FILE

ዋዜማ ራዲዮ- በሶማሌ ክልል በሚገኘው ቶጎጫሎ ከተማ የሚገኙ የባንክ ቅርንጫፎች የብድርና የውጭ ምንዛሬ አገልግሎት እንዳይሰጡ ብሔራዊ ባንክ አግዷል። 

ወሳኔው የተላለፈው ብሔራዊ ባንኩ በከተማው የሚገኙ ቅርንጫፎች እንቅሰቃሴ ላይ ባደረገው ጥናት መሰረት ነው። 

ባንኮቹ ለአካባቢው ህዝብ አገልግሎት ከመስጠት ይልቅ ህገወጥ የውጭ ምንዛሬ ግብይት የሚካሄድባቸው መሆኑን ባንኩ በጥናቱ እንደተረዳ ዋዜማ ሰምታለች። ህገወጥ ስራው የውጭ ምንዛሬ እስከማቅረብ እንደሚደርስም ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልልንና ራስ ገዟን ጎረቤት ሲማሊላንድን የምታዋስነው ቶጎጫሌ ከተማ ከፍተኛ ህገውጥ የውጭ ምንዛሬና የኮንትሮባንድ ንግድ ከሚደረጉባቸው ከተሞች መካከል አንዷ ነች። የህገወጥ የነዳጅ ንግድ ቦታም እንደመሆኗ የንግድና ቀጥናዊ ሚንስቴር የኮታ ስርጭት እንዲደረግ ከወሰነባቸው 4 የ ሶማሌ ክልል ቦታዎች አንዷ ነች።

በከተማው ዳሽን፣ አዋሽና አቢሲኒያ ባንኮችን ጨምሮ በርካታ ባንኮች ቅርንጫፎች አሏቸው። 

ብሔራዊ ባንክ ያካሄደውን ጥናት መነሻ አድርጎ በቶጎጫሌ የሚገኙ ቅርንጫፎች በሙሉ ወደ ንዑስ ቅርንጫፍነት(Sub-branch) እንዲለወጡ ውሳኔ ተላልፏል::

ብሔራዊ ባንኩ ከ8 ዓመት በፊት ባወጣው መመሪያ መሰርት ንዑስ ቅርንጫፎች የአለም አቀፍ ባንኪንግና የንግድ ፋይናንስ ስራዎች እንዲሁም የብድር አገልግሎት እንዳይሰጡ ይከለክላል።

የብሔራዊ ባንክ የፋይናንሻል ቁጥጥር ዘርፍ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የጻፈው ደብዳቤ ተጨማሪ ክልከላዎችንም የያዘ ነው። ገንዘብ ገቢና ወጪ የማድረግ አገልግሎት ለአካባቢው ተጠቃሚ ግልሰቦችና ቢዝነሶች ብቻ መሰጠት ሲኖርበት የአካባቢው ነዋሪ ስለመሆናቸውም መረጋገጥ አለብት። ነገር ግን ዝውውር ማድረግ የሚቻለው በዛው በንዑስ ቅርንጫፉ በተከፈቱ ሂሳቦች መካከል ብቻ ነው። 

ብሔራዊ ባንክ እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች በአፋጣኝ እንዲሟሉ ያዘዘ ሲሆን ለቅርንጫፎቹ የተሰጡት ፍቃዶች ተመላሽ ተደረግው አዲስ ፈቃድ እንዲያወጡም አዟል።   

ባንኩ እንደዚህ ዓይነት ጥናት ሲያካሄድ የመጀመሪያው አይደለም። ከሁለት አመት በፊት በተደረገ ጥናትም የተለያዩ ህገወጥ ዝውውሮችን በመለየት ውሳኔዎች አስተላልፎ ነበር። 

በሀገሪቱ የሚገኙት 20 ባንኮች 7, 500 አካባቢ ቅርንጫፎችን በመላው ሀገሪቷ ያንቀሳቅሳሉ። [ዋዜማ ራዲዮ]