ዋዜማ ራዲዮ- የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያ በገባበት ወቅት በስራ ላይ የነበሩ የተወሰኑ ሀኪሞች እና ነርሶች ተቀንሰው ወደ ኮቪድ ወረርሽኝ መከላከያ ግብረ ሀይል እና ማገገሚያ ማዕከላት መሸጋገራቸው የሚታወስ ነው፡፡


ይህን ተከትሎ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ስር ባሉ ስድስት ሆስፒታሎች ውስጥ የሚያገለግሉ አንዳንድ ሀኪሞች ለግብረ ሀይሉ በተቀነሱ ባለሞያዎች ምትክ ተተኪ የሰው ሀይል አለመጨመሩ ለሌሎች በሽታዎች የህክምና አገልግሎት በሚሰጡት ባለሙያዎች ላይ ትልቅ ጫና እንዳሳደረባቸው ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡


የፌደራል መንግስት የሰራተኞች አዋጅ የመንግስት ሰራተኞች መደበኛ የስራ ሰዓት እንደየስራው ሁኔታ ቢወሰንም በሳምንት ከ39 ሰዓታት መብለጥ እንደሌለበት ቢደነግግም ዋዜማ ያነጋገረቻቸው ዶክተሮች በሳምንት ውስጥ ከ108 ሰዓታት በላይ እንደሚያገለግሉ ነው የገለፁት፡፡ እናም የሚያገኙት እረፍት በቂ አለመሆኑ በዕለት ስራቸው፣ በኑሯቸው እና በጤናቸው ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳደረባቸው አስረድተዋል፡፡


“ኮቪድ ከገባ ወዲህ ብዙ ሀኪሞች ወደ ማዕከላት ተወስደዋል፡፡ ከዛ በኋላ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የተወሰነ ሰው በጊዜያዊነት ቢቀጥርም አብዛኞቹ ቋሚ ስራ እያገኙ ስለወጡ የስራ ጫናውን ምንም ያህል አልቀነሰልንም፡፡ ከዚያ በተጨማሪም ሀኪሞች እና ነርሶች ለኮሮና ቫይረስ ያላቸው ተጋላጭነት ከፍተኛ በመሆኑ በእሱ ምክኒያት ከስራ ገበታው የሚቀረው ሰውም ሲጨመር አገልግሎት የምንሰጠው ሀኪሞች ቁጥር በጣም ይቀንሳል” ሲሉ ችግራቸውን ያስረዳሉ ባለሙያዎቹ።

“ በፊት ቢያንስ በየሁለት ቀኑ ነበር አድረን የምንሰራው አሁን ግን በየአንድ ቀን ልዩነት ያለማቋረጥ 36 ሰዓት እንሰራለን፡፡ በአጠቃላይ ከ108 ሰዓት በላይ በሳምንት ውስጥ እንሰራለን፡፡” በማለት በራስ ደስታ አጠቃላይ ሆስፒታል የሚያገለግሉ ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ ሀኪሞች ለዋዜማ ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡


ይህም ለስራው ፣ ለጤንነታቸው እና ለማህበራዊ ኑሯቸው ከባድ ሁኔታ እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡ ለሆስፒታሉ ተጨማሪ ሀኪም እንዲቀጠርላቸው ለአዲስ አበባ ጤና ቢሮ በተደጋጋሚ ደብዳቤ ቢያስገቡም ምንም አይነት ምላሽ እንዳላገኙም አክለዋል፡፡


ዋዜማ ሬዲዮ ለአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ዮሀንስ ጫላ ለዚህ ጉዳይ ምን አይነት እልባት ሊሰጥ እንደታሰበ ጥያቄ ብታቀርብም በቂ ሀኪም እንዳለ እና ምንም አይነት እጥረት እንዳልተከሰተ ነው ምላሽ የሰጡት፡፡


አሁን ላይ በአጠቃላይ በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ጤና ቢሮ ስር ከኮቪድ ውጪ ላሉ በሽታዎችም ህክምና እየሰጡ ባሉት በስድስቱ ሆስፒታሎች ማለትም በራስ ደስታ፣ የካቲት 12፣ ጥሩነሽ ቤጂንግ፣ ዘውዲቱ፣ ጋንዲ እና ጥቁር አንበሳ 433 ዶክተሮች እና 1695 ነርሶች ይገኛሉ፡፡ [ዋዜማ ሬዲዮ]