PHOTO from SM

ዋዜማ ራዲዮ- በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ማንነትን መሰረት አድርጎ የሚፈፀም ግድያ፣ ማፈናቀልና እስራት ትኩረት እንዲሰጠው እንዲሁም በተለያዩ ምክንያች እየታሰሩ የሚገኙ ጋዜጠኞች በአፋጣኝፍትህ የማግኘት መብታቸው እንዲጠብቀላቸው ሲል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ ) ታህሳስ 27 ቀን 2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አሳስቧል፡፡

ኢሰመጉ ዕሮብ አመሻሹ ላይ ባወጣው መግለጫ ከመስከረም 2014 ዓ.ም ጀምሮ ማንነትን መሰረት ያረገ ጥቃት በኦሮሚያ ክልል በርካታ አካባቢዎች መከሰቱን በመጥቀስ ለዚህም መንግስት አስፈላውን ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡

ለአብነትም ታሳስ 23 ቀን 2014 ዓ.ም በሆሮ ጉድሩ ዞን ጃርቲ ወረዳ በኦነግ ሸኔ ማንነትን መሰረት ባደረገ ጥቃት ገበያ ላይ አምስት ንጹሃንን እንዲሁም ታህሳስ 24 ቀን 2014 ዓ.ም ጃርቲ ወረዳ ሆሮ ሎጌ በተባለ የገበያ ቦታ አንዲት ሴት በአሰቃቂ ሁኔታነ ተገድላ አስክሬኗም እንዳልተነሳ መረጃ እንደደረሰው አስታውቋል፡፡

በምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦ ወረዳ መንቃታ በተባለ ቀበሌ ታሳስ 11 ቀን 2014 ዓ.ም ሌሊት ላይ በስፍራው ለበርካታ ዓመታት ነዋሪ የነበሩ 10 የአማራ ተወላጆች ከአንድ ቤት ሶስት ሰዎችን ጨምሮ ግድያ ስለመፈጸሙም ሪፖርቱ ጠቅሷል።፡፡

ታህሳስ 14 ቀን 2014 ዓ.ም ጃርቲ ወረዳ ሰንባ ጨፌ ቀበሌ ስብሰባ ላይ የተገኙ 7 የአማራ ተወላጆችን እንዲሁም ታህሳስ 22 ቀን 2014 ዓ.ም አሞሩ ወረዳ ጃባ ጀቦን ቀበሌ 5 ሚሊሻዎች ለስብሰባ ተጠርተው በሄዱበት ተደብድበው መታሰራቸውን አስታውቋል፡፡

በዚሁ ቀን በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ከተማ እና አካባቢው በሚኖሩ ዜጎች ላይ በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በተፈፀመ ጥቃት ቁጥራቸው ያልተገለጸ በርካታ ንጹሃን ዜጎች ስለመገደላቸውና በከተማዋ የሚገኙ የባለሀብቶች ንብረት ላይ ዘረፋ መፈፀሙን መረጃ ደርሶኛል ብሏል፡

መግለጫው እንደሚያሳው ከመስከረም 27 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል በምእራብ ሸዋ ዞን ጅባት ወረዳ ዳርጌ ቀበሌ (አዳኒ፣ ኡኩ፣ መሩሃ፣ ገጃ፣ ሬጂ እና ኮምቦልቾ መንደሮች) ነዋሪ የነበሩ ዜጎች ተፈናቅለው መኖሪያ ቤቶቻቸው ስለመቃጠሉና ግለሰቦች ስለመገደላቸው እንዲሁም ለመሰብሰብ የደረሰ በርካታ ሰብል ሳይሰበሰብ በእርሻ ላይ ተበላሽቷል፡፡

ኢሰመጉ በመግለጫው ሀገራዊ፣ አህጉራዊ እንዲሁም ዓለምአቀፍ ህግጋትን በተፃረረ መልኩ ክቡር በሆነው የሰው ልጅህይወት ላይ እየደረሰ ያለውን አሳዛኝ ድርጊት በማውገዝ፣ ጥቃቱን ተከትሎ ንብረታቸው የወደመባቸው እንዲሁም ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ጉዳይ ያሳስበኛል ብሏል፡፡

በተጨማሪም በተለያዩ ምክንያቶች እየታሰሩ የሚገኙ ጋዜጠኞች አፋጣኝ ፍትህ የማግኘት መብታቸው እንዲሁም ሰብዓዊ አያያዛቸውን በተመለከተ ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ አቅርቧል፡፡

መንግስት ድርጊቱን የሚፈፅሙ አካላትን በአግባቡ አጣርቶ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ፤ ለዚህ ተደጋጋሚ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ፈጣን፣ ተጨባጭ እና ዘላቂ መፍትሄ ማፈላለጉ ላይ በብርቱ እንዲሰራ ጠይቋል፡፡

በተጨማሪም ዜጎች፣ የማህበረሰብ አንቂዎች፣ መገናኛብዙሃን፣ ሲቪክ ማህበራት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሀይማኖት ተቋማት እና የሀገር ሽማግሌዎች ይህ ጉዳይ እልባት እንዲያገኝ የሚጠበቅባቸውን እገዛ እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ላይ ውትወታ እንዲያደርጉ ኢሰመጉ ጥሪውን ጥሪ አቅርቧል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]