ዋዜማ ራዲዮ- ዛሬ ከሰዓት በኋላ (ረቡዕ) የተሰየመው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በእነ እስክንድር ነጋ መዝገብ የምስክር ስሚን ሂደት በተመለከተ በቀረበው አቤቱታ ላይ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጠውን ውሳኔ በመሻር ክርክሩ እንዲቀጥል በይኗል፡፡

እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ ቀለብ ስዩም፣ አስካለ ደምሴ እና ጌትነት በቀለ በሽብር ወንጀል በፌደራል ከፍተኛ ፍር ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ ሽብር እና በህገመንግስት ላይ የመፈፀሙ ወንጀሎች ጉዳይ ችሎት ክስ ተመስርቶባቸው በክርክር ላይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን ክስ ክደው መከራከራቸውን ተከትሎ ምስክር እንዲያሰማ የተጠየቀው አቃቤ ህግ ምስክሮቹ ዛቻ እና ማስፈራሪያ እንዲሁም የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸዋል በማለት በምስክሮች እና ጠቋሚዎች ደህንነት ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 መሰረት ከዘረዘራቸው ምስክሮች ውስጥ ገሚሱን በዝግ ችሎት ገሚሱን ደግሞ ከመጋረጃ በስተጀርባ ለማሰማት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

ተከሳሾች ግን ይህ ጥያቄ ህገመንግስቱ ከሰጣቸው መብት ጋር የሚቃረን እና የሚመሰክርባቸውን አይተው መስቀለኛ ጥያቄ የማቅረብም ሆነ የመከላከል መብታቸውን የሚጋፋ እንደሆነ ለችሎቱ በመግለፅ ተከራክረዋል፡፡

የግራቀኙን ክርክር ያዳመጠው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ችሎትም የአቃቤ ህግን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ምስክሮቹን በግልፅ ችሎት እንዲያሰማ ትዕዛዝ ሰጥቷል

ሆኖም ከሳሽ አቃቤ ህግ ትዕዛዙን በመቃወም ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ 2ኛ ወንጀል ችሎት ይግባኝ ብሏል፡፡ ችሎቱም የአቃቤ ህግን አቤቱታ ከመረመረ በኋላ ይግባኝ የሚያስቀርብ አይደለም በማለት ታህሳስ 13 ቀን 2013 ዓ.ም ውድቅ አድርጎት ነበር፡፡

ይህን ተከትሎም አቃቤ ህግ ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ አቤቱታውን የመረመረው ከወንለኛ መቅጫ ስነስራዓት ህጉ አንፃር ብቻ በመሆኑ ልክ አይደለም በማለት ጉዳዩን ወደ ሰበር ሰሚ ችሎት ወስዶታል፡፡

ታዲያ በዚህ ጉዳይ ላይ መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ዛሬ የካቲት 10 ቀን 2013 ዓም ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ የተሰየመው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የይግባኝ ሰሚ ችሎቱን ውሳኔ አግባብ ይደለም በማለት ሽሮታል፡፡

የስነ ስርዓት ህጉ አገልግሎት ላይ መዋል ከጀመረ 40 አመታትን አስቆጥሯል ያለው ችሎቱ ከዛ በኋላ የወጡ እንደ የምስክር እና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጆች ውሳኔ ሲሰጥ ከግምት ውስጥ መግባት እንዳለባቸው ተናግሯል፡፡

በመሆኑም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይጋበኝ ሰሚ ችሎት የሰጠው ውሳኔ ተሸሮ ምስክሮች ከመጋረጃ በስተጀርባ እና በዝግ ችሎት መቅረብ አለባቸው ወይንሰ የለባቸውም የሚለውን ግራ ቀኙን አስቀርቦ እንዲያከራክር ውሳኔ ተላልፏል፡፡[ዋዜማ ራዲዮ]