Anti ISIS protest in Addis Ababa with victims picture in 2015

ዋዜማ ራዲዮ- ከአምስት ዓመት በፊት በአሸባሪዎች በሊቢያ በግፍ የተገደሉ 34 ኢትዮጵያውያንና ኤርትራዉያን አፅም ወደ ሀገራቸው ገብቶ በወግ እንዲቀበር ለማድረግ በመንግስት በኩል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ዋዜማ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያውያንና ኤርትራዉያኑ አፅም ከአንድ ወር በፊት የሊቢያ የሽግግር መንግስት በቁጥጥር ስር ባዋላቸው አሸባሪዎች ጥቆማ ስርት በተባለችው ከተማ የባህር ዳርቻ አቅራቢያ አንድ እርሻ አጠገብ መቃብሩን ማግኘት ተችሏል። የመቃብሩ ቦታ መገኘቱ እንደተሰማም የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ሊቢያ የልዑካን ቡድን ልኮ ከሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ተነጋግሯል።

የተገኘውን አፅም በዲ ኤን ኤ (DNA) ምርመራ የማጣራትና የመለየት ስራ እየተካሄደ ሲሆን ከሟች ቤተሰቦች መካከል ለዲ ኤን ኤ ምርመራ የተጠሩና ናሙናም የሰጡ መሆናቸውን ቤተሰቦች ነግረውናል።


የሟቾቹን አፅም የማምጣቱ ሂደት የሚያስፈልገውን ህጋዊ ሂደት ለማሟላትም በመንግስት በኩል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ያለን መረጃ ያመለክታል።
34 ኢትዮጵያውያንና ኤርትራዉያን አይ ኤስ በተባለው አሽባሪ ቡድን መገደላቸው ይታወሳል። ወጣቶቹ በስደት ወደ አውሮፓ በመጓዝ ላይ ነበሩ።

የዋዜማ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንዳንድ ቤተሰቦች ከሀዘኑ ተከትሎ በደረሰባቸው የስነልቦናና የጤና ቀውስ የአልጋ ቁራኛ እስከመሆን የደረሱ እንዳሉ ያስረዳሉ።

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ ለመፈፀም ቃል ከገቧቸው ጉዳዮች አንዱ ስደተኞችን ከስቃይ እስር ቤቶች ወደ ሀገራቸው መመለስና በሊቢያ የተገደሉትን ወጣቶች አፅም አፈላልጎ በወግ እንዲቀበሩ ማስቻል የሚል ይገኝበታል። [ዋዜማ ራዲዮ]