(ይህ እስከ ጠዋቱ ሁለት ሰዓት ድረስ ያጠናቀርነው ነው፣ በከተማዋ ያለውን ሁኔታ ተከታትለን ተጨማሪ ዘገባ እንደደረስን እናቀርባለን)

ዋዜማ ራዲዮ-በአዲስ አበባ  እሁድ ነሀሴ 15 (ዛሬ) ሊደረግ የታቀደውን ስልፍ ሊቀላቀሉ ይችላሉ ተብለው የተጠረጠሩ በርካታ ወጣቶች ሌሊቱን በፀጥታ ሀይሎች ሲታፈሱ አደሩ። በኮልፌ ቀራንዮ በአራዳ በቃሊቲ በልደታና በየካ ክፍለ ከተሞች በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ከቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ጀምሮ ከየመንገዱና ከመኖሪያ ቤታቸው ተፍሰው ተወስደዋል።

በጦር ሀይሎች አካባቢ ነዋሪ የሆኑ አንድ እናት የሳቸውን ልጅ ጨምሮ አራት ወጣቶች ከአካባቢያቸው በፖሊስ ተይዘው መወሰዳቸውን ለዋዜማ ተናግረዋል።

“ከምሽቱ ሶስት ሰዓት በድንገት በር አንኳኩተው ወስደውታል፣ ብርሀኑ የሚባል የጎረቤት ልጅ በጊዜ ከበራፍ ላይ ይዘውት ሲሄዱ አይቻለሁ” ብለዋል የ 59 ዓመት እማ-ወራ የሆኑት እናት። ልጃቸው የት ቦታ እንደታሰረ ባያውቁትም እኚህ እናት ቁርስ ስርተው ለልጃቸው ለመውሰድ በመንገድ ላይ ባሉበት ጊዜ ነበር ያናገርናቸው።

እሁድ ማለዳ ከተማው ያለውትሮው ጭር ብሎ ይታያል። በተለያዩ አካባቢዎች ታጣቂና ሲቪል የፀጥታ ሀይሎች በተለያዩ ተቋማት ግቢና ህንፃዎች ውስጥ በስውር በተጠንቀቅ መሽገዋል። ሜክሲኮ አካባቢ የፌደራል ፖሊስ አባላትን የጫኑ ሁለት ከባድ ተሸከርካሪዎች ወደከተማው ሲዘልቁ ታይተዋል። ስድስት ኪሎ አካባቢ አልሞ ተኳሽ ወታደሮችን የጫኑ ፒክ አፕ መኪናዎች ቅኝት እየደረጉ ነው። በቄራ መንገድ ገነት ሆቴል አካባቢ ከሀምሳ የሚበልጡ የፌደራል ፖሊሶች ቆመጥ ዱላ ይዘው በተጠንቀቅ ይታያሉ።