PM Abiy Ahmed of Ethiopia and UAE leader Mohamed Ben Zayed- FILE

ዋዜማ ራዲዮ-  ባለፉት ተከታታይ ዓመታት የተደረጉ ድርድሮች አለመሳካታቸውን ተከትሎ በቀጣዮቹ ሳምንታት በተባበሩት  ዓረብ ኤምሬትስ አደራዳሪነት በሕዳሴ ግድብ ውዝግብ ዙሪያ አዲስ ውይይት ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ዋዜማ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል። 

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ምንጮች እንደነገሩን ግብፅ ሱዳንና ኢትዮጵያን ወደ አንድ ጠረጴዛ በማምጣት በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ያሉ አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት ሀገራቸው ገንቢ ሚና ለመጫወት እየተንቀሳቀሰች መሆኗን አመልክተዋል። 

በግድቡ ዙሪያ ቀደም ሲል በአሜሪካ አደራዳሪነት ተሞክሮ የነበረው ውይይት ያለ ውጤት ሲበተን፣ አሜሪካ በዓለም ባንክና በግምጃ ቤቷ  በኩል የዕርዳታና ድጋፍ እቀባ በማድረግ ኢትዮጵያን ለማስገደድ ሙከራ ማድረጓ ይታወሳል። ኢትዮጵያ ውይይቱን ትታ የወጣችው ለግብፅ ያደላ ስምምነት እንድትፈርም ብርቱ ግፊት ከተደረገባት በኋላ ነበር። 

ሌላው የሕዳሴ ግድብ ድርድር በአፍሪቃ ሕብረት በኩል ሲደረግ የነበረ ሲሆን ውይይቱ ያለመቋጫ በእንጥልጥል ቆሟል። 

አሁን በአቡ ዳቢ ሊደረግ ለታሰበው ድርድር የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የቴክኒክና የባለሙያዎች ቡድን አደራጅታ ያለፉትን ሁለት ወራት ዝግጅት ስታደርግ እንደነበር ስምተናል። 

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ  ለዚህ ተልዕኮ የአፍሪቃ ጉዳይ ሚንስትሯን የ32 ዓመቱን ሼክ ሻክቡት ቤን ንህያምን መመደቧም ታውቋል። 

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ሶስቱ ሀገራት ኢትዮጵያ ሶስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ከማካሄዷ በፊት መግባባት ላይ እንዲደረስ ፍላጎት አላት። ኢትዮጵያ ሶስተኛ ዙር የውሀ ሙሌት በቅርቡ ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኗ ይታወቃል።

ሱዳን የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስን አደራዳሪነት በደስታ መቀበሏን ከወራት በፊት ያስታወቀች ሲሆን ኢትዮጵያ በአፍሪቃ ሕብረት በተጀመረው ድርድር ብቻ የመቀጠል ፍላጎት ነበራት። 

ከዚህ ቀደም የየሀገራቱ ተወካዮች ወደ አቡዳቢ በመሄድ ከየተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ አደራዳሪዎች ጋር የተናጠል ውይይት ማድረጋቸውን ለጉዳዩ ቅርብ ነን ያሉ ምንጮች ያስረዳሉ። 

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ድርድር በዚህ ወር ከመጀመሩ አስቀድሞ የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታ አልሲሲ አሜሪካ የሕዳሴውን ግድብ ጉዳይ ቸል እንዳትለው በማሳሰብ ጥያቄ አቅርበዋል። የውጪ ጉዳይ ሚንስትራቸው ሰማ ሽኩሪ ወደ ዋሽንግተን አቅንተው አሜሪካንን የማግባባት ስራ ሲሰሩ ስንብተዋል። 

በሩሲያና ዩክሬይን ጦርነት ገለልተኛ አቋም ያላት ግብፅ ድጋፏን ለዩክሬይን እንድታሳይ አሜሪካ ከፍ ያለ ፍላጎት አላት። በዚህ የግብፅ ገለልተኛ አቋም አሜሪካ የሕዳሴውን ግድብ ጉዳይ ግፊት ለማሳደር እንደተጠመችበትና የአሜሪካ ኘሬዝዳንት የፀጥታ ጉዳይ ሀላፊ ጃክ ሱሌይቫን ይህን ፍላጎታቸውን ለግብፁ መሪ አብዱል ፈታ አልሲሲ መግለፃቸው ተሰምቷል። 

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ያቀደችው ድርድር በአሜሪካ ተፅዕኖ የሚጀመር ይሁን ገለልተኛ እስካሁን የጠራ መረጃ የለም። 

የተባበሩት ዓረብ ዔምሬትስ  በሱዳን ስፋፊ እርሻ የማካሄድ ሰፊ እቅድ ስላላት የአባይ ውሃን ለእርሻ ስራ መጠቀምን የሚደግፍ አቋም አላት። 

በጉዳዩ ላይ አስተያየት የጠየቅናቸው የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች ወደ አቡዳቢው ውይይት ለመጓዝ ዝግጁ ስለመሆናቸው ላነሳንላቸው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት አልፈቀዱም። 

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ለኢትዮጵያ በይፋና ይፋዊ ባልሆነ መንገድ የምታደርገው የፋይናንስና ወታደራዊ ድጋፍ አዲስ አባባ በዚህ ውይይት አልሳተፍም ለማለት አስቸጋሪ እንደሚያደርግባትና የተዳራዳሪ ቡድኑ ወደ አቡዳቢ መጓዙ አይቀሬ መሆኑን ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉና በጡረታ ላይ የሚገኙ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት ነግረውናል። 

የፖለቲካ አስተደዳሩ በበርካታ ጫናዎች ውስጥ ነው። በተለይ የኢኮኖሚ ጉዳይ። ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ከየተባበሩት ዓረብ ኤምሬት መሪ መሀመድ ቤን ዛይድ ጋር ያላቸው ቅርበት ድርድሩን አልቀበልም ለማለት አስቸጋሪ እንደሚሆን ዲፕሎማቱ ይገምታሉ። 

ከዚህ ቀደም በፖለቲካ አስተዳድሩ ውሳኔ በአሜሪካ በኩል የተዘጋጀውን ድርድር እንዲሳተፍ የተላከው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ውይይቱን ጥሎ በመውጣት ለግብፅ አድልቶ የነበረውን ስምምነት ሳይፈረም መቅረቱ ይታወሳል። [ዋዜማ ራዲዮ]

To Reach Wazema Editors please write to wazemaradio@gmail.com