀቅ ፍላጎቱ እምብዛምም ነው ተብሏል፡፡

ምንም እንኳ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በመጪው መጋቢት 28 6ኛ ወር ቢሞላውም አዋጁ በአንድ ሆነ በሌላ አጋጣሚ የሚራዘምበት እድል ካለ የአልበሙ መውጫ ጊዜም ሊራዘም እንደሚችል የድምጻዊው የቅርብ ሰዎች ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡

የቴዲ አዲስ አልበሙ ከተጠናቀቀ ዘለግ ያለ ጊዜን ቢያስቆጥርም አገር ዉስጥ ያለው ፖለቲካዊ ድባብና የሕዝብ ስሜት መልካም ሳይሆን በመቆየቱ ሙዚቃውን ለሕዝብ ለማቅረብ አለመሻቱን ወዳጆቹ ይናገራሉ፡፡ “ አገር በችግር ዉስጥ ኾና ሙዚቃዬን መልቀቅ ሕዝብን አለማክበር ነው የሚሆንብኝ” የሚለው ቴዲ ይህ ሥራው እንዲደመጥለት ባልተለመደ ሁኔታ ከፍተኛ ጉጉት አሳይቷል ተብሏል፡፡ “እስከ ዛሬ ከሠራኋቸው ሥራዎች ይህ ለኔ ልዩ ነው” በማለት በተደጋጋሚ እንደሚናገርም ዋዜማ ያነገረቻቸው ወዳጆቹ ይመሰክራሉ፡፡

አገራዊ አንድነትን አብዝተው በሚሰብኩና ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛነት ባጠቃቸው ስንኞች የተሞላው ይህ አዲሱ አልበም ይፋዊ ርዕሱ ጦቢያ ወይም ኢትዮጵያ ሊሆን እንደሚችልና መጠሪያው እስከአሁንም እንዳልተወሰነ ታውቋል፡፡ ኾኖም አዲስ ከሠራቸው 16 የሚኾኑ ሙዚቃዎች ኢትዮጵያ የተሰኘ ድንቅ ዜማ እንደሚገኝበትና ይህም የአልበሙ ርዕስ የመሆን እድሉ ከፍተኛ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ ወደ 24 የሚሆኑ ዜማዎች መሰራታቸውን እንደሚያውቅና ሆኖም ቴዲ በዚህ አልበሙ ምን ያህሉን ሊያካትት እንደሚችል መተንበያ አስቸጋሪ እንደሆነበት ይኸው ወዳጁ ይናገራል፡፡ ቴዲ በጉዳዩ ላይ ይፋ ያደረገው ነገር ባይኖርም ይህ ኢትዮጵያ የተሰኘው ሙዚቃ በመልዕክትም በዉበትም ገኖ የመውጣት እድሉ አጠያያቂ አይደለም ብሏል፡፡ ብዙዎቹ የቅርብ ወዳጆቹ እንደሚስማሙት ቴዲ አፍሮ ሙዚቃዎቹን ደጋግሞ የመከለስና አለቀ የተባለ ሥራውን አፍርሶ የመስራት፣ እንዲሁም በሥራው ያለመርካት ባሕሪ ይስተዋልበታል፡፡

ቴዲ አፍሮ ከዚህ ገናና እንደሚሆን ከሚጠበቀው ኢትዮጰያ ከሚለው ሙዚቃው ባሻገር ስለ ኤርታሌና ስለ ባሮ ወንዝ ማቀንቀኑ ተሰምቷል፡፡

በዚህ አልበሙ የቴዲን አነጋጋሪነትና የፈጠራ ሰው መሆኑን ዳግም ይመሰክርሉታል ተብለው ከሚጠበቁት ሙዚቃዎቹ ዉስጥ በዋናነት በሐዲስ ዓለማየሁ ዝነኛ ረዥም ልቦለድ ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› ላይ ተንተርሶ ያዜመው ሥራው ሊሆን እንደሚችል ሙዚቃውን ካቀናበሩለት ሰዎች ዋዜማ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡

ቴዲ አፍሮ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ኤርታሌ ለተሰኘው ሙዚቃው አጃቢ ተንቀሳቃሽ ምስል በማሰናዳት ላይ መጠመዱንና ብዙ ደክሞበታል የተባለውን አልበሙን ለሽያጭ በማቅረብ በኩል ደግሞ ባለቤቱ ወይዘሮ አምሰለሰት ሙጬና የሙዚቀኛው የረዥም ጊዜ አማካሪው አቶ ጌታቸው ማንጉዳይ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር እየተደራደሩ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ ኾኖም አልበሙ እስከ 10 ሚሊዮን ብር ሊያወጣ ይችላል ተብሎ ቅድመ ግምት ተሰጥቶታል፡፡

እነዚህ የዋዜማ ምንጮች አልበሙ ከ5 እስከ 8 ሚሊዮን ብር ተሸጧል ተብሎ በአገር ቤት ሚዲያዎች መዘገቡ ትክክለኛ መረጃ አይደለም ሲሉ መረጃዉን አጣጥለውታል፡፡ እስከአሁንም ድርድር እንጂ ሽያጭ አልተከናወነም ተብሏል፡፡

ቴዲ አፍሮ አቡጊዳ የተሰኘውን የበኩር አልበሙን በ1993 ለሕዝብ ካቀረበ በኋላ ፣ ጃ ያስተሰርያል አልበመሙን ከአራት ዓመት በኋላ በ (1997)፣ እንዲሁም ጥቁር ሰው የተሰኘ አልበሙን ከአምስት ዓመት በፊት በ2004 ዓ.ም ለሕዝብ አድርሷል፡፡

ከዚህ ዉጭ በርካታ የዉጭ አገር የኮንሰርት ጥያቄዎች በተደጋጋሚ የሚቀርቡለት ሲሆን በአንዳንዶቹ ላይ ካልሆነ እምብዛምም ከአገር ቤት መራቅ አይሻም፤ የኮንሰርት ሥራ ለማቅረብም ፍላጎቱ የተገደበ ነው፡፡ በተቃራኒው ለአገር ቤት ተመልካች ኮንሰርት ለማቅረብ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ይነገራል፡፡ ኾኖም የመንግሥት ሹማምንት ይህ እንዲሆን መልካም ፍቃድ ሳይሰጡ ቆይተዋል፡፡

የአገር ቤት ኮንሰርቱ እንዲከወን ካለመፍቀድም በላይ ድምጻዊው ለዉጭ ሥራ በሚጓዝበት ወቅት የደኅንነት ሰዎች እንግልትና ወከባ እንደሚያደርሱበት ይነገራል፡፡ ከስድስት ጊዜ በላይ ፖስፖርቱን በኢሜግሬሽን ሰዎች እንደተነጠቀና ጉዞዎቹ እንደተሰረዙበት፣ ይህ ለምን እንደሚሆን ሲጠይቅም በቂ መልስ እንደማይሰጠው የቅርብ ወዳጆቹ ይናገራሉ፡፡

“የደኅንነት ሰዎች የእርሱን ጉዞ በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ለማስተጓጎል ይፈልጋሉ፣ ምናልባት የልጁን ሞራል ለመንካት ፈልገው ሊሆን ይችላል” ይላል፣ የቅርብ ወዳጁ፡፡

ቴዲ በአሁኑ ሰዓት ለገጣፎ ካንትሪ ከለብ ሪልስቴት ግቢ ባለ አንድ ፎቅ ቤት ተከራይቶ የሚኖር ሲኾን በቀኑ ክፍለ ጊዜ እምብዛምም ከቤት የመውጣት ልምድ የለውም፡፡ ድምጻዊው አሁን በኪራይ ቤት ይሁን እንጂ በዚያው የለገጣፎ ካንትሪ ክለብ እያስገነባው የሚገኘውን ቪላውን በሚመጣው ዓመት መጨረሻ ይረከባል፡፡

ከአመታት በፊት ካንትሪ ክለብ ሪልስቴት ሥራ ሲጀምር ሙዚቀኛው ቴዲ ማስታወቂያ እንዲሠራላቸውና በምትኩ አንድ ቪላ ቤት በነጻ ገንብተው እንደሚሰጡት የሥራ ግብዣ አቅርበውለት እንደነበረና ቴዲ ሐሳቡን ሳይቀበል እንደቀረ፣ ከዚያ ይልቅ በራሱ ወጪ በዚያው ግቢ ቤት ማሠራት እንደመረጠ የቅርብ ወዳጆቹ ያስታውሳሉ፡፡

በሚዲያ ላይ በሚሰጣቸው አስተያየቶች ቁጥብነት የሚታይበት ቴዲ አፍሮ የሙዚቃ ባለሞያዎችም እርሱን ለመተቸት ድፍረቱ እንደሌላቸው ይነገራል፡፡ ይህም የሚሆነው በርሱ ላይ አሉታዊ አስተያየት መሰንዘር በአድናቂዎቹ ከፍተኛ ዉግዘትን እንደሚያስከትል ከመረዳት የሚመነጭ ነው፡፡

የቴዲ አፍሮ ልዩ ክህሎትና ድክመት ምን እንደሆነ በአንድ ወቅት በፎርቹን ጋዜጣ የተጠየቀው የሙዚቃ ተመራማሪው ሰርጸ ፍሬስብሀት ቴዲ አሰልቺ ሊሆን ተቃርቦ የነበረውን የኢትዮጵያ የፖፕ ሙዚቃ ዘዬ አዲስ ፎርም ፈጥሮ ነፍስ ዘርቶበታል፡፡ ኾኖም ድምጻዊው በተለያየ ሬንጅ መዝፈን የሚችልና በርካታ የድምፅ ቴክኒኮች አፈራርቆ መጠቀም የሚችል አይደለም፡፡ ጠንካራ ግጥሞቹንና ሳቢ ዜማውን የሚሰፋው ለራሱ በሚመቸው ምጣኔ መሆኑ የቴክኒክ ድክመቱ ጎልቶ እንዳይወጣ አስችሎታል በሚል አስተያየቱን ሰጥቶ ነበር፡፡

የቴዲ በዓለማቀፍ ሙዚቃ ዉስጥ ሰብሮ ለምን እስከዛሬ ሊገባ እንዳልቻለ ለጋዜጣው ያብራራው አቶ ሰርፀፍሬ ስብሐት “ምዕራቡ የራስህ የሆነ ልዩ ቀለም፣ ማንነትና ቱባ (ኦሪጅናል) የሙዚቃ ባህል ይዘህ ስትመጣ ያከብርሀል፡፡ የእነርሱ የሚመስል የዜማ ቅርጽና ፎርም ይዘህ ልባቸውን ማሸነፍ የሚሞከር አይደለም፡፡ የቴዲ ዜማ የሚመተር፣ የሚገመት ነው፡፡ አሁን ዓለም የሚፈለገው የማይመተር፣ የማይገመትና እጅግ ወጣ ያለ የዜማ ቅርጽ (Irregular shape) ያለውን ነገር ነው፡፡ ቴዲ የዓለም አቀፍ ገበያ ዉስጥ የመግባት እድሉ ጠባብ የሆነውም ለዚሁ ይመስለኛል” ይላል፡፡

ሰርጸፍሬ ስብሐት በተጨማሪም በወቅቱ በሰጠው አስተያየት ቴዲ ከእስር ሲፈታ ወደ ድምጽ ትምህርት ቤት ይገባል የሚል ተስፋ እንደነበረው ለጋዜጣው ተናግሮ ነበር፡፡ “ትምህርት ቤት የመግባት ድፍረቱ ሊኖረው ይገባል፤ ታሪክ ፍልስፍናና ቋንቋ ኮርሶችን ቢወስድ አቅሙን ይበልጥ ማጎልበት ይችላል ብዬ አስባለሁ” ሲል ሐሳቡን አጋርቶ ነበር፡፡