internetዋዜማ ራዲዮ- እየተገባደደደ የሚገኘው የአውሮፓውያኑ ዓመት 2016 በአፍሪካ የኢንተርንርኔት መቋረጥ በብዛት የታየበት ዓመት እንደነበረ ፓራዳይም ኢንሽየቲቭ ናይጄሪያ (paradigm Initiativen Nigeria) የተባለ ድርጅት ያዘጋጀው ሪፖርት ጠቁሟል።

በሜክሲኮ ጓዳላሃራ ተኪያሒዶ በነበረው የበይነመረብ አስተዳደር ጉባዔ (Internet Governance Forum) ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ የኾነው ይህ ሪፖርት የአፍሪካ መንግስታት ለአህጉሪቱ እድገት ወሳኝ ሚና ሊጫወት በሚችለው የኢንተርኔት አገልግሎት ላይ ገደብና ማነቆ ሲጥሉበት እንደሚታይ እና ይህም በዚህ ዓመት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበረ ይገልጻል። በዚህ ዓመት ብቻ ኢትዮጵያን ጨምሮ 11 የአፍሪካ አገራት የኢንተርኔት አገልግሎት አቋርጠው እንደነበረም በሪፖርቱ ተጠቁሟል። የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡም በየአገራቱ ያለውን የዲጂታል ቴክኖሎጂ የመጠቅም መብት በመጻረር የየአገራቱ ዜጎች ሊያገኙት የሚገባውን ለእድገትና ለዲሞክራሲያዊ ጥያቄ ወሳኝ የኾነ መረጃ እንደሚነፍጋቸውም ሪፖርቱ ጠቁሟል።

በዚህ ዓመት በኢትዮጵያ በተከሰተው ሕዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት ኢንተርኔት ማቋረጥን ተቃውሞውን የማፈኛ መንገድ አድርጎ የተጠቀመው የኢትዮጵያ መንግስት በሪፖርቱ ላይ ከዋነኞቹ የዲጂታል መብት ተጻራሪ መንግስታት መካከል አንዱ ሆኖ ተጠቅሷል።የኢትዮጵያ መንግስት  የኢንተርኔት አገልግሎት ከማቋረጡም በተጨማሪ በሌሎች የመገናኛ ብዙኃን ላይ የሚጥለውን አይነት አፋኝ ገደብ በኢንተርኔት አገግሎትም ላይ ለመጣል የሚያስችለው ሕግ ማሳለፉም በሪፖርቱ ተጠቃሽ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ ነበር።

ከዚህም በተጨማሪ የበይነመረብ ተሟጋቾችንና ጦማሪዎችን ሲያስር የከረመው የኢትዮጵያ መንግስት እነኚህ ጉዳዮች በዲጂታል መብት ላይ ለሚያደርሰው ተጽእኖ ማሳያ ሆነው በሪፖርቱ ተዘርዝረዋል።  የአህጉሪቱን ጠቅላላ የዲጂታል መብት ሁኔታ የዳሰሰው ይኸው ሪፖርት ይህ ኢንተርኔት የመጠቀም መብት ላይ ማነቆ በመጣሉ ጉዳይ ላይ ተወቃሽ የኾኑት ወትሮም ቢኾን በአፋኝነታቸው የሚታወቁት የኢትዮጵያውን የመሰሉ መንግስታት ብቻ ሳይኾኑ በዲሞክራሲያዊነታቸው  የሚታወቁትን የደቡብ አፍሪካንና የኬንያን የመሳሰሉት መንግስታትም ጭምር ናቸው። ደቡብ አፍሪካና ኬንያ በዚሁ የፈረንጆች ዓመት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አቅርቦት የነበረውን የበይነ መረብ ነጻነትን የሚመለከት ስምምነት ኢትዮጵያን ከመሰሉ መንግስታት ጋር በማበር በመቃወማቸውም ምክንያት በሪፖርቱ ስማቸው በክፉ ተነስቷል።

ይህ ሪፖርት ለየት ከሚያደርጉት ባህርያትም መካከል አንዱ የየአገራቱ መንግስታት በዲጂታል ነጻነት ላይ ያሳረፉትን አሉታዊ ተጽእኖ ከማቅረቡ ጎን ለጎን የችግሩ ተጠያቂ ያደረጋቸው የኢንተርኔት አገልግሎት አቅራቢ ኩባንይዎችም ጭምር ነው። ሪፖርቱ ከአፍሪካ መንግስታት ጋር ውል በመግባት የኢንተርኔት አገልግሎት የሚሰጡ የምእራቡ ዓለም አገራት ኩባንያዎች የመብት ጥሰቱ ተባባሪዎች እንደኾኑ ጠቁሟል። እነኚህ ኩባንያዎች በየአገራቸው የነበራቸውን የሰበአዊ መብትና የስነምግባር ሕግ በመቃረን ለአፍሪካውያኑ መሪዎች አጎብዳጅ ሲኾኑ እንደሚስተዋል ሪፖርቱ ጠቁሟል። የየአገራቱ መንግስታት የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲያቋርጡ ወይም ሌላ የመብት ጥሰት ሊያስከትል የሚችል ተግባር እንዲፈጽሙ ሲያዟቸው እሺ ባይ የመሆናቸውን ጉዳይ የነቀፈው ይህ ሪፖርት ምእራባውያኑ ኩባንያዎች ለጥቅም ሲሉ የሚያደርጉትን ይህን ባሕርያቸውን መለወጥ እንደሚገባቸው አሳስቧል።

ከየትኛውም አገር መንግስታት ጋር በችኮላ ውል ከመፈጸም በፊት የየአገራቱ የዲጂታል ሕግ ከሰበአዊ መብትና የስነምግባር አቋማቸው ጋር የሚስማማ መኾኑን መፈተሽ እንሚኖርባቸውም መክሯል። ሪፖርቱ በዚህ ጉዳይ በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ያለው ነገር ባይኖርም፥ በኢትዮጵያ አንድ ብቻ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ መኖሩንና ይህም አገልግሎት ሰጪ የመንግስት ተቋም መኾኑን ኢትዮጵያን በተመለከተ ባቀረበው ሪፖርት ክፍል ገልጿል።

“የነጻነታችን ልክ በየአገራችን ጉዳይ እንደዜጋ በምንሳተፍበት መጠን የተገደበ ነው ።” የሚለው ይህ ሪፖርት ይህን የመሰሉ የኢንተርኔት ክልከላዎች በድንገት የሚከሰቱ እንዳልሆኑም ጥቁሟል። ለዚህ እንደማሳያ ያቀረበውም እነኚህ የኢንተርኔት ገደቦች ከመጣላቸው አስቀድሞ በብዙ የአፍሪካ አገራት ከሕግ አግባብ ውጪ የሞባይል ስልክ ሲም ካርድ የማስመዝገብ ግዴታ መጣሉን ይጠቅሳል። ተጠቃሚዎች ሲም ካርዶቻቸውን እንዲያስመዘግቡ የማስገደዱ ጉዳይ ብዙ የአፍሪካ አገሮች ካላቸው የመረጃ ነጻነት ሕግ ጋር የሚቃረን ቢኾንም ያለጥያቄ ስራ ላይ ሲውል እንደሚስተዋልም ሪፖርቱ አስታውሷል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ የዲጂታል መብትን ለመገደብ የሚወጡ ሕጎች ብዙዎቹ የአፍሪካ መንግስታት በሕገመንግስታቸው ያስቀመጡትንም ኾነ በፈቃደኝነት የፈረሟቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ከግምት ያላስገቡ አንዳንዴም እነኚህኑ ሕጎች የሚሽሩ ሆነው እንደሚታዩም ሪፖርቱ ያብራራል።

የሪፖርቱን ሙሉ ይዘት እዚህ ያገኙታል- http://pinigeria.org/2016/wp-content/uploads/documents/research/Digital%20Rights%20In%20Africa%20Report%202016%20%28LR%29.pdf