[ዋዜማ ራዲዮ] የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጠንካራ ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎች ተጋርጠውትበታል። የዋዜማ ምንጮች እንድሚሉት ከአምስቱ የቦርዱ አባላት አንዱ የሆኑት ጌታሁን ካሳ (ዶ/ር) የሥራ መልቀቂያ ማቅረባቸው የውስጣዊ ፈተናዎቹ ትልቅ ማሳያ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል።


ዶ/ር ጌታሁን ትናንት ሰኞ፣ መስከረም 18 ቀን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የሥራ መልቀቂያቸውን ከማስገባታቸው በፊት ከአፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ጋራ ከረር ያለ ውይይት አድርገው እንደነበር ታውቋል። ምንጮቻችን የውይይቱን ይዘት ከመዘረዘር ቢቆጠቡም ዶ/ር ጌታሁን አባል በሆኑበት ቦርድ ውስጥ እየጎለበተ የመጣው የዓላማና የአመለካከት ልዩነት አንዱ እንደነበር አረጋግጠዋል።


የሕግ ባለሞያው ዶ/ር ጌታሁን፣ ቦርዱ እንደ አዲስ ሲዋቀር ከተሰየሙት አምስት አባላት አንዱ ናቸው። ከዚያ በፊት በአዲስ አበባ እና በመቀሌ ዩኒቨርሲቲዎች መምህርና ዲን፣ በትግራይ ክልል የፍትሕ ቢሮ ሃላፊ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኤግዚኪዩቲቭ ዳይሬክተር በመሆን መሥራታቸው በቦርዱ ድረ ገጽ ሰፍሯል።

ለቦርዱ አባላት እጩዎች በሚመለመሉበት ወቅት የዶ/ር ጌታሁን የህወሃት አባልነት ጉዳይ ተነሥቶ እንደነበርና አሁን አባል አይደሉም በሚል መታለፉን አንድ በሒደቱ የታሰተፉ ሰው ለዋዜማ ተናግረዋል። ዶ/ር ጌታሁን የቦርዱ አባል ከሆኑ በኋላ ከህወሃት በኩል ጫና ይደርግብኛል ሲሉ መደመጣቸውን አንድ በግል የሚያውቋቸው ሰው ነግረውናል።

አሁን የመልቀቂያ ጥያቄ ያቀረቡበት ምክንያት ከዚህ ጫና ይመንጭ ወይም በቦርዱ ውስጥ ባለው ሁኔታ ግልጽ አይደለም። በመልቀቂያ ደብዳቤያቸው የገለጹትን ምክንያት ለማረጋገጥ ባንችልም፣ አፈ ጉባኤው የመልቀቂያ ጥያቄውን እንደሚቀበሉት የዋዜማ ምንጮች ግምታቸውን አስቀምጠዋል

ዶ/ር ጌታሁን ካሳ አስተያየት እንዲሰጡ በስልክ ጠይቀናቸው መልቀቂያ ያስገቡት አስበውበት መሆኑን፣ በቦርዱ አሰራር ላይ ቅሬታ እንዳላቸው ይሁንና ቦርዱ ወሳኝ የህዝብ ተቋም በመሆኑ ገፅታውን የሚጎዳ ነገር መናገር እንደማይፈልጉ ነግረውናል።
“ቆይቼ በጉዳዩ ላይ ለህዝብ መግለጫ እሰጣለሁ ፣አሁን ምክንያቱን ማብራራት አልችልም ” ብለዋል።

ዋዜማ ሬዲዮ እንደተረዳችው ከሆነ ዶ/ር ጌታሁን ምርጫ ቦርዱ ባለፉት ወራት በወሰዳቸው ቁልፍ ሊባሉ በሚችሉ የፖሊሲ እና የአሠራር ውሳኔዎች ላይ ከአብዛኛው የቦርዱ አባላት የተለየ አቋም ወስደዋል። ከእነዚህም መካከል የኢሕአዴግ መፍረስ እና የትግራይ ክልል ምርጫ የሚጠቀሱ ናቸው። ዶ/ር ጌታሁን እና አንድ ሌላ የቦርዱ አባል፣ ቦርዱ የኢሕአዴግን መፍረስ ማጽደቅ የለበትም የሚል አቋም ወስደው ነበር። በወቅቱ የውሳኔ ሐሳቡን በመቃወም ከቀረቡት መከራከሪያዎች አንዱ የግንባሩ በዚህ ሁኔታ መፍረስ ለአገሪቱ አደጋ ያስከትላል የሚል ነበር። ጉዳዩ በድምጽ ብልጫ ውሳኔ ከተሰጠበት በኋላ በድጋሚ ውይይት ሳይደረግበት እንዳልቀረ ምንጮች ጥርጣሬያቸውን ይገልጻሉ።

የቦርዱ አባላት ለነሐሴ 2010 ታቅዶ የነበረው ምርጫ እንዲራዘም በጋራ ስምምነት መወሰናቸውን የዋዜማ ምንጮች ገልጸዋል። የህወሓት እና የትግራይ ክልላዊ መንግሥት በተናጠል በክልል ደረጃ ምርጫ ለማድረግ ያሳለፉት ውሳኔ ግን በቦርዱ ውስጥ ልዩነት የታየበት ነበር። ክልሎች የራሳቸውን ምርጫ ማካሄድ ይችላሉ የሚል አቋም ካራመዱት ሁለት የቦርዱ አባላት አንዱ ዶ/ር ጌታሁን እንደነበሩ የዋዜማ ምንጮች ያስቀምጣሉ። ቦርዱ ክልሎች የራሳቸውን ምርጫ ማደራጀትና ማካሔድ አይችሉም የሚል አቋም መውሰዱ የሚታወስ ነው።

ስለጉዳዩ አስተያየት የጠየቅናቸው የቦርዱ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ወሪት ሶልያና ሽመልስ “ቦርዱ በሚያደርጋቸው ዝርዝር ውይይት ይዘት ላይ ለጊዜው አስተያየት መስጠት አልችልም” ብለውናል።

የፖለቲካ ውጤታቸው ከፍተኛ በሆኑት በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የታተው ልዩነት ባለፉት ጥቂት ወራት የቦርዱን የሥራ ሂደቶች እሰከማጓተት መድረሱን የቦርዱ የሥራ ባልደረቦች ሳይታዘቡ አልቀሩም። ቀደም ሲል በፓርቲ ትስስራቸው በመመደባቸው በሥራቸው ላይ የፖለቲካ ውግንና ያሳያሉ ወይም የአቅም ማነስ አለባቸው የሚባሉ ሠራተኞችን ለማሰናበት እና አዳዲስ ሰራተኞችን ለመቅጠር የተያዘው እቅድ እስከ አሁን አለመፈጸሙን የቦርዱ ሠራተኞች ይገልጻሉ። የዋዜማ ምንጮች እንደሚሉት፣ የዚህ መጓተት ዋና ምክንያት የቦርዱ አባላት በሂደቱ ላይ ሙሉ በሙሉ አለመስማማታቸው ነው።

ቦርዱ ከውጭ የሚደርስበት ጫና ስራውን በአግባቡ እንዳያከናውን እንቅፋት መሆኑን የቦርዱን ሥራ በቅርብ የሚከታተሉ የዋዜማ ምንጮች ይናገራሉ። የተለያዩ የመንግሥት አካላት በሚጠበቀው መጠንና ፍጥነት ለቦርዱ ድጋፍ ለማድረግ ማቅማማት እንደሚያሳዩ በሁለት የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ያሉ የዋዜማ ምንጮች ተናግረዋል። ለቦርዱ ጽሕፈት ቤትና መሪዎች የሚደረገው የደኅንነት ጥበቃ ለቦርዱ አባላት አንድ የስጋት ምንጭ ነው። ቦርዱ ይህን ጉዳይ ለደኅንነቱ መሥሪያ ቤት ማሳወቁን የገለጹ ምንጮች “ችግሩ ሳይፈታ ቆይቷል” በማለት ስጋቱን ያጎላሉ።

ከሳምንታት በፊት ለምርጫ ቦርድ ሀላፊዋ ወሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ተመድበው ከነበሩ ጠባቂዎች አንዱ አጠራጣሪ እንቅስቃሴ ሲያደርግ በመታየቱ ለጊዜው ወደ ሌላ ቦታ እንዲቀየር ቢደረግም የአለቆቹን ትዕዛዝ ቸል በማለት ከነትጥቁ መኮብለሉንና በአሁኑ ስዓት በክልል ከተማ ተደብቆ እንደሚገኝ ዋዜማ ከደህንነት መስሪያቤቱ ምንጮች ሰምታለች።

በ2011 በተወካዮች ምክርቤት የተሰየሙት አምስቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አባላት ብርቱካ ሚደቅሳ (ሰብሳቢ)፣ ውብሸት አየል (ምክትል ሰብሳቤ)፣ አበራ ደገፋ (ዶ/ር) (አባል)፣ ብዙወርቅ ከተተ (አባል) እና ጌታሁን ካሳ (ዶ/ር) (አባል) ናቸው።[ዋዜማ ራዲዮ]

To Reach wazema Radio editors you can write wazemaradio@gmail.com