Abebaw Ayalew- Deputy Director

ዋዜማ ራዲዮ- ከጥቂት ቀናት በፊት በርከት ያሉ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ቅርሶች እንደሆኑ የተነገረላቸውና ኢቤይ(eBay) በተሰኘ የበይነመረብ ገበያ ላይ ለሽያጭ መቅረባቸውን ተከትሎ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎችና በታዋቂ ግለሰቦች ቅርሶቹ ከትግራይ ክልል የተዘረፉ አድርጎ በማቅረብ ጉዳዩ ፖለቲካዊ እንዲሆን የተደረገውን ሙከራ የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን አውግዞታል።

በግብይት መድረኩ በግዕዝ ቋንቋ በመቃ-ብዕር የተጻፉ ሃይማኖታዊና ጥንታዊ የብራና ላይ ፅሁፎችና መስቀሎች ሲሆኑ በርካሽ በሆነ ዋጋ በበይነመረብ ገበያ ለሽያጭ ቀርበው ተመልክተናል።

ዋዜማ ለሽያጭ ቀረቡ ስለተባሉት ቅርሶች በኢትዮጵያ የቅርሶች የበላይ ጠባቂ ከሆነው የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን  ማብራሪያ እንዲሰጥበት ጠይቃለች።

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው (ረዳት ፕሮፌሰር) ከሰሞኑ በበይነመረብ በገበያ ላይ ወጡ የተባሉት ቅርሶች የመጀመሪያ ጊዜ ክስተት አለመሆኑንና በቀደሙት ጊዜያት በተለያዩ መንገዶች በመሰል የሽያጭ መድረኮች ለሽያጭ ሲቀርቡ ባለስልጣኑ ተከታትሎ ያስመለሳቸው በርካታ ቅርሶች ስለመኖራቸው አብራርተዋል፡፡

ይሁን እንጅ አሁን ቅርሶቹ በተለይም አንዳንድ አካለት በገለጹት መንገድ ከትግራይ ክልል ወይንም ሌላ አካባቢ ስለወሰዳቸው ማረጋገጫ አለመኖሩን የጠቀሱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ከዚህ በፊት ሆኖ የማያውቅ ክስተት አስመስሎ እንደ አዲስ ጉዳዩን በማጮህ የፖለቲካ ይዘት እንዲኖረው ተደርጎ እየቀረበ መሆኑ አግባብ አይደለም ብለዋል፡፡ 

በተጨማሪም ቅርሶቹ ከዚህ በፊት ከነበረው ልምድ በመነሳት ከኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከኤርትራ በተለይም ከሐማሴን፣ አካለ ጉዛይና ሌሎችም የኤርትራ አካባቢዎች የተወሰዱ ሊሆኑ የሚችልበት አጋጣሚ እንደሚኖር አበባው አክለው አብራርተዋል፡፡

ሆኖም ቅርሶቹ ከየትም የተወሰዱ ቢሆኑ እንደማንኛውም አይነት ጌጣጌጥ ወይንም ሸቀጥ እንዳሸጡና ባሉበት እንዲያቆሙና ከጨረታ ላይ እንዲወርዱ ሻጩን በማግባባት እንደሚጠይቁ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ በኩል ቅርሶቹ እንዳይሸጡ ጥያቄ ሲቀርብ ሻጩን ማስገደድ የማይቻል መሆኑን በመጥቀስ በዚህኛው መንገድ የማይቻል ከሆነ ከሚመለከታቸው አለማቀፍ ተቋማት ጋር በመነገገር  በመደበኛው ዲፕሎማሲያዊ  አካሄድ ወይንም ሌሎች አማራጮች  በማስተባበር እንሰራልን ብለዋል፡፡ 

ምንም እንኳ ቅርሶቹ ከጨረታ እንዲወርዱ ጥያቄ ቢቀርብም “ የቅርሱ ባለቤት እኔ ነኝ” ብሎ ሲጠየቅ በዕርግጥም የኢትዮጵያ ስለመሆናቸው ከጨረታ ሰነዱ ላይ ማረጋገጥ ስለማይቻል የማረጋገጫ ስራ ይሰራል ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡

በእነዚህ የገበያ መድረኮች ከዚህ በፊትም የቅርስ ዋጋ ያላቸው ሜዳሊያ ጭምር የሚሸጥባቸው የገበያ ቦታዎች መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ አበባው  ለገበያ የቀረቡ ቅርሶችን ከገበያ እንዲወርዱ ማድረግ ባለስልጣኑ ወትሮም የሚሰራው ስራ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

ከሰሞኑ የታየው የአንዳንድ መገናኛ ብዙሀን ዘገባና መደምደሚያ ጉዳዩን ፖለቲካዊ አጀንዳ ለማድረግ የተሞከረበት ነው ሲሉ አውግዘውታል።

‹‹የቅርስን ጉዳይ የፖለቲካ አጀንዳ ማድረግ አግባብ አይደለም›› ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ ከዚህ በፊት‹‹ ብዙ ቅርሶች እናስመልሰላን፤ ነገር ግን አስመልሰናል እወቁልን አካኪ ዘራፍ ብለን አናቅም›› ብለዋል፡፡

ባለስልጣኑ በዚህ አመት ብቻ በተደረገ ጥረት ለጨረታ ወጥተው የነበሩ ቅርሶቸን ጨረታ ይቁም ተብሎ ክርክር ሳይገባ በውጪ በሚኖሩ ሀገር ወዳዶች ተገዝተው ወደ አገርቤት እንዲመለሱ መደረጋቸውን አብራርተዋል፡፡

አቶ አበባው እንደገለጹት በሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት በሁለቱም ጦርነት ላይ በነበሩ አካለት የደረሰውን የቅርስ ጉዳት መጠን ለማወቅ ባለስልጣኑ ባካሄደው ጥናት በአማራና አፋር ክልሎች በርካታ ቅርሶች ተዘርፈዋል፡፡

አሁንም ባለስልጣኑ ከዚህ በፊት የነበረውን ቅርስ የማስመለስ ልምድ በመጠቀም መሰል ቅርሶች እንደሌላ ጌጣጌጥ ለሽያጭ እንዳይቀርቡ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመነጋገር እንደሚሰራና እንዲሁም ከኤርትራ መንግስትም ጋር በመሆን ጉዳዩ ክትትል ይደርግበታል ብለዋል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]