Ethiopian – FILE

ዋዜማ ራዲዮ- በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች እየታየ ያለው አጠቃላይ የነዳጅ እጥረት ወደ አዲስ አበባ ቦሌ ኢንተርናሽናል አየር ማረፊያ የሚመጡትን በረራዎችም እንዳያስተጓጉል የሰጋው መንግስት አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ መጀመሩን ዋዜማ ከተለያዩ ምንጮች ተረድታለች። 

በአየር ማረፊያው በአሁን ሰአት ነዳጅ ሙሉ ለሙሉ ባይሟጠጥም አቅርቦቱ አስተማማኝ ባለመሆኑ አየር መንገዶች ወደ አዲስ አበባ በረራ ከማድረጋቸው በፊት ይህን ችግር እንዲያስቡት እና ነዳጅ ከሌላ ሃገር አየር ማረፊያ  ቀድተው እንዲመጡ እየተመከሩ ነው። 

ከዚህ በፊት በሃገሪቱ የነዳጅ እጥረት እና ስርጭት መስተጓጎል ሲከሰት በቦሌ ኢንተርናሽናል አየር ማረፊያ ግን የአውሮፕላን ነዳጅ እጥረት አሳሳሲ ደረጃ ደርሶ አያውቅም ነበር። 

አሁን የተከሰተው እጥረት መንግስትንም ሆነ በአቪየሽን ዘርፍ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣንም ችግሩ እንዳይባባስ እርምጃዎች መውሰድ መጀመሩን ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የአውሮፕላን በረራ ባለሙያ ያስረዳሉ። 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎች መስተጓጎል እንዳይገጥማቸው የነዳጅ ክምችቱን ለማሻሻል ብዙ ሙከራዎች እየተደረጉ መሆኑን ባለሙያው ነግረውናል። ችግሩ በአጭር ጊዜ ይፈታል የሚል ተስፋ አላቸው። 

በአዲስ አበባ ቦሌ ኢንተርናሽናል አየር ማረፊያ ውስጥ ቶታል (Total) እና ኖክን (NOC) ጨምሮ አራት የነዳጅ ድርጅቶች የአውሮፕላን ነዳጅ በማከፋፈል የተሰማሩ ሲሆን ከኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ከጅቡቲ ወደብ ጀምሮ የሚቀርብላቸውን የአውሮፕላን ነዳጅ በአየር ማረፊያ ውስጥ ለሚያርፍ ማንኛውም አውሮፕላን ሲያቀርቡ ቆይተዋል። 

የአውሮፕላን ነዳጅ ለማመላለስ ወደ ወደብ የሚሄዱ መኪኖች በጂቡቱ ወደብ በርካታ ቀናት እየቆሙ እንደሆነም ዋዜማ ሰምታለች።

መደበኛ በረራ ያላቸው የተለያዩ አየር መንገዶችን ጨምሮ በጣም በርካታ መደበኛ የበረራ ሰአት የሌላቸው በረራዎች የሃገር ውስጥም ሆነ የውጭም የበረራ ድርጅቶች ቦሌ ኢንተርናሽናል አየር ማረፊያን ነዳጅ ለመቅዳት ይጠቀሙበታል። ስምምንት ያልገቡ የበረራ ድርጅቶች እና በመደበኛ በረራ ለማያረጉት አየር መንገዶች የነዳጅ ዋጋ እስከ 1.4 ዶላር በሊትር ይከፍሉ ነበር። 

በባለፈው በጀት አመት ኢትዮጵያ 72.6 ቢልየን ብር ከፍላ አስገብታ ከነበረው 3.7 ሚልየን ቶን አጠቃላይ የንዳጅ ምርቶች ውስጥ የአውሮፕላን ነዳጅ ወደ 444,000 ቶን የሚጠጋ ሲሆን ወደ 8.4 ቢልየን ብር ወጪ ተደርጎበታል። 

ባለፈው በጀት አመት ወደ ሃገር ውስጥ የገባው የአውሮፕላን ነዳጅ በፊት ከነበረው አመት ጋር ሲነጻጸር በ 197,000 ቶን ዝቅ የሚል ሲሆን ይህም በኮቪድ ምክንያት በቀነሰው የአየር መንገዶች ገበያ ሳቢያ የተከሰተ መሆኑ ይታመናል።

በዚህኛው በጀት ሩብ አመት ግን (ሃምሌ 2013፣ ነሃሴ 2013  እና መስከረም 2014 ላይ) ሃገሪቷ ካስገባችው የአንድ ሚልየን ቶን ነዳጅ ውስጥ የአውሮፕላን ነዳጅ 12 በመቶ ነው። 

ሌሎች የነዳጅ ምርቶች ላይ መንግስት ድጎማ የሚያደርግ ሲሆን ለአውሮፕላን ነዳጅ ግን ምንም ድጎማ የለውም። 

ከባለፈው ታህሳስ ወር ጀምሮ ተግባራዊ የሆነው 25 በመቶ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በኋላ መንግስት በነዳጅ ምርቶች ላይ የሚያደርገው ድጎማ ከጥቂት ወራት በኋላ ከህዝብ ትራንፖርት ማመላለሻ መኪኖች በስተቀር እስከ ቀጣዩ አመት መጨረሻ ድረስ ያነሳል። 

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የሃገሪቱ ከተሞችና በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ከፍተኛ የነዳጅ እጥረት እየታየ ነው። ካለፈው ሳምንት ጀምሮም በተለይም የቤንዝን መኪኖች እስከ ግማሽ ቀን ድረስ በማደያዎች ለመሰለፍ እየተገደዱ ነው። 

በአዲስ አበባ የሚገኙ የነዳጅ አከፋፋይ ጣቢያዎች ከከተማዋ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር በትናትናው ዕለት በችግሩ ዙሪያ ምክክር ላይ ነበሩ። [ዋዜማ ራዲዮ]