FILE

ዋዜማ ራዲዮ- የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) በደቡብ አፍሪካዊቷ አገር ማላዊ በሚገኝ አንድ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ዜጎችን ጨምሮ የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ የሆኑ አፍሪካዊያን መኖራቸውን እንደደረሰበት አስታውቋል።

አሁን ዛለካ በተሰኘው የማላዊ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የተደረሰበት የሕገወጥ ሰዎች ዝውውር መረብ እና የሰለባዎች ብዛት፣ ቀደም ሲል ከተገመተው በላይ መጠነ ሰፊ መሆኑ እንደታወቀ የተመድ የአደንዛዥ ዕጽ እና ወንጀል መከላከያ ቢሮተናግሯል። በመጠለያ ውስጥ በሳምንት አንድ ጊዜ ዕሁድ ላይ ሕጻናት ለአስገዳጅ ጉልበት ብዝበዛ እና ለወሲብ ንግድ ገበያ ላይ እንደሚሸጡ ቢሮው ማረጋገጥ ችሏል።

የተመድ ቢሮ እስከ ስደተኞች መጠለያ ድረስ የተዘረጉትን የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መረቦች ለመበጣጠስ፣ የወንጀሉን ሰለባዎች ለመታደግ እና ወንጀለኞችን ለሕግ ለማቅረብ የሚያስችሉ ርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሆነ ገልጧል። በመጠለያው ውስጥ በተደረገ ክትትል የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ የሆኑ 90 ስደተኞችችን እስካሁን መታደግ የተቻለ ሲሆን፣ አብዛኞቹ ሰለባዎች ከ18 እስከ 30 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ወንዶች እንደሆኑ ተረጋግጧል። ቢሮው ከታደጋቸው ሰለባዎች መካከል፣ እድሜያቸው ከ12 እስከ 24 የሚሆኑ የኢትዮጵያ፣ ቡሩንዲ እና ዲሞክራሲያዊት ኮንጎ ዜጎች የሆኑ ስደተኛ ሴቶች እና ልጃገረዶችም ይገኙበታል ተብሏል።

በመጠለያው ውስጥ የተንሰራፋውን ሕገወጥ የሰዎች ንግድ ሰንሰለት እና የሰለባዎቹን ማንነት ተከታትለው የደረሱበት፣ የተመድ የአደንዛዥ ዕጽ እና ወንጀል መከላከል ቢሮ ቀደም ሲል በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ክትትል ዙሪያ ያሰለጠናቸው የስደተኞች መጠለያ ሠራተኞችና ሕግ አስከባሪዎች ናቸው።

ካለፈው ታኅሳስ ወዲህ ባለው የተመድ መረጃ፣ ማላዊ ከ52 ሺህ 600 በላይ ስደተኞችን ያስጠለለች ሲሆን፣ ዛለካ በተሰኘው የስደተኞች መጠለያ በብዛት የሚገቡት የዲሞክራሲያዊት ኮንጎ፣ ቡሩንዲ እና ሩዋንዳ ስደተኞች ናቸው። በመጠለያው ውስጥ ከሚገኙት የተለያዩ አገር ዜጎች መካከል፣ 21 ሺዎቹ የስደተኝነት እና 40 ሺህ ያህሉ ደሞ የጥገኝነት ጠያቂነት ማረጋገጫ የተሰጣቸው ናቸው።

በሕገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ወደ ደቡብ አፍሪካ በሕገወጥ መንገድ መሻገር የሚፈልጉ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞች፣ ማላዊ ላይ በጸጥታ ኃይሎች ተይዘው በእስር ቤቶች እንደሚማቅቁ በተደጋጋሚ ሲዘገብ ቆይቷል። ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ሕገወጥ ፍልሰተኞች ደሞ፣ በሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች አማካኝነት በስደተኛ መጠለያ ሽፋን የአስገዳጅ ጉልበት ብዝበዛ፣ ባርነት እና የወሲብ ንግድ ሰለባ እንደሚሆኑ የአሁኑ የተመድ ክትትል ግኝት ማሳያ ነው። [ዋዜማ ራዲዮ]