A view shows the military-run Metals and Engineering Corporation’s (METEC) office in Addis Ababa, Ethiopia December 3, 2018. Picture taken December 3, 2018. REUTERS/Tiksa Negeri

ዋዜማ ራዲዮ- ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ፣ ከስኳር ፕሮጀክቶችና በርካታ ኢንቨስትመንት ላይ ተሰማርቶ ለበርካታ ኪሳራ እና ሀገሪቱን ለከፋ ብክነት የዳረጋት የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) እንደ አዲስ ከተዋቀረና በአዲስ አመራር መመራት ከጀመረ በሁዋላ ኪሳራውን ቀንሶ ገቢን ለማግኘት በቢሊየን የሚያወጣ ገንዘብ ያስገኝልኛል ያላቸውን ንብረቶች በጨረታ አውጥቷል። የተወሰነው ጨረታ ገዥ ማግኘት ሳይችል የቀረ ሲሆን አዲስ የግብር ዕዳም ገጥሞታል።


      የዋዜማ ምንጮች እንደነገሩን ከሆነ ኮርፖሬሽኑ በአንደኛ ጨረታ ላይ ለመሸጥ አስቦ ያወጣው የተከማቹ በርካታ ውድ ብረቶችን፣ ተሽከርካሪዎችን ሌሎች ንብረቶቹን ነው። ከዚህ ጨረታ ሜቴክ ቢያንስ ከአንድ ቢሊየን ብር በላይ ገቢን ለማግኘት አቅዶ ነበር።ሆኖም ይህ ጨረታ አሸናፊ በማጣቱ ለሁለተኛ ዙር ሊወጣ መሆኑን ሰምተናል። የጨረታ ተሳታፊ የጠፋውም በዚህ ውስጥ የወጡት ንብረቶች ዋጋቸው የማይቀመስ በመሆኑ በቀላሉ ተጫራች ባለመገኘቱ መሆኑንም ምንጫችን ነግረውናል። ሜቴክ በሌላ ጨረታ ያወጣቸው የመኪና ባትሪ ፣ፕላስቲኮችና መለስተኛ ንብረቶቹ የ15 ሚሊየን ብር ገዥ አግኝተዋል። በዚህ ጨረታ 17 አሸናፊዎች መገኘታቸውንም ሰምተናል።


      የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በቀጣይ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለማግኘት ተከታታይ ጨረታዎችን ያወጣል።በተለያየ ጊዜ ገዝቶ ያከማቻቸው ተሽከርካሪዎች ሆቴሎችም ለሽያጭ ይቀርባሉ። የዋዜማ ምንጮች እንደጠቆሙን ከሆነም በኮርፖሬሽኑ የቀድሞ አመራሮች ተገዝተው የነበሩ ነገር ግን በቂ ሰነድ ያልነበራቸው ሆቴሎችን ጨምሮ ተጨማሪ የሜቴክ ንብረቶች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተገኙ ነው። ስለ ንብረቶቹ ግልጽ ያለ መረጃ ግን ለሰራተኞችም ቢሆን በዝርዝር የተነገረ ነገር የለም። ሆኖም ከተቋሙ ተልእኮ ውጭ ያሉት ግን በጨረታ እንደሚሸጡ ማወቅ ተችሏል።


      በሌላ በኩል ኮርፖሬሽኑ ገዝቶት ከነበረው ኢምፔሪያ ሆቴል ያልተከፈለ 32 ሚሊየን ግብር አለኝ ብሎ የገቢዎች ሚኒስቴር ለሜቴክ ደብዳቤ ጽፎለታለ። ሚኒስቴሩ በአንድ ወር ውስጥ ክፍያው ካልተፈጸመልኝም ሆቴሉን ለእዳ ማስመለሻ እንደሚያውለውም በደብዳቤው ላይ ጠቅሷል። የ32 ሚሊየን ብሩ የኢምፔሪያል ሆቴል እዳ ሊመጣ የቻለው ኢምፔሪያል ሆቴል ለኤምያስ አመልጋ ተሽጦ ሜቴክ ጋር ከመድረሱ በፊት የሆቴሉ ባለቤት የነበሩት ግለሰብ ለሆቴል ዘርፍ የቀረጥ ነጻ መብት ነበራቸው።

ሆኖም የሆቴሉ ባለቤትነት ወደ ሌላ ሲሸጋገር የገዛው አካል የቀረጥ ነጻ መብት ከሌለው ለገባው እቃ ግብሩን ይከፍላል። ሜቴክም የ32 ሚሊየን እዳም የመጣበትም በዚሁ መንገድ ነው።በገዳዩ ላይም የሜቴክና የገቢዎች ሚኒስቴር ሀላፊዎች ተወያይተው ከስምምነት ሊደርሱ ይችላሉ ተብሏል። ይህ ጉዳይ ሲያልቅም ኢምፔሪያል ሆቴል ከሌሎች ሆቴሎች ጋር ለሀብት ማሰባሰቢያ ለጨረታ የሚቀርብ ይሆናል።


      በ2002 አ.ም የተቋቋመው ሜቴክ ፣ የ10 ቢሊየን ብር ካፒታል ይኖረዋል ተብሎ የተቋቋመ ነው። ከአመታት በሁዋላ በኪሳራና በብክነት ተዘፍቆ በስሩ የነበሩ የተወሰኑ ኢንዱስትሪዎችን ለመከላከያ ሚኒስቴር አስረክቦ የሲቪል ምርቶችን ብቻ እንዲያመርት ተወስኖበት ወደ ስራ ተገብቷል። [ዝርዝር የዋዜማ ዘገባዎችን ከታች ያዳምጡ] 

https://youtu.be/CwPtiVkxVuQ