ዋዜማ ራዲዮ- መንግስት በብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ውስጥ ተፈፅሟል የተባለውን ከፍተኛ ሙስና ማጣራት ከጀመረ ወራት ተቆጥረዋል። በማጣራቱ ሂደት በርካታ መረጃዎች ተሰብስበዋል። ይሁንና ከመስሪያ ቤቱ የተሰወሩ፣ ያልተሟሉና የተጭበረበሩ መረጃዎችን የማጣራቱ ስራ አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል።

ዋዜማ ከምርመራው ጋር ቅርበት ካላቸው ምንጮች እንደሰማቸው የሙስና ስንሰለቱ ከፖለቲካ አመራሩ ከግል ባለሀብቶችና በውጪ ሀገር ካሉ ኩባንያዎች ጋር የተያያዘና እጅግ ፈታኝ ነበር።
ባለፉት ወራት ከሜቴክ መካከለኛ አመራሮች ከባለሙያዎችና ጉዳዩን ከሚያውቁ ጋር የመርማሪ ቡድኑ አባላት እየተገናኙ መረጃ ሲያሰባስቡ ነበር። ይሁንና መቀሌ የመሸጉት የሜቴክ አመራሮች የደህንነት መስሪያቤት አባላትና እስካሁንም በሜቴክ ውስጥ እየሰሩ ያሉ ሀላፊዎች በመመሳጠርና መረጃ በማዛበት ምርመራው እንዳይሳካ ለማድረግ ሞክረዋል። መረጃ በማሸሽም ምርመራውን ለማስተጓጎል ሞክረዋል።

እንደመረጃ ምንጮቻችን ለምርመራው እጅግ ጠቃሚ መረጃ በመስጠት ትብብር ያደረጉም አሉ። በምርመራው ሂደት የተባበሩት ላይ የግድያ ዛቻና ማስፈራራት የደረሰባቸውም እንደነበሩ ተሰምቷል።
አሁን ከሀገር ውጪ የሚገኙና ለምርመራው እጅግ ጠቃሚ መረጃ ያቀበሉ ግለሰብ እንደሚሉት የሜቴክ ጥፋቶች በሁለት ይከፈላሉ። አንዱ የማያውቁትንና የማይችሉትን ስራ ለመስራት በመሞከር ሳይሳካ ሲቀር ደግሞ ከማረምና ከማቆም ይልቅ እንደገና አዲስስ ህተት በመደመር የተፈፀመ ወንጀል ነው። ሁለተኛው ጥፋት ሆነ ተብሎ በተደራጀና በተቀነባበረ መንገድ የህዝብ ሀብትን በዘመድ አዝማድ እየዘረፉ የማሸሽ ወንጀል ተሰርቷል ይላሉ።

ሜቴክ ውስጥ ውድ ህይወታቸውን መስዋዕት አድርገው ለሀገራቸው የለፉና ሽልማት የሚገባቸው ሰዎች አሉ። አንዳንዶች ሙስና ሲፈፀም “ለምን?”  ብለው ስለጠየቁ ከስራ የተባረሩና የደረሱበት ያልታወቀም አሉ።
ከሕወሀት አመራሮች መካከል ሜቴክ የህዳሴው ግድብ እንዳይሰጠው በሌሎች ስራዎቹም ቁጥጥር እንዲደረግበት የጠየቁ እንደ ከሀዲ ተቆጥረው ተዋክበዋል። በተለይ ከመለስ ዜናዊ ሞት በኋላ ሜቴክ በሀገሪቱ ውስጥ ያሻውን ማድረግ የሚችል ተቋም በመሆኑ ሀገሪቱ ልትሸከመው ከምትችለው በላይ ዕዳ ውስጥ ከቷታል።

የሜቴክ ችግሮች የቀረበላቸው የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ኋይለማርያም ደሳለኝ ጉዳዩ አንስተው ለመጠቅ እንኳን አልደፈሩም የሚሉት ምንጫችን ያቀረብንላቸውን መረጃ ሂዱና ለፍትህ ሚኒስቴር አቅርቡ፣ ሜቴክ የመከላከያ ተቋም ስለሆነ ገመናችንን አደባባይ ማውጣት ተገቢ አይደለም የሚል ምላሽ ተሰጥቶናል ብለዋል።

እስከ መስከረም ወር መጨረሻ በሜቴክ ውስጥ በሀላፊነት ሲሰሩ እንደነበረና አሁን ከምርመራው ጋር በተያያዘ ወደ ውጪ ሀገር መውጣቻውን የነገሩን ምንጫችን ከቀናት በፊት የተጀመረው አንዳንድ የሜቴክ አመራሮችንና ስራተኞችን የማሰር ሂደት የተሟላ መረጃ ለመሰብሰብና ምርመራውን የተሟላ ለማድረግ አስፈላጊ እርምጃ ነው።
የታሰሩት ሁሉ ወንጀለኛ ናቸው ማለት ላይሆን ይችላል፣ ይሁንና መረጃ የማሸሽ ሁኔታ ስላለ ይህን ለመግታት ታስቦ ይመስለኛል ብለዋል።
መቀሌ የተደበቁት የሜቴክ አመራሮችን ህግ ፊት ማቅረብ አይቀሬ ነው ያሉት ግለሰቡ በጉዳዩ ላይ ከትግራይ ክልል መንግስት ጋር ውይይት መደረጉን እንደሚያውቁ ነግረውናል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ እርምጃ ከመወሰዱ በፊት መረጃ እንዲሰባሰብ ባዘዙት መሰረት ለወራት መረጃዎቹ ሲዘጋጁ ነበር። በቅርቡ የተጠናቀረው መረጃ ሲደርሳቸውና በጉዳይ ላይ ገለፃ ሲደረግላቸው “አሁን ይህን ጉድ ለህዝቡ ምን ብለን ልንነግረው ነው?”  ሲሉ መደመጣቸውን ያስታውሳሉ።