ዋዜማ ራዲዮ- የተለያዩ የኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጭ የግል ማህበሮች ስራ አስኪያጆቻቸው እና ወኪሎቻቸው ሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ በዱቤ ለሚሸጥላቸው ሲሚንቶ በአባይ ባንክ ስም የተዘጋጀ ሀሰተኛ የባንክ የዋስትና ሰነድ በማዘጋጀት እና በማስገባት በፋብሪካው ላይ ኪሳራ አድርሰዋል ተብሏል፡፡

ይህን ተከትሎም በጥቅም በመመሳጠር እና የፋብሪካውን መመርያ በመጣስ ሀሰተኛ ሰነዱ እንዲያልፍ አድርገዋል ተብለው የተጠረጠሩት የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ዋና ስራ አስኪያጅ አካሉ ገ/ህይወት፣ የማርኬቲንግ ስራ ሂደት ሀላፊ የሆኑትን ፍቅሬ በቀለ፣ የኮርፖሬት ፋይናንስ ስራ ሂደት ሀላፊ የሆኑትን ጌቱ አጎናፍር እና በአዲስ አበባ የኮርፖሬት ፋይናንስ ቡድን መሪ ተወካይ የሆኑትን ጌታቸው ቶልቻን የፌደራል ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሏቸዋል፡፡

ጉዳያቸውንም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡

ሙገር ሲሚንቶ የባንክ የዋስትና ደብዳቤ ለሚያቀርቡ የኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጭ ማህበራት እና ድርጅቶች በዱቤ ሲሚንቶ የሚያቀርብበት አሰራር እንዳለው የተገለፀ ሲሆን የ7 ስራ ተቋራጭ ማህበራት ስራ አስኪያጆችን እና ወኪሎቻቸውም በአባይ ባንክ ስም የተሰራ ሀሰተኛ ሰነድ በማቅረብ እያንዳንዳቸው የተለያየ መጠን ያለው ሲሚንቶ ወስደው ሳይከፍሉ ቀርተዋል በሚል ነው የተጠረጠሩት፡፡

በጥቅሉም 88 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ በፋብሪካው ላይ እንዲደርስ አድርገዋል ተብሏል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]