ዋዜማ ራዲዮ- በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን አሁንም ስርዓት አልበኝነት መቀጠሉንና ታጣቂዎች ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን መዝረፋቸውን ዋዜማ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።

በምዕራብ ወለጋ ጊሊሶ ወረዳ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አይራ ቅርንጫፍ ላይ ታጣቂዎች ዝርፊያ አካሂደው ስምንት መቶ ሰማንያ ስድስት ሺህ ብር መዝረፋቸው ታውቋል።

ታጣቂ ዘራፊዎቹ ወንጀሉን በሚፈፅሙበት ወቅት የአካባቢው ፖሊስ እርምጃ ለመውሰድ ዘገምተኛ መሆኑንም ጉዳዩን የሚያውቁ ይናገራሉ። ከቀናት በፊት የተዘረፈው የንግድ ባንክ አይራ ቅርንጫፍ ከከተማይቱ ፖሊስ ጣቢያ ብዙም ሳይርቅ የሚገኝ ቢሆንም ዝርፊያውን ለማስቆም መድረስ እንዳልቻለ ምንጮቻችን ጠቁመዋል።
ዘራፊዎቹም ማንነታቸውን ለመደበቅ ሙከራ እንኳ አለማድረጋቸውን እማኞች ያስረዳሉ።

ዘራፊዎቹ በባንኩ ሰራተኞች ላይ ድብደባ የፈፀሙ ሲሆን 886,000 ብር ወስደው ሄደዋል። የንግድ ባንክ አይራ ቅርንጫፍ ቀደም ሲል ስድስት መቶ ሺህ ብር ተዘርፎ ለሶስት ወራት ያህል ተዘግቶ የነበረ ቅርንጫፍ ነው።

በጥር ወር መጀመሪያ ላይ በኦሮሚያ በሁለት ቀናት ውስጥ አስራ ሰባት ባንኮች ተዘርፈው እንደነበር ይታወሳል።

በምዕራብ ወለጋ ግድያ ዝርፊያን ሰርዓት አልበኝነት በስፋት የሚታይ መሆኑን የሚናገሩት የአካባቢው ነዋሪዎች የመከላከያ ሰራዊት በኣአካባቢው ቢኖርም ተመጣጣኝ እርምጃ እየወሰደ አይደለም። ይልቁንም የመከላከያ ሰራዊቱ አባላት ላይ ታጣቂዎች ጥቃት ለማድረስ ተደጋጋሚ ሙከራ ሲያደርጉ ታይተዋል። በሰራዊቱና በታጣቂዎቹ መካከል ውጊያ ይቀሰቀሳል የሚል ስጋት እንዳላቸውም ነዋሪዎች ለዋዜማ ነግረዋል።


በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስተያየት እንዲስጥ ለማነጋገር እየሞከርን ነው። በሀገሪቱ የፀጥታ ሁኔታ ላይ ለጠቅላይ ሚንስትሩ የፕሬስ ሰክረታሪያት ከአምስት ቀናት በፊት ያቀረብነው ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አላገኘም። በሀገሪቱ የፀጥታ ጉዳይ ላይ ያሰናዳነውን የድምፅ ዘገባ ከታች ያድምጡት።

https://youtu.be/Bc7pTrvQAk0