Bewketu 1(ዋዜማ ራዲዮ)-ለዘብተኛ ፖለቲከኛ የሚሉት አሉ፣ ስለታዋቂነቱ ለመናገር ዝግጁ አይመስልም ግን ደግሞ ሰዎች ከሱ ምን እንደሚጠብቁ ጠንቅቆ ያውቃል። የአድናቂዎቹን ቀልብ የሚገዛ ስራ ይዞ ለመምጣት አመታት ፈጅቶበታል። እነሆ ሰለ አዲሱ የበዕውቀቱ ስዩም “ከአሜን ባሻገር” መፅሀፍ ውልደት በዋዜማ ራዲዮ የተሰናዳውን አድምጡልን።ዘጋቢያችን ሰሎሞን ሩሽዲ ስለ በዕውቀቱና ስለስራዎቹ የሚለን አለው- መዝገቡ ሀይሉ ያቀርበዋል።

የሥነ ጽሑፍ ዳዴ
በዕውቀቱ ስዩም ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ደብረማርቆስ የ2ኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ ‹‹ፈውስ›› የምትል የበቀል ትውፊት ላይ መሰረት ያደረገች ተውኔት ጻፈ፡፡ ተውኔቷ ከማርቆስ አልፋ የባህርዳር መድረክ ላይ ለመታየት በቃች፡፡ ተመልካቾቹ ጎረምሳው በዕውቀቱ እንደነገሩ በጻፋት ተውኔት ላይ እየተንፈቀፈቁ መሳቃቸው ለብላቴናው ፀሐፊ የልብ ልብ ሰጠው፡፡
ማርቆስ ዉስጥ የእንግሊዝኛ መምህር የሆኑት አባቱ እርሱንም ጭምር አስተምረውታል፡፡ እርሳቸው ታዲያ ቢሆን ቢሆን ኢኮኖሚክስ ካልሆነም አካውንቲንግ እንዲያጠና ጽኑ ፍላጎት ነበራቸው፡፡ በዕውቀቱ ግን ነፍሱ ለፍልስፍና ትምህርት አደላች፡፡ ኾኖም የአባትም የልጅም ምኞት ሳይሰምር ቀረ፡፡በዕውቀቱ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በገባበት ዘመን የፍልስፍና ትምህርት ክፍሉ ተዘግቶት ስለነበር እርሱ ‹‹የፍልስፍና ታናሽ ወንድም›› ብሎ የሚጠራውን የሳይኮሎጂ ትምህርት ለመማር ተገደደ፡፡ያም ሆኖ ‹‹ሰቃይ›› የሚባል ተማሪ አልነበረም፡፡
በወቅቱ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በነበረበት ዘመን የዩኒቨርስቲው የባህል ማዕከል የጥበብ ከርቤ የሚንቦለቦልበት ዘመን ነበር ቢባልለትም እርሱ ግን በአብዛኛው ታዳሚ እንጂ አቅራቢ አልነበረም፡፡ ከነዚህ ምሽቶች በአንዱ ግን አሁን በካናዳ በጥገኝነት የሚኖረውና የያኔው ወዳጁ ተክለሚካኤል ወደ ባህል ማዕከል ተሳታፊነት አሸጋገረው፡፡ ግብዣውን የተቀበለው በእውቀቱ ፈራ ተባ እያለ ሁለት ግጥሞቹን ለተሳትፎ ያህል አበረከተ፡፡‹‹እንጀራ›› እና ‹‹የበረሀ ጠኔ›› የሚሉት ግጥሞቹን እፍግፍግ ባለው አዳራሽ ዉስጥ ድምጹን ጎላ አድርጎ አነበባቸው፡፡

‹‹ጭብጨባው ዘለግ ሲልብኝ የሹፈት መስሎኝ ነበር›› ይላል በወቅቱ የተፈጠረበትን ስሜት ሲያስታውስ፡፡
በእውቀቱ በ1994 የዲግሪ ቆብ ሲደፋ በተማረበት የስነልቦና ሳይንስ ዘርፍ የመቀጠር ግብ አልሰነቀም ነበር፡፡ ኾኖም ኑሮ አስገደደችው፡፡ ጋዜጣ አገላብጦ፣ ሥራ ፈልጎና አፈላልጎ፣ የኤች አይ ቪ ኤድስ የምክር አገልግሎት ባለሞያ ሆነ፡፡ የአሁኑን በዕውቀቱን በዚህ የአማካሪነት ወንበር ማሰብ በራሱ ፈገግታን የሚጭር ጉዳይ ቢሆንም በዚሁ ሞያ ለመንፈቅ ያህል ሠርቶበታል፡፡ የቢሮ ሥራው ያተረፈለት ነገር ቢኖር ‹‹ዮፍታሄ ›› የሚባል ግሩም ገጸ ባህሪን እንዲስል ማስቻሉ ነበር፡፡ ‹‹እንቅልፍና ዕድሜ›› ለተሰኘው መጽሐፉ ከሽኖ የቀረፀው ይህ ገጸ ባህሪ የኤች አይ ቪ የምክር አገልግሎት የሚሰጥ ሰው ነው፡፡

‹‹ጎዴ ስንሻው›› የሚባለው የብእርና የገጸ ባሕሪ ስም በዩኒቨርስቲ ቆይታውና በባህል ማእከሉ ሲሳተፍ የሚታወቅበት ቢሆንም አብዛኛውን ዘመኑን የጻፈው በእውነተኛ ስሙ ነው፡፡ አዲስ አድማስ ላይ የጥበብ አምደኛ ሳለም በዚሁ ስም አጫጭር ልቦለዶችን አስነብቧል፡፡ያን ጊዜ ይጽፋቸው የነበሩ ልቦለዶች የስነልቦና ጥምዝ ይበዛቸው ነበር ይላሉ አንባቢዎቹ፡፡

የግል የሕትመት ሚዲያው በብዛት ይገኝ በነበረበት ወቅት በዕውቀቱ በብዙዎቹ ላይ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ተሳትፎ አድርጓል፡፡ አንዳንዶቹን የሕትመት ሚዲያዎች ባርኮ የከፈታቸውም እርሱ ነበር፡፡ በጊዜው ኑሮውን ይደጉም የነበረው በጽሑፍና ትርጉም ሥራ ብቻ ስለነበረም በአስገዳጅ ሁኔታዎች ዉስጥ ለብዙዎቹ አዲስና ነባር መጽሔቶችና ጋዜጦች ለመጻፍ ይገደድ እንደነበር ይወሳል፡፡
በጋዜጣ ዘርፍ በሳምንታዊው አዲስ አድማስ እጆቹን ያፍታታው በእውቀቱ ወደ መዝናኛ በኋላም ወደ አዲስ ነገር ጋዜጣ የጥበብ አምደኝነት ሲሻገር እውቅናውን አንድ እርከን ከፍ ያለ አደረገው፡፡ በተለይም ከምርጫ 97 በኋላ በመጡ የሕትመት ዉጤቶች ላይ የበዕውቀቱ የተባለ ጽሑፍ በሙሉ ታድኖ የሚነበብበት ወቅት ስለነበር ጋዜጦች ያለርሱ ፍቃድም ቢሆን ሥራዎቹን ከማተም ወደኋላ ያሉበት ጊዜ የለም፡፡
ከአዲስ ነገር መዘጋት በኋላ አሁን በእስር ቤት የሚገኘው ተመስገን ደሳለኝ በሚመራቸው በፍትህና በፋክት መጽሔቶች ጠጠር ያሉ ሥራዎቹን አቅርቧል፡፡ በተለይም ከሀያሲና ደራሲ አለማየሁ ገላጋይ ጋር በቴዎድሮስ ስብዕና ላይ ያደርግ የነበረው ሙግት ብዙ ተከታዮችን አፍርቶለታል፡፡

‹‹እግር አልባው ባለክንፍ›› የተሰኘውና በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የጻፈው ፌዝ ቀመስ ተቺ ጽሑፍ የአንድ ዲያቆን ቡጢ እንዲያርፍበት ምክንያት ሆነ፡፡

ይህ ጽሑፍ ያስነሳው አቧራ የመዝናኛና ማኅበራዊ ሚዲያውን ሁለት ጎራ ለይቶ ያከራከረ ሲሆን እርሱና ጽሑፉ በመጪው ዘመን እንደዋዛ የሚታለፉ እንዳልሆነም ጠቆም አድርጎ አልፏል፡፡
በከፍተኛ ደረጃ እያደገ የመጣው ዝናውና የማዝናናት ተሰጥኦው ኑሮውን መደጎም በሚያስችል ቁመና ላይ ባያደርሱትም በአዲስ ነገር፣ በአዲስ ጉዳይና በፋክት መጽሔት ለሚያቀርባቸው ሥራዎች በሕትመት ሚዲያ ከዚያ ቀደም ባልተለመደ መልኩ ዳጎስ ያለ ክፍያም ያስገኝለት ነበር፡፡ አዲስ ነገር ላይ በየ15 ቀኑ ይቀርቡ የነበሩት ሽሙጥ አዘል ልቦለዶቹ ከጋዜጣው መዘጋት በኋላ ‹‹መግባትና መውጣት›› በሚል ርዕስ በመጽሐፍ መልክ ለሕትመት ሲቀርቡ በሰፊው ተነባቢ መሆን ችለው ነበር፡፡ ሰባት ጊዜ በተደጋጋሚ በመታተም 50 ሺ ኮፒ ያህል እንደተሸጠለት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

የተራዘመው የሥነ ጽሑፍ ምጥ
በዕውቀቱ በአዲስ ሥራ ለመምጣት ማማጥ የጀመረበት ምዕራፍ ከዚሁ ‹‹መግባትና መውጣት›› ከተሰኘው መጽሐፉ ሕትመት ወዲህ ነበር፡፡ ይህ ሥራው የጋዜጣ ጽሑፍ ስብስብ በመሆኑ እንደመጨረሻ ወጥ ሥራ ላይወሰድ ይችላል፡፡ የመጨረሻው ወጥ የመጽሐፍ ሥራው እንቅልፍና እድሜ ሲሆን ከታተመ ድፍን 8 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይህ ሁኔታ በየመድረኮቹ አልፎ አልፎ ካቀረባቸው ሥራዎቹ ጋር ተደማምሮ በእውቀቱን በእጅጉ እንዲናፈቅ አድርጎታል፡፡

በዕውቀቱ በነዚህ 8 ዓመታት ውስጥ ከአድናቂዎቹ በአዲስ ሥራ እንዲመጣ ከፍተኛ ግፊት እንደነበረበት መገመት አያዳግትም፡፡ በዕውቀቱን ያገኘ አድናቂ ከሰላምታ ቀጥሎ የሚያቀርብለት የመጀመርያ አስተያየት ‹‹አዲስ ሥራ ጀባ በለን እንጂ…ምነው ጠፋህብን›› የሚል ሆኖ ቆይቷል፡፡

ይህ በደራሲው ላይ ቀጥተኛ ያልሆነ ጫና መፍጠሩ አልቀረም፡፡ ጫናው ጥንቃቄን ፈለገ፣ ጥንቃቄው ጊዜን ፈለገ፣ የአሜን ባሻገር መዘግየት ሚስጢርም ይኸው ነው፡፡በርግጥም ‹‹ከአሜን ባሻገር›› የሽፋን ሥራው ተሰርቶ ለገበያ ይቀርባል ከተባለ እንኳን ሦስት ድፍን ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ የመዘግየቱ ነገር ጠንካራ ሥራ ይዞ መቅረብን አጥብቆ ከመሻት ይመስላል፡፡

ከጽሑፍ ባሻገር
በዕውቀቱ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ሸንቋጭ ሐሳቦችን እያሰለሰም ቢሆን ያነሳል፡፡ በዚህም አንዳንዶች ለዘብተኛ ተቃዋሚ አድርገው ይቆጥሩታል፡፡ ይህን ስሜት ያጎላው ከጥቂት ዓመታት በፊት ሰማያዊ ፓርቲ በጠራው ተቃውሞ ሰልፍ ላይ ተገኝቶ ፎቶው በማኅበራዊ ሚዲያ ከተዛመተ በኋላ ነው፡፡ ቴዲ አፍሮ 70 ደረጃ የሚለውን ነጠላ ዜማ ለአድማጭ ባቀረበ ማግስት ድምጻዊውን በማብጠልጠል ስሙን ለማጉደፍ የተጣጣሩትን ፖለቲከኞች ዝም ለማሰኘት አንድ ጽሑፍ መጻፉ ይታወሳል፡፡ ለጽሑፍ ሥራው በፌሎውሺፕ ወደ አሜሪካ ካቀና በኋላ ደግሞ ብዙ አንባቢዎቹ ባልለመዱት ሁኔታ ፖለቲካዊ ቅኝት ያላቸው የሥነ ጽሑፍ ትንኮሳዎችን በገዢው ፓርቲ ላይ መሰንዘሩ ልጁ ወደ አገሩ አይመለስ ይሆን የሚል ጥርጣሬን እስከማጫር ደርሷል፡፡ ለደኅንነቱ የሚጨነቁ አንዳንዶችም እንዳይመለስ ምክራቸውን ለግሰውታል፡፡

በዕውቀቱ ከዝና ባሻገር
በዕውቀቱ ዝናን በሦስት ደረጃ ይመለከታል፡፡ አንደኛው    ዝና የቴዲ አፍሮ ዓይነት ሲሆን ‹‹ስመጥር መሆን›› ብሎ ይጠራዋል፡፡መጠነኛ እውቅና ያላቸው ሰዎች የሚገኙበትን ሁለተኛውን ደረጃ ደግሞ ‹‹ታዋቂነት›› ተብሎ ይጠራል፡፡ሦስተኛው በቤተሰብ ብቻ የሚታወቅ ሲሆን ስሙም ‹‹አባወራ›› ይሰኛል ሲል ያብራራል፡፡የርሱ እውቅና በነዚህ መሐል ሆኖ ነገር ግን ‹‹አጠራጣሪ እውቅና›› የሚባል ዓይነት ነው ሲል በአንድ ወቅት ከመዓዛ ብሩ ጋር ባደረገው ቆይታ ላይ በተለመደው የጨዋታ ለዛው ተናግሯል፡፡ ይሁንና በዕውቀቱ አሁን ያለበት የመወደድና የመታወቅ ደረጃ እርሱ እንደሚለው አጠራጣሪ ከመሆን ይልቅ ትልቅ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ግልጽ ነው፡፡ ከዚሁ መወደዱና መከበሩም የተነሳ ይመስላል የርሱን ፈለግ የሚከተሉ አዳዲስ ጸሐፍያን መታየትም ጀምረዋል፡፡
በእውቀቱ በ1995 ለሕትመት ያበቃት ‹‹ኗሪ አልባ ጎጆዎች›› የግጥም መድብል አምስት ጊዜ ታትማ ከገበያ ጠፍታለች፡፡

የዚህች ግጥም ስኬት ምስጢር ቁጥብነትና ሰፊና ጥልቅ ሐሳብን መመጠን ቢሆንም ይህንኑ ዘዬ ለመከተል የሞከሩ ብዙ ወጣት ፀሐፊዎች አራት መስመር ስንኝ ጽፈው ገጣሚ እንደሆኑ እንዲሰማቸው የልብ ልብ የሰጠች መጽሐፍ እንደሆነች የሚተቹ ሰዎች አሉ፡፡ በዕውቀቱ ሳያስበው ለወጣቶቹ መጥፎ ምሳሌ ሆኗል የሚሉ ብዙ ናቸው፡፡

እርሱ ግን ‹‹ግጥሞቼ አጭር የሆኑት ሐሳባቸው ስላለቀ እንጂ አጭር እንዲሆኑ ታቅደው አይደለም›› ይላል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ እርሱ ከማርቆስ አዋቂዎች ቀሰምኩት የሚለውና ቃላትን በድርብ ትርጉም የማጫወት ዘዴ ‹‹ Malapropism ›› ሌሎችም በቸከ መንገድ እንዲጠቀሙበት መንገድ ከመክፈቱ የተነሳ አሁን አሁን የሰርክ ድግግሞሽ ‹‹ክሊሼ›› ወደመሆን ተጠግቷል፡፡ እንደምሳሌ ያህልም ሽርፍራሪ ታሪኮች በተሰኘው ስራው ውስጥ እንዲህ የሚል አረፍተነገር እናገኛለን፡፡
‹‹ተባሩኩ!›› ለነገሩ ድሀ ከሚባርካችሁ ሐብታም ይማርካችሁ…፡፡
ቃላቱን እንዲህ በተመሳስሎሽ ለማጋጨት በተደረገ ሙከራ በዕውቀቱን የማይመጥን ልል አገላለጽ ይወለዳል፡፡ እንደመታደል ሆኖ እርሱ ይህን ስልት ሲጠቀምበት ከመቶ አንድ አንድ ጊዜ ባይሳካለት ነው፡፡ ሌሎች ማኅበራዊ ሚዲያ የወለዳቸው ፀሐፊዎች ሲጠቀሙበት ግን ከስምረቱ ክሽፈቱ ይበዛል፡፡
የበዕውቀቱ የ15 ዓመታት የሥነ ጽሑፍ ጉዞው በጥቅሉ የሰመረ የሚባል ነው፡፡ በማስተር ሳውንድ አሳታሚነት ከኮሜዲያን ደረጀ ጋር ሆኖ የተወነበት ‹‹እየሳቁ መኖር ›› የተሰኘው ኮሜዲ ፊልም ‹‹በመጠኑ የከሸፈበት›› የሚባል ካልሆነ በቀር ሥራዎቹ እያደጉ እንጂ እየኮሰመኑ አልመጡም፡፡ አድናቂዎቹ ፍጹም ስኬትን ከርሱ መጠበቃቸው እርሱ ላይ ቁጥብነትና ከልክ ያለፈ ጥንቃቄን ሳያስከትልበት ግን አልቀረም፡፡Bewketu 4
በዕውቀቱ ከሃይማኖት ባሻገር
‹‹እግር አልባው ባለክንፍ›› የተሰኘችው መጣጥፍ ለቡጢ ከዳረገችው ወዲህም ቢሆን በዕውቀቱ አይነኬ የሚመስሉ ታሪኮችና ሃይማኖታዊ ቀኖናዎችን በስሱም ቢሆን መተቸትን አላቆመም፡፡ “ታሪክን ወግን ልማድን ዝቅ አድርጎ የማየት ነገር አለብህ ወይ?” የሚል ጥያቄ በአንድ ወቅት ተነስቶለት ባሕልን በሁለት መልኩ እንደሚያይ አብራርቷል፡፡ “አንደኛው የእምነት ባህል ሲሆን ሁለተኛው የጥርጣሬና ነጻ መንፈስ ባህል ነው፡፡ የእምነት ባህል – እነ አቡነ ተክለሀይማኖት እነ ቢላል የሚገኙበት ጎራ ሲሆን የጥርጣሬና በነጻ መንፈስ ባህል አለቃ ገብረሃና፣ እማሆይ ገላነሽ፣ ዘርአ ያእቆብና ወልደ ሕይወት የሚገኙበት ነው›› ሲል ካብራራ በኋላ የርሱም ቦታ ይኸው ሁለተኛው መደብ እንደሆነ ይናገራል፡፡
በዕውቀቱን የተራቡ ሼልፎች
በአዲስ አበባ አስፋልትና ደረታቸው ላይ አንጥፈው መጽሐፍ የሚቸረችሩት ብዙዎቹ በዕውቀቱን በአካል ያውቁታል፡፡ ደራሲ ብቻ ሳይሆን የወንዝ ልጅም ነው፡፡ እነርሱም ከአንባቢው በላቀ የርሱን መምጣት ናፍቀዋል፡፡ በነጋ ቁጥር ‹‹የበዕውቄ ወጣ እንዴ?›› የሚላቸው ሕዝብ በቁጥር እጅግ ብዙ ነው፡፡
‹‹የሱ ሲወጣ በሌላ መጽሐፍ ክንዴ አይዝልም…›› የሚለው የአራት ኪሎው የመጽሐፍ አዝዋሪ አፈወርቅ ሰሞኑን ጓደኞቹ እቁብ እንዲሰጡት እየተማጸነ እንደሆነ ይናገራል፡፡ አላማውም በሚደርሰው ገንዘብ ሁሉ የበዕውቀቱን መጽሐፍ በብዛት ገዝቶ ቶሎ ቶሎ መቸርቸር ነው፡፡
“አንድ ሰው የኪነ ጥበብ ሥራ ሲያበረክት በምላሹ የሚሰፈርለት ቀለብ መኖር አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ የድሮ ተራኪ ‹‹ተረቴን መልሱ አፌን በዳቦ አብሱ›› ይላል፡፡ ዳቦ ዋጋው ነው፡፡” ሲል የሚናገረው በዕውቀቱ የዓመታት ድካሙ የሚካስበት ጊዜ የደረሰ ይመስላል፡፡

ሰለሞን ሩሽዲ- ለዋዜማ ራዲዮ