Siraj Fegessa, Minster of Defense
Siraj Fegessa, Minster of Defense

ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ  ብሄራዊ የፀጥታና ደህንነት ምክር ቤት በተሸኘው ሳምንት መጨረሻ በደረገው ስብሰባ የሀገሪቱ የፀጥታ ሁኔታ መሻሻል ባለማሳየቱ መንግስት ፖለቲካዊ መፍትሄ ጭምር እንዲፈልግ ከፀጥታ አካላት መጠየቁ ተሰማ።

ጠቅላይ ሚንስትር ሀይለማርያም ደሳለኝና የመከላከያ ሚንስትሩ ሲራጅ ፈጌሳ በመሩት በዚህ ስብሰባ ከፌደራልና ክልል ፖሊስ፣ ከመከላከያ ስራዊት፣ ከልዩ ሀይልና ከደህንነት ክፍሎች ሪፖርቶች የቀረቡ ሲሆን በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ያለው ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑ ተብራርቷል።

የፀጥታ ሁኔታውን ለማሻሻል ይረዳሉ የተባሉ ዕቅዶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የመንግስት መዋቅር የማፍረስ፣ ብሄርን እየመረጡ ማጥቃት፣ መንገዶች መዝጋት በመንግስት ተቋማት ላይ ጥቃት ማድረስ የተለመዱ ክስተቶች ሆነዋል። ዋና ዋና መንገዶች እንዳይዘጉ ለማድረግ በምናደርገው እንቅስቃሴ የበርካታ አባላት ህይወት አደጋ ላይ ወድቋል ይህም የሰራዊቱንና የፖሊስ አባላትን ስነልቦና የጎዳ በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል ብለዋል ተሰብሳቢዎቹ።

በኦሮሚያ በክልሉ ፖሊስ አባላትና በመከላከያ ሰራዊት መካከል ተደጋጋሚ ግጭት ተከስቶ በርካቶች የተገደሉ ሲሆን በጋራ መስራት የማይቻልበት ደረጃ ደርሰናል ብለዋል ሪፖርት አቅራቢዎቹ።
የሰው ህይወት ሳይጠፋ ተቃውሞ ለመበተን ስንሞክር ከሰልፈኞች አልያም ካልታወቁ ታጣቂዎች ይተኮስብናል፣ ለዚህ መልስ ስንሰጥ ደግሞ ከህዝቡ ጋር እንቃቃራለን ሲሉ ይናገራሉ አንድ የመከላከያ ሀላፊ።
በተለይ ቄሮ የተባለው የኦሮሞ ወጣቶች ህብዕ አደረጃጀት ከጊዜ ወደ ጊዜ በመንግስት ተቋማትና በባለሀብቶች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በማድረስ አካባቢያዊ አስተዳደሮችን ለማፍረስ እየሰራ በመሆኑ አፋጣኝ እርምጃ መወሰድ አለበት ብለው እንደሚያምኑ ከምስራቅ ኢትዮጵያ የመጡ የመከላከያ ደህንነት ባልደረባ አስረድተዋል።
በአማራ ክልል ተደጋጋሚ ድንገተኛ ጥቃት በፀጥታ ሰራተኞችና በመንግስት መዋቅር ሀላፊዎች ላይ መፈፀሙን በዚህም ባለፉት ወራት ብቻ ከሀያ የማያንሱ የቀበሌና የወረዳ አስተዳደር ባልደረቦች መምህራንና የጤና ባለሙያዎች ላይ ግድያ መፈፀሙን ከክልሉ የቀረበ ሪፖርት ያስረዳል።
የጦር መሳሪያ ዝውውር መበራከት፣ ትናንሽ ከህግ የሸሹ ሽፍቶች እንደ አዲስ ማቆጥቆጥ በአማራ ክልል የታዩ ችግሮች መሆናቸውንና በቅርቡ ተጨማሪ ሀይል በማሰማራት ስፊ እርምጃ በመወሰዱ ሁኔታው አንፃራዊ መረጋጋት ማሳየቱ ተነግሯል።
ከመቀሌና ከጎንደር የሚነሱ የህዝብ ማመላለሻና የጭነት ተሽከርካሪዎች በተደጋጋሚ የጥቃት ኢላማ በመሆናቸው የጉዞ መስመር ለውጥ ማድረግ እንደተገደዱና ይህም ረጅምና አስቸጋሪ መንገዶችን እንዲጋፈጡ ምክንያት እንደሆነ ተወስቷል።
ማናቸውንም ስፖርታዊና ህዝባዊ ስብሰባዎችን ከአጎራባች ክልሎች ጋር ማድረግ ባለመቻሉ ዝግጅቶች መሰረዛቸውን ብሎም ወደ ሌላ አካባቢ እንዲዛወሩ መደረጉን ተሰብሳቢዎች ተናግረዋል።

የፖለቲካ አመራሩ ብቃት ያለውና ወደ መፍትሄ የሚወስድ ይ አፖለቲካ ውሳኔ ካላሳለፈና ተግባራዊ ካላደረገ እንዲህ ያለውን የፀጥታ ጉዳይ በሀይል ብቻ ለመመከት መሞከር ችግሩን እንደሚያባባስ ከፖሊስ ስራዊት አባላት ሀሳብ ቀርቧል።
አቶ ሲራጅ ፈጌሳ የክልልና የፀጥታ አካላቱን ሪፖርት ካዳመጡና ውይይት ከተደረገ በኋላ ከሁለት ወር በፊት የተነደፈውን የፀጥታና የደህንነት ዕቅድ በመከለስና ለተሰብሳቢዎች በማስረዳት ክልሎችና የፌደራል መንግስት አዲስ የጋራ የፀጥታ ዘመቻ ተግባራዊ እንዲደረግ የተላለፈውን ውሳኔ አብራርተዋል።
ለሁከት ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ተጨማሪ ሀይል የሚሰማራ ሲሆን በመላው ሀገሪቱ ያሉ ዋና ዋና መንገዶችንና ተቋማትን ደህንነት መጠበቅ የሚያስችል እቅድ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።
በአድመኞችና በሁከት ፈጣሪዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ የሚወሰድ ሲሆን በእስካሁኑ ሁከት የተሳተፉትን ህግ ፊት ለማቅረብ ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።
የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ፖለቲካዊ ስራዎች የሚሰሩ ሲሆን አዲሱ የፀጥታ እቅድ ከየአካባቢው ማህበረሰብ የሀገር ሽማግሌና የሀይማኖት ተቋማት ጋር ተግባራዊ እንደሚደረግ ይጠበቃል።

የመከላከያና የፖሊስ አባላት ከፍተኛ የአቅርቦትና የፋይናንስ ችግር እንዳለባቸው ላቀረቡት ጥያቄም ከማዕከል ችግር ወዳላባቸው አካባቢዎች አስፈላጊው ድጋፍ መድረሱን የሚከታተል አካል እንደሚመደብና መንግስት የሀገሪቱን አቅም ያገናዘበ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተነግሯል።

“የሰራዊቱ አባላት ህዝቡ እንዲጠላንና እንዲያጠቃን ስለተቀሰቀሰ ለስራችን ትልቅ እንቅፋት ሆኗል” ፣ “መንግስት በኦሮሚያ ላለው ችግር ለምን ፈጣን ምላሽ አልሰጠም?  “በሰራዊቱ ውስጥ ድሮ የነበረው መተማመንና አንድነት አሁን የለም”  የሚሉ ሀሳቦች ተነስተዋል።