Photo ESAT
Photo ESAT

ዋዜማ ራዲዮ- ዜጎችን በብሄር ማንነታቸው ለይቶ ከቀያቸው ማፈናቀል ከብሄር ተኮሩ ፌደራላዊ ሥርዓት ዕድሜ ጋር እኩያ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በታይቶ በማይታወቅ መጠን የታየው ግን በቅርቡ በሱማሌ ክልል የሚኖሩ ከ800 ሺህ በላይ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች የተፈናቀሉ ጊዜ ነው ማለት ይቻላል፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አሕመድ ሥልጣን ይዘው በሀገሪቱ ተስፋ የሚያጭር ሁኔታ በታየበት ሰዓት ማፈናቀሉ መቀጠሉ ብቻ ሳይሆን እሳቸው የሚመሩት ፌደራል መንግስት ዝምታን መምረጡ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡

ማንነትን መሠረት ያደረገው ዜጎችን ከቀያቸው የማፈናቀል ድርጊት ብዙ ትኩረት የተነፈጋቸውን ጥያቄዎች ያዘለ ነው፡፡ ለዜጎች መፈናቀል ሰበብ እየሆኑ ያሉት ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኦኮኖሚያዊ እና ጸጥታ-ነከ ምክንያቶች ምን ይሆኑ? ድርጊቱ እንዴት መጠነ ሰፊ እና ተከታታይ ሊሆን ቻለ? ወንጀሉ ተቋማዊ እና የራሱን ፖለቲካ ኢኮኖሚ የፈጠረ ሀገራዊ ክስተት እየሆነ ይሆን? ከዚህ ወንጀል እነማን ምን ዐይነት ትርፍ ያገኛሉ? ለመሆኑ ሀገሪቱ መፈናቀልን ለማስቀረት የሚረዱ ሕጋዊ ማዕቀፎች አሏትን? ዜጎችስ “መጤ” እና “ባይተዋር” የሚባሉት በምን አግባብ ነው? የሚሉ በርካታ አንገብጋቢ ጥያቄዎችን ማንሳት ተገቢ ይሆናል፡፡ ችግሩ ሁሉንም ጥያቄዎች ከሞላ ጎደል ለመመርመር እንዳይቻል እንቅፋት የሆኑ ውስንነቶች መኖራቸው ነው፡፡ [ተጨማሪ የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ አልያም ንባብዎን ይቀጥሉ]

አማሮቹን እያፈናቀለ ያለው ማነው?

ዜጎችን በብሄር ማንነታቸው ለይቶ ከቀያቸው ማፈናቀል በየትኛውም ሀገር የከፋ ወንጀል ሲሆን በዐለም ዐቀፉ ፍርድ ቤትም በእንግሊዝኛው “ethnic cleansing” (ዘር ማጥራት) ተብሎ የተሰየመ ከባድ ዐለም ዐቀፍ ወንጀል ነው፡፡ በዚህ ወንጀል ከምስራቅ፣ ምዕራብ እና መካከለኛው አፍሪካ እስከ አውሮፓ ሀገራት ያሉ መሪዎች እና የጦር አበጋዞች ዋጋ በዐለም ዐቀፉ ፍርድ ቤት ተከሰው ፍርዳቸውን አግኝተውበታል፡፡

በሀገራችን በተለይ የአማራ ብሄር ተፈናቃዮችን ቁጥር፣ የአፈናቃዮቹን ማንነት እና የማፈናቀሉ ሂደት ምን እንደሚመስል በገለልተኛ አካል የተጠናቀረ መረጃ አለመገኘቱ ክስተቱ እዚያ ደረጃ ላይ መድረስ አለመድረሱን ለማወቅ እንዳይቻል ያደርገዋል፡፡ ማንነትን መሰረት ያደረገ መፈናቀል ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን በጥናት ማረጋገጡን የፌደራሉ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሰሞኑን አስታውቋል፡፡ ለዐመታት ሲከሰት የኖረው ይሄው ወንጀል ድርብርብ ወንል እየሆነ ነው፡፡ ከቀየ በጅምላ ከማፈናቀል እና ማባረር ጀምሮ እስከ ንብረት ዘረፋ፣ ቤት ንብረትን ማቃጠል እና ግድያ ድረስ የሚፈጸምበት ድርጊት…

የብሄር ማንነትን መሰረት ያደረገው መፈናቀል ለሃያ ዐመታት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን በዋናነት በተደጋጋሚ ተጠቂ የሆኑት በኦሮሚያ፣ ቤንሻንጉል እና ደቡብ ክልሎች የሚኖሩ የአማራ ብሄር (አማርኛ ተናጋሪ) የሕብረተሰብ ክፍሎች ነበሩ፡፡ ላለፉት ሁለት ወራት የሀገሪቱ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ጋብ ባለበት ሰዓትም የአማራ ብሄር ተወላጆችን ከቀያቸው የማፈናቀሉ ሕገ ወጥ ድርጊት እንደገና አገርሽቶበታል፡፡

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር መሪዎች አቶ ሌንጮ ለታ እና ዶክተር ዲማ ነግዎ ወደ አዲሳባ በገቡበት ወቅት ከኦሮሚያ ክልል ጭምር የአማርኛ ተናጋሪዎች መፈናቀላቸውም ግጥምጥሞሹን ምጸታዊ ማድረጉ አልቀረም፡፡

ምክንያቱም በሽግግሩ መንግስት ዘመን የአማራ ብሄር ተወላጆች እስካሁንም ደረስ ተጠያቂው አካል ተጣርቶ ባልታወቀበት ሁኔታ በተለይ ከአርሲ አካባቢ አሰቃቂ ጅምላ ግድያ እና መፈናቀል የደረሰባቸው ኦነግ “ክልል አራት” ይባል የነበረውን የአሁኑን ኦሮሚያ ክልል በስፋት ይቆጣጠር በነበረበት ወቅት ነበርና፡፡ ያ እኩይ ድርጊትም በሽግግር መንግስቱ ውክልና ላልነበረው አማራ ብሄር መላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአሕድ) የተባለ ተቃዋሚ ድርጅት እንዲመሰረት እርሾ ሆኖ ያገለገለ ሲሆን ካለፉት ሁለት ዐመታት ወዲህ ደሞ ለአማራ ሕዝብ ብሄርተኝነት ወደ አንድ ደረጃ ከፍ እንዲል የራሱን አስተዋጽዖ እያደረገ እንደሆነ ከእየአቅጣጫው ይሰማል፡፡

በቤንሻንጉል ጉሙዝ የሰው ሕይወት የጠፋበት እና ንብረት የወደመበት ማፈናቀል በቅርቡ ደጋሚ የተከሰተ ሲሆን ከ500 በላይ የሚሆኑ የአማራ ብሄር ተወላጅ የሆኑ ተፈናቃዮችም በባህር ዳር ከተማ መከተማቸውን መገናኛ ብዙሃን ሲዘግቡት ሰንብተዋል፡፡ የፌደራሉ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አሁን ባለው አወቃቀሩ ከፖለቲካ ገለልተኛ የሆነ ማጣራት ያደርጋል ብለው የሚያምኑ ወገኖች እምብዛም ቢሆኑም ሁኔታውን ለማጣራት ቡድኑን ወደ ባህር ዳር እና ቤንሻንጉል እንደላከ ስለገለጠ ውጤቱን መጠበቅ ግድ ይላል፡፡

የማፈናቀሉ መግፍዔዎች

ለዜጎች መፈናቀል መጋቢ የሚሆኑት ፖለቲካዊ፣ ኦኮኖሚያዊ እና ጸጥታ-ነከ ነገሮች ምንድን ናቸው? ፌደራላዊ ሥርዓቱ የተዋቀረበት ገዥ መርህ ብሄር እና ቋንቋን መሠረት ያደረገ ይሁን እንጅ ሁሉም ክልሎች ግን የተለያዩ ብሄሮች እና ሕዝቦች ተሰባጥረው የሚኖሩባቸው ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ሕገ መንግስቱ የዜጎችን በየትኛውም ስፍራ ተንቀሳቅሶ የመኖር መብት የፈቀደ በመሆኑ ዜጎችን በማነነታቸው ለይቶ እንደ ባይተዋር የመቁጠር እና “አካባቢያችን ለቃችሁ ውጡልን” ለማለት የሚያበቃ አንዳችም ሕጋዊ ክፍተት የለም፡፡

ሆኖም ግን በተቃራኒው ሕገ መንግስቱ የግዛት፣ ስልጣን እና ሃብት ባለቤትነትን ለሀገሪቱ ዜጎች እንደ ገለሰብ ሳይሆን ለብሄረሰቦች እንደ ቡድን ስለሰጣቸው ባንድ ግዛት ካለው ገናና ብሄረሰብ ውጭ ያሉ ወገኖችን ለማፈናቀል የፖለቲካ ሽፋን ሆኖ እያገለገለ ነው የሚገኘው፡፡ እናም ዋናው ገፊ ምክንያት ብሄር ተኮሩ ፖለቲካ መሆኑ ዐሊ የሚባል አይደለም፡፡

በተለይ ላለፉት 27 ዐመታት ኢሕአዴግ ሲሰብከው የኖረው “አማራ ብሄር በታሪክ ሌሎችን ጨቋኝ እና ገዥ መደብ ነበር” የሚለው ትርክት በበታች ካድሬዎች እና አስተዳደር ሃላፊዎች ዘንድ የተዛባ አመለካከት መፍጠሩን መገንዘብ ይቻላል፡፡ መንግሥትም ቢሆን ዜጎች የሚፈናቀሉት የበታች አስተዳደሮች የብሄር ፌደራሊዝሙን ባግባቡ ካለመረዳታቸው እና ከአመለካከት ችግር የሚመነጭ ነው የሚል ምክንያት ደጋግሞ ሲያቀርብ ይሰማል፡፡

ሌላው ተያያዥ ገፊ ምክንያት በሀገሪቱ ብሄራዊ ማንነት መደብዘዙ ነው ሊባል ይችላል፡፡ ከከፍተኛ ትምህርት ጀምሮ እስከ ተራው ዜጋ ድረስ የብሄረሰብ እና ክልላዊ ዜግነት ከብሄራዊ ማንነትን እየደፈቀ የጋራ እሴቶችንና ምልክቶችን እያኮሰሰ መሄዱ ተደጋግሞ ተነግሯል፡፡ መንግስት ደሞ አንድ የጋራ ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መመስረት ስራ ላይ ዳተኛ ሆኖ ነው የኖረው፡፡ እናም የብሄረሰቦች ሉዓላዊነት ከሕግ በላይ መሆኑ ዜጎች በሚኖሩበት ክልል “መጤ” የሚባሉት በምን መስፈርት ነው? የሚለው ጥያቄ በበቂ ሁኔታ መወያያ እንዳይሆን እንቅፋት ፈጥሯል ማለት ይቻላል፡፡

በቤንሻንጉል፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች አብዛኛዎቹ “መጤ” የሚባሉት አማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ዜጎች ግን ባለፉት ሁለት ሥርዓቶች ሀገሪቱ አሃዳዊ ቅርጽ እያላት ለሥራ እና በመንግስት-መር ሠፈራ ምክንያት የሄዱ እንደሆኑ በጥናት የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡ የኢሕአዴግ ሠፈራ ፕሮግራም እንደሆነ ክልል ተሻጋሪ ስላልነበር ለዚህ ክስተት አስተዋጽኦ አላደረገም ማለት ይቻላል፡፡ ከዚያ ውጭ በ1990ዎቹ መጨረሻ ግድም በአማራ ክልል፣ ምስራቅ ጎጃም አካባቢ የገጠር መሬት ሽግሽግ መካሄዱን ተከትሎ በርከት ያሉ ገበሬዎች ወደ ምስራቅ ወለጋ ሂደው እነደሰፈሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከዚህ ውጭ ያለው እንግዲህ በተናጥል የግለሰቦች ዝውውር ነው የሚሆነው፡፡

ከፖለቲካው ሌላ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ከደቡብ ክልል የሚፈናቀሉ ዜጎች የነባሩን ኀብረተሰብ ደን በመጨፍጨፍ ስነ ምህዳር ስላራቆቱ ነው በማለት ፓርላማ ላይ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡ እንዲህ ዐይነት በመሪ ደረጃ የሚነገሩ ንግግሮች ደሞ በክልል አስተዳደር እርከኖች ስር መስደዳቸው አይቀሬ መሆኑን መገመት አያዳግትም፡፡ መፍትሄ ብለው ያቀረቡትም በተደራጀ እና ስርዓት ባለው መንገድ መስፈርን ነው፡፡ አስፋሪ ከልሎች ግን በተደራጀ መንገድ የሚካሄድን ሰፈራ ምን ያህል ይፈልጉታል? የሚለው በራሱ አጠራጣሪ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ መፈናቀሉ ባብዛኛው የሚታየው ሰፋፊ ለም መሬቶች ባሉባቸው አካባቢዎች በመሆኑ የመሬት እና የሌሎች ሃብቶች ቅርምት የመነሳቱም ነገር እምብዛም ስለሆነ ለመፈናቀል በር ሊከፍት አይችልም፡፡

የማፈናቀሉ ተዋናዮች

ማንነትን መሰረት ያደረገው መፈናቀል ከነባር ብሄረሰቦች ጋር በባህል፣ እምነት ወይም በፖለቲካ አመለካከት ሳቢያ በሚፈጠር ግጭት ሳቢያ መሆኑን የሚጠቁም ሁነኛ መረጃም የለም ማለት ይቻላል፡፡ ከአማራ ብሄር ተፈናቃዮች በብዛት የሚሰማው ከአካባበው ሕብረተሰብ ጋር በደጉም ሆነ በክፉ ጊዜ ተሳስበው፣ ተጋብተው እና ተዋልደው እንደሚኖሩ፣ ይልቁንስ ሰላም የሚነሷቸው በበታች የመንግስት መዋቅር ያሉ አካላት እንደሆኑ ነው፡፡

ዜጎችን በማፈናቀሉ ሂደት ተዋናይ በሆኑ የአስተዳደር እና ጸጥታ አካላት እንዲሁም ተራ ግለሰቦች በሕግ ተጠያቂ አለመሆናቸውም አንዱ ድርጊቱ ተስፋፍቶ እንዲቀጥል አበረታች ሁኔታ የፈጠረ ይመስላል፡፡ በተለይ ጸጥታ ሃይሎች አጥፊዎችን ለፍርድ የማቅረብ ግዴታቸውን ሲወጡ አይታይም፡፡ እንዲያውም መሊሻዎች እና በወረዳ ደረጃ ያሉ የክልል ፖሊሶች የማፈናቀሉ ሽፋን ሰጭዎች እንደሚሆኑ ለእውነታ የቀረበ ጥርጣሬ አለ፡፡ እናም የሕግ የበላይነት እና ተጠያቂነት መጥፋቱ ፖለቲከኞች “ነገም ብንፈጽመው ምንም አንሆንም” የሚል አመለካከት እንዲያዳብሩ ያደረገ ይመስላል፡፡ ላለፉት በርካታ ዐመታት የአማራ ብሄር ተወላጆች ከየክልሉ ቢፈናቀሉም ባለፈው ዐመት ብቻ ነው የደቡብ ክልል መንግስት በጉራፈርዳ ወረዳ ወንጀሉን የፈጸሙ የበታች የአስተዳደር እና ጸጥታ አካላትን ለሕግ ያቀረበው፡፡

ባጠቃላይ ችግሩ ዞሮ ዞሮ ከአስተዳደራዊ አካላት ጋር የሚቆራኝ ፖለቲካዊ ነው የሆነው፡፡ ድርጊቱ ፖለቲካዊ እና አስተዳደራዊ ድጋፍ ካላገኘ እንዴት መጠነ ሰፊ እና ተከታታይ ሊሆን ቻለ? የሚለውን ጥያቄ ብዙ ወገኖች የሚያነሱትም ለዚህ ነው፡፡ በርግጥም ድርጊቱ ቀስበቀስ ተቋማዊ የሆነ፣ እንዲሁም ስር የሰደደ የፖለቲካ ኢኮኖሚ የፈጠረ ሀገራዊ ክስተት እንዳይሆን ስጋት አለ፡፡

በርግጥ የማፈናቀልን ፖለቲካ ኢኮኖሚ በቅጡ ለማወቅ ቢያንስ ከዜጎች ጅምላ መፈናቀል እነማን ይጠቀማሉ? የሚለውን ማወቅ ይጠይቃል፡፡ ምንም እንኳ በመረጃ እጥረት ሳቢያ ሁሉንም ስውር እና ግልጽ ተወናዮች መለየት ቢያስቸግርም ጠባብ ብሄረተኛ ፖለቲከኞች ግን ግንባር ቀደም ተጠቃሚዎች መሆናቸው የአደባባይ ሚስጢር ነው፡፡ ሌላው ተያያዥ ጥቅም በማፈናቀሉ ተወናይ የሆኑ ወገኖች ከተፈናቃዮች ንብረት ተጠቃሚዎች እንዲሆኑም ያስችላቸዋል፡፡

የገናናው ብሄረሰብ ገዥዎች ማንነትን ማዕከል ያደረገው መፈናቀል ልዩ አስተዳደራዊ እርከኖችን ላለመዘርጋት ይጠቅማቸዋል፡፡ ገናና ብሄረሰብ ባለበት ክልል ወይም የበታች መዋቅር የሚኖሩ የአናሳ ብሄር ተወላጆች እንደ ብሄረሰብ የሚወክላቸው ፖለቲካ ድርጅት ስለሌላቸው በምርጫ ተወዳድረው የመመረጥም ሆነ በበታች አስተዳደራዊ እርክኖች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብታቸውን ለማስከበር አይችሉም፡፡ ለዚህም በየክልሉ በቁጥር አናሳ የሆኑ የሌላ ብሄር ተወላጆችን መብት የሚያስከብሩ ሕጋዊ እና አስተዳደራዊ ማዕቀፎች ሲዘረጉ የማይታዩት፡፡ ይሄ የፖለቲካ ፍቃደኝነት ማጣትም ዜጎችን አንደኛ እና ሁለተኘ ደረጃ ዜጎች እንዲሆኑ አድርጓል ማለት ይቻላል፡፡

በዚህ ረገድ አማራ ክልል ብቻ ነው እንደ ኦሮሚያ ልዩ ዞን፣ አገዋዊ ልዩ ዞን እና ዋግ ኽምራ ልዩ ዞን የመሳሰሉ ልዩ አስተዳደራዊ መዋቅሮችን በማቋቋም ሁነኛ ሕጋዊ እና አስተዳደራዊ ምላሽ የሰጠው፡፡ እናም በዚህ መስፈርት ሲታይ የደቡቡ ጉራፈርዳ ወረዳ አማርኛ ተናጋሪዎች ሊፈናቀሉ ይቅርና ለዚሁ መብት ሊበቁ ይገባቸው እንደነበር ነው አካባቢውን ያጠኑ ባለሙያዎች የሚገልጹት፡፡

የክልል መንግስታት ተፈናቃዮች አካባቢያቸውን ከለቀቁ በኋላ “ወደቀያቸው እንዲመለሱ ሁኔታዎችን አመቻችተናል” የሚል የይስሙላ የሚመስል ምላሽ ሲሰጡ መስማት መልሶ ማቋቋም ራሱ ምን ያህል ፖለቲካዊ ውጥንቅጥ እንዳለው ያሳየናል፡፡ ይሄ የሚነገረው እንግዲህ በአጥፊዎች ላይ ርምጃ ሳይወሰድ እና አስተማማኝ የደኅንነት ዋስትና ሳይገኝ ነው፡፡ በርግጥም የደኅንነት ስጋት ያለበት ሰው ወደመጣህበት ተመለስ መባሉ በየትኛውም መስፈርት ተቀባይነት ያለው ነገር አይደለም፡፡ ችግሩ ከመደጋገሙ አንጻር ከባድ ወንጀል መሆኑ እየተረሳ “መፈናቀላቸው ተገቢነት የለውም” በሚል ለስላሳ መግለጫ ሲተካ እየታየ ነው፡፡ የተፈናቃዮች ካሳ የመጠየቅ መብትማ ቅንጦት የሆነ ነው የሚመስለው፡፡

መፍትሄ ፍለጋ

ለመሆኑ ሀገሪቱ ብሄር ማንነትን የለዩ መፈናቀሎችን ለማስቀረት የሚረዱ ሕጋዊ ማዕቀፎች አሏት ወይ? ቢባል ቀደም ሲል እንዳነሳነው ዋናው ሕጋዊ ማዕቀፍ የዜጎችን ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ፣ ተንቀሳቅሶ ሃብት የማፍራት እና የመኖር መብት ያስጠበቀው ሕገ መንግስት ሆኖ ነው የምናገኘው፡፡ ይህኑንም መሰረት በማድረግ በረዥም ጊዜ አንድ ወጥ የፖለቲካ ማህበረሰብ የመመስረት እቅድ ይዞ ነበር፡፡ ሕገ መንግስቱ ግን በብሄር ማንነት መፈናቀል ሳቢያ ከመሰረቱ እየተሸረሸረ መሆኑን የፌደራሉ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሳይቀር አምኗል፡፡

በተቋማት ረገድም ችግሩን በመታገል ረገድ ቀዳሚ መሆን ያለባቸው ፌደሬሽን ምክር ቤት፣ ሕዝብ ተወካዮች ምከር ቤት፣ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የክልል መንግስታት እና ሕግ አውጭ ምክር ቤቶቻቸው መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ቸግሩ ግን አሁንም የመንግስት አንገብጋቢ እና አጣዳፊ ሀገራዊ ችግር ሆኖ ብቅ አላለም፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትርም ትኩረት የሰጡት አይመስልም፡፡ ባጠቃላይ ከድርጊቱ አሳሳቢነት አንጻር የክልል መንግስታት መፋዘዝ ከክልል አስተዳደሮች እና የበታች አስተዳደር አመራሮች የገዘፈ ስውር እጅ ያለ አስመስሎታል፡፡ [ተጨማሪ የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ ]

https://youtu.be/_JuY6tGXtjM