ዋዜማ ራዲዮ- በአፋር ክልል ውስጥ የሕወሓት አማፅያን የከፈቱትን ማጥቃት ተከትሎ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው ወደ ጊዜያዊ መጠለያዎች የመጡ ነዋሪዎች አንድ መቶ ሺሕ ያህል መድረሳቸውን የተለያዩ የረድዔት ተቋማት ምንጮች ለዋዜማ ተናግረዋል።

ነዋሪዎቹ ቀደም ባሉት ቀናት ጦርነቱ በሕወሓት አማፅያንና በፌደራሉ መንግስት እንዲሁም በክልሉ ልዩ ሀይል መካከል ሲቀሰቀስ ከመኖሪያቸው ሸሽተው በተለያዩ አካባቢዎች ተደብቀው የቆዩ ሲሆኑ አሁን ወደ ጊዜያዊ መጠለያዎች እየመጡ ነው።
ከተፈናቃዮቹ ቁጥር አንፃር ከመንግስት እያገኙ ያሉት ድጋፍ በቂ አለመሆኑንና ተጨማሪ ድጋፍ ካላገኙ የከፋ ችግር እንደሚገጥማቸው ስጋታቸውን ለዋዜማ ተናግረዋል።

በአፋር ክልል በተለያዩ ወረዳዎች በተከሰተውን ጦርነት በመፍራት ወደ መጠለያ ጣቢያው የሚገቡ ሰዎች ቁጥር ቀን ከቀን እየጨመረ እየመጣ እንደሆነ ለዋዜማ የተናገሩት አቶ አይደሲስ ያሲን በአፋር ክልል የአደጋ መከላከል ቅድመ ማስተንቀቂያ ፈጣን ምላሽ ዳሬክተር ለዋዜማ እንዳስረዱት ” በዘጠኝ የመጠለያ ጣቢያዎች ተፈናቃዩች አሉ። በአጠቃለይ ያሉት ተፈናቃዩች ቁጥር 76 ሺሕ ነው ፡፡ ተፈናቃዩቹ ወደ መጠለያው ከመጡ ሁለት ሳምንት ያለፋቸው ሲሆን በአሁኑ ሰአት ህፃናት ላይ የምግብ እጥረት ከመከሰት ወጪ ምንም ችግር አልገጠመንም”

በፌደራልና በክልሉ መንግስት እንዲሁም በእርዳታ ድርጅቶች ድጋፍ እየተደረገ ነው ያሉት አቶ አይደሲስ “ጦርነቱ በሕወሓት ቡድን ሲከፈት በተለያዩ ቦታዎች ተደብቀው የነበሩ ነዋሪዎች አሁን ላይ ወደ መጠለያ በመምጣት ላይ ናችው። ስለዚ ከቀን ቀን የተፈናቃዩች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል” ብለዋል። [ዋዜማ ራዲዮ]