power stationበቅርቡ በኢትዮጵያ የተከሰተው መጠነ-ሰፊ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት መስተጓጎል በርካታ ጥያቄዎችን የሚያስነሳ ነው፡፡ ግዙፎቹ ግድቦች ከከባቢና ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የሚነሳባቸው ትችት እንደተጠበቀ ሆኖ በተለይ በቅርቡ የታየው የሃይል መስተጓጎል በሀገሪቱ ማምረቻ ዘርፍ እና በሚሌኒዬሙ ዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት ላይ ከባድ እክል ሊደቅን ይችላል፡፡

በተጠናቀቀው የአምስት ኣመት ዕቅድ የማምረቻ ዘርፉ በአስራ ሶስት በመቶ ቢያድግም ከአጠቃላይ ምርቱ ያለው ድርሻ ግን ከአራት በመቶ በታች ስለሆነ በመጭዎቹ አምስት ኣመታት አሁን ካለበት በሃያ ሰባት በመቶ ለማሳደግ ታቅዷል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የቱርክና ቻይናን ጨምሮ ሌሎች የእስያ አህጉር ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋል ንዋቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት ቢያሳዩም መንግስት አስተማማኝና በቂ ኤሌክትሪክ ሃይል ማቅረብ አለመቻሉ በኢንቨስትመንት ፍሰቱ ላይ እንቅፋት ፈጥሯል፡፡

በሌላ በኩል የሃይል መስተጓጎሉ በተከታታይ ድርቅ በምትጠቃዋ ሀገር በዝናብ ውሃ ላይ ጥገኛ የሆነ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ያለውን አስተማማኝነት እና አዋጭነት እንዲሁም አስተዳደራዊና ቴክኒካዊ ጉዳዮችን ሁሉ ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው፡፡ መቼም መጠነ-ሰፊ ድርቅ ዱብ ዕዳ ሊሆን ባይችልም መንግስት ግን የሃይል ዕጥረት ተከስቶ ሃይል ማመንጫዎች ስራ ወደማቆም ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት ቀደም ብሎ ዝግጅት ያደረገ አይመስልም፡፡

(ቻላቸው ታደሰ ዝርዝሩን ያሰማችኋል አድምጡት)

የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚንስቴር በቅርቡ ለተከሰተው መጠነ-ሰፊ የሃይል አቅርቦት መቋረጥ ምክንያት የሆነው በትልቁ ”ጣና በለስ”፣ “ግልገል ጊቤ አንድ” እና “ጊቤ ሁለት” የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መቆጣጠሪያ ላይ በተፈጠረ ብልሽት ሳቢያ እንደሆነ አስታውቋል፡፡ ምንም እንኳ ሚንስቴሩ የሰሞኑን የሃይል አቅርቦት መስተጓጎል በቀጥታ ከዝናብ እጥረቱ ጋር ባያያይዘውም ድርቁ ግን የግድቦችን ውሃ መጠን ስለቀነሰው ከፍተኛ የሃይል እጥረት ሊከሰት እንደሚችል መግለፁ ግን አልቀረም፡፡ በመላ ሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ስርጭት ወደ ፈረቃ ሊዞር እንደሆነም ተነግሯል፡፡

ድርቁ በኃይል ማመንጫ ግድቦች ላይ ስላስከተለው ጉዳት ከሞላ ጎደል ግልፅ ማረጋገጫ የሰጡት ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ በቅርቡ እንደተናገሩት መንግስት በሚገነባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ የሃይል አቅርቦት እጥረት ያጋጠመው በዝናብ እጥረቱ ምክንያት የ”ተከዜ”፣ “አዋሽ” እና “መልካ ዋካና” ሃይል ማመንጫ ግድቦች የሚይዙት ውሃ መጠን እጅጉን ስለቀነሰ እና ሃይል ሊያመነጩ የማይችሉበት ደረጃ ላይ ስለደረሱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ድርቁ በነባሮቹ አነስተኛ ኃይል ማመንጫዎችም ላይ ከባድ ጫና ፈጥሯል፡፡ ለአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ ሃይል የሚያቀርበው ባላንድ መቶ አርባ ሁለት ሜጋ ዋቱ (142) “ቆቃ” ሃይል ማመንጫም በዝናብ እጥረቱ ከፍተኛ ችግር ውስጥ መግባቱን ጠቅላይ ሚንስትሩ አረጋግጠዋል፡፡ በዘንድሮው ድርቅ ክፉኛ በተጎዳው አካባቢ የሚገኘው አዋሽ ወንዝም ጭራሹን ሊጠፋ እንደተቃረበ እየተነገረ ነው፡፡

እንግዲህ በዝናብ እጥረት አቅማቸው የተመናመነው ግድቦች ተመልሰው በቂ ሃይል ለማመንጨት ቀጣዩን የዝናብ ወቅት መጠበቅ ይኖርባቸዋል ማለት ነው፡፡

[አርጋው አሽኔ በኢትዮዽያ የአየር ፀባይ ትንበያ ዙሪያ ያሉ መረጃዎችንና የሀገሪቱን የተፈጥሮ አካባቢ ይዞታ የቃኘበትን ዘገባ ደግሞ እዚህ ማድመጥ ትችላላችሁ]

በስራ ላይ እንዳሉ የሚነገርላቸው አስራ አንድ ሃይል ማመንጫዎች ማለትም ጣና በለስ፣ ፊንጫ፣ ጢስ አባይ አንድ፣ ጢስ አባይ ሁለት፣ አዋሽ ሁለት፣ አዋሽ ሦስት፣ ቆቃ፣ ግልገል ጊቤ አንድ፣ ግልገል ጊቤ ሁለት፣ ተከዜ፣ መልካ ዋከና ሲሆኑ በድምሩ የሚያመነጩት እንድ ሺህ ስምንት መቶ ሰላሳ ሶስት (1,833) ሜጋ ዋት “ጊቤ ሶስት” ብቻውን እንደሚያመነጨው ከሚጠበቀው በታች ነው፡፡ በተለይ ቆቃ፣ አዋሽና ጢስ አባይ እያዳንዳቸው የሚያመነጩት ከአንድ መቶ ሜጋ ዋት በታች ነው፡፡ በግንባታ ላይ ወይም በዕቅድ ላይ ያሉት ደግሞ በአባይ ወንዝ ላይ የሚሰሩትን ታላቁ ህዳሴ ግድብ እና በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመኑ የተጠናቀቀውን ፊንጫ-አመርቲ-ነሼን ጨምሮ ሰባት ኃይል ማመንጫዎች አሉ፡፡ በጠቅላላው በመጪዎቹ ዓመታት ከሃያ ያላነሱ ኃይል ማመንጫዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡

ከብዙ መጓተት በኋላ ጊቤ ሦስት ሃይል ማመንጫ ከአስሩ ኃይል አመንጪ ተርባይኖች መካከል ሁለቱ ተርባይኖች በያዝነው ወር ሃይል ማመንጨት መጀመራቸው ተነግሯል፡፡ አንድ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዶላር (1.8 billion) ወጪ የፈሰሰበት እና አንድ ሺህ ስምንት መቶ ሰባ ሜጋ ዋት (1,870) ያመነጫል ተብሎ የሚጠበቀው ይኸው ግድበ ከአስራ ከአንድ ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በላይ ውሃ እንደሚያጠራቅም የተነገረለት ሲሆን ይህም እስካሁን በአፍሪካ ትልቁ እንደሆነ ተነግሮለታል፡፡ ያም ሆኖ ከወራት በፊት ውሃ ሙሌቱ ከተጀመረ ወዲህ ምን ያህል ውሃ እንዳጠራቀመ መረጃ ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ የዝናብ እጥረቱ በጊቤ ሦስት ላይ ያደረሰው ወቅታዊ ተፅዕኖ እስካሁን ይፋ ባይሆንም ቀሪዎቹ ተርባይኖች ግን እንደታሰበው በሚቀጥለው ዓመት ስራ ስለመጀመራቸው ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡Gibe 3 dam

 

በሚሌኒዬሙ ዘላቂ ልማት ግቦች ከተያዙት ዕቅዶች ውስጥ አንደኛው እኤአ በ2030 አስተማማኝ የኢነርጂ አቅርቦት ለሁሉም ዜጎች እንዲዳረስ ማድረግ ነው፡፡ ዓለም ባንክ አምና ያወጣው መረጃ እንደሚያሳው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት በየዓመቱ በሃያ አምስት በመቶ ይጨምራል፡፡ ሀገሪቱ ከዘጠና አራት በመቶ በላይ የሃይል አቅርቦቷን ከወንዞቿ የምታገኘው ሲሆን እንደ ዓለም ባንክ ግምት በጠቅላላው ከወንዝ ውሃ አርባ አምስት ሺህ (45,000) ሜጋ ዋት ማመንጨት ትችላለች፡፡ እስከ 2020ም ተጨማሪ አስራ ሁለት ሺህ ሜጋ ዋት ለማመንጨት እንደታቀደ መንግስት ይገልፃል፡፡

ሆኖም ከምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች ጋር ሲነፃፀር ኢትዮጵያ በቁጥር ብልጫ ያላቸው የሃይል ማመንጫ ግድቦች ብትገነባም እስካሁን በኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ራሷን አልቻለችም፡፡ እንዲያውም በዓለም ባንክ መረጃ መሰረት ለኤሌክትሪክ አቅርቦት ተደራሽ የሆነው ህዝቧ ሃያ ስድስት በመቶው ብቻ ነው፡፡ በአንፃሩ የሱዳን ሰላሳ ሁለት በመቶ ሲሆን ግብፅ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ማዳረስ ችላለች፡፡ ዓለም ባንክ እንደሚለው የኢትዮጵያ የነፍስ ወከፍ ዓመታዊ አማካይ የኤሌክትሪክ ፍጆታ ሃምሳ ሁለት ኪሎ ዋት ብቻ ሲሆን ኤርትራና ሱማሊያን ሳይጨምር በምስራቅ አፍሪካ አነስተኛው ነው፡፡

በጠቅላላው የዝናብ ዕጥረቱ ለመጠነ-ሰፊ ምግብ ዕጥረት ቀውስ ምክንያት መሆኑ አንሶ ሀገሪቱን ለከፋ የኃይል አቅርቦት ቀውስ እንዳይዳጋት ያሰጋል፡፡ መጠነ-ሰፊ የሃይል አቅርት ቀውስ ከተከሰተ “ሀገሪቱን የምስራቅ አፍሪካ ኃይል አቅራቢ ማዕክል (regional power house) አደርጋታለሁ” የሚለውን የመንግስት ትርክት ተጨባጭነትም ክፉኛ ጥያቄ ውስጥ ያስገባዋል፡፡ የግድብ ሃይል ማመንጫዎቸ ለድርቅ ክፉኛ ተጋላጭ መሆናቸው መንግስት በንፋስ፣ ጅኦተርማልና ፀሃይ አማራጭ ሃይል ማመንጫዎች ላይ በበለጠ ትኩረት እንዲደርግ የሚገፋፋ ሊሆን ይችላል፡፡

በሀገሪቱ አንጡራ ሃብት በተገነቡትና በሚገነቡት ግዙፍ ፕሮጄክቶች ላይ በተደጋጋሚ የሚከሰቱት ብልሽቶችና ሃይል የማመንጨት አቅም ውስንነቶችም ሃይል ማመንጫዎቹ አላስፈላጊ ብክነቶች እንደሚሆኑ ሲከራከሩ የነበሩትን አንዳንድ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ምሁራንን የሚያስታውስ ነው፡፡ ይሁንና ሀገሪቱ የገባችበት የሃይል አቅርቦት አጣብቂኝ መቼ እና እንዴት እንደሚፈታ አሁን በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም፡