ዋዜማ ራዲዮ- በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የጠራ አስተያየት በመስጠት የሚታወቁት ቴረንስ ሊየንስ አዲስ መፅሐፍ ለንባብ አብቅተዋል
የተለያዩ ጥናቶችን በመፃፍ አስተያየት በመስጠትና በማማከር ለአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቅርብ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ቴረንስ ሊየንስ የኢትዮጵያ የፖለቲካ እንቆቅልሽ (The Puzzle of Ethiopian Politics) የሚል ርዕስ የሰጡትን ወደ 250 ገፅ ያለው መፅሐፍ አሳትመዋል።

መፅሐፉ የኢትዮጵያን የፖለቲካ አጣብቂኝ በማውሳት ጀምሮ ሙሉ ትኩረቱን በኢሕአዴግ መንግስት ዘመነ ስልጣን ላይ አድርጎ የመለስ ዜናዊን የአገዛዝ መንገድ በዝርዝር ይመለከታል። ምርጫ ዘጠና ስባት፣ ልማታዊ መንግስትና የቅርብ ጊዜው ህዝባዊ አመፅና የፖለቲካ ለውጥ በመፅሐፉ ተካተዋል።
በእርግጥ መፅሐፉ ከፖለቲካ ለውጡ በፊት የተፃፈ ስለነበር አዳዲሶቹን ለውጦች ለማካተት አስቸጋሪ እንደነበር ፀሀፊው በመግቢያቸው ላይ ያብራራሉ። የመጨረሻዎቹ ሶስት ምዕራፎች በለውጡ ዙሪያ ያተኮሩ ናቸው። ኢትዮጵያ ወደተሻለ መንገድ እያመራች ነውን? ሲሉ ይጠይቃሉ የጆርጅ ሜስን ፕሮፌሰሩ ቴረንስ ሊየንስ።
መፅሐፉ ከአንድ ወር በፊት ለተመረጡ አስተያይት ስጪዎች ተበትኖ የነበረ ሲሆን ካረፈው ሳምንት ጀምሮ ደግሞ ለገበያ ቀርቧል። ዋጋው ስማንያ የአሜሪካ ዶላር ነው።