Diaspora Reception event in Addis Ababa , January 2022- FILE
  • ዲያስፖራው በዘጠኝ ወር 3.8 ቢሊዮን ዶላር በባንክ ልኳል

ዋዜማ ራዲዮ- በባለፈው የገና በዓል የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባቀረቡት “1 ሚሊዮን ዲያስፖራ ወደ አገር ቤት” ጥሪ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎችና የኢትዮጵያ ወዳጆች 119 ሺሕ 56 ብቻ እንደነበር ዋዜማ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሪፖርት ተመልክታለች፡፡

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የላከውን የዘጠኝ ወር ሪፐርት አፈጻጸም ዋዜማ የተመለከትች ሲሆን፣ ሪፖርቱ ለቋሚ ኮሚቴው ይቅረብ እንጅ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አፈጻጸም ግምገማ ላይ ለምክር ቤቱ አልቀረበም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዲያስፖራው ማኅበረሰብ ባቀረቡት ጥሪ አንድ ሚሊዮን ኢትየጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ ተብሎ ቢጠበቅም ቁጥሩ የተጠበቀውን ያክል መሆን አልቻለም፡፡ ይሁን እንጅ ዋዜማ የተመለከተችው ውጭ ጉዳይ ሪፖርት ቁጥሩ ያነሰበትን ምክንያት ለቋሚ ኮሚቴው ባቀረበው አፈጻጸም ላይ አልተጠቀሰም፡፡

አገራዊ ጥሪውን በመቀበል ወደ አገር ቤት የመጡ የዳያስፖራ አባላት 114 ሚሊዮን 189 ሺህ 780 ብር በአይነትና በጥሬ ገንዘብ ለተፈናቀሉ ዜጎች በተለያዩ ቦታዎች (በተለይም በአማራና በአፋር ክልሎች) ሰጥተዋል ብሏል፡፡ እንዲሁም 98 ሚሊዮን 805 ሺህ 768 ብር የሚገመት መድሀኒት እና የህክምና ግብዓቶች ወደ ሀገር ቤት ይዞ በመምጣት ለጤና ሚኒስቴር ማስረከባቸውን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

በተጨማሪም በአገር ቤት የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት 49.6 ሚሊዮን ብር ማሰባሰብ የተቻለ ሲሆን፣ ለበጎ አገልግሎት ስራዎች ደግሞ 1 ሚሊዮን 930 ሺህ 560 ብር በመለገስ በአጠቃላይ 264 ሚሊዮን 526 ሺህ 108 ብር ሀብት ተስብስቧል፡፡ 

ከአገር  ቤት ጉዞው ጋር በተያያዘ ከዳያስፖራው የተገኘውን የሀብት ፍሰት በአንድ ወር ውስጥ 7 ሚሊዮን 672 ሺህ 419 ዶላር እና 172 ሺህ 877 ዩሮ ከውጭ የተላለፈ መሆኑን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማረጋጋጡን መሥሪያ ቤቱ በሪፖርቱ አብራርቷል፡፡ 

በዳያስፖራው በሁለት ወር (ታህሳስ እና ጥር ወር 2014 ዓ/ም) አካውንት በመክፈት 1 ሚሊዮን 480 ሺህ 136 ዶላር ተቀማጭ ያደረገ  ሲሆን፣ ይህም በአምስት ወር ከሀምሌ 2013 ዓ/ም እስከ ህዳር ወር 2014 ዓ/ም በዳያስፖራው በተከፈተው አካውንት ጋር ተመሳሳይነት ስላለው የሀብት ፍሰቱ በሶስት እጥፍ መጨመሩን ያሳያል ተብሏል፡፡ 

በሌላ በኩል አጠቃላይ በውጪ የሚኖረው ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ (ዲያስፖራው) በዘጠኝ ወር 3.8 ቢሊዮን ዶላር በሕጋዊ መንገድ ወይም በኢትዮጵያ ባንኮችና የሕጋዊ የገንዘብ አስተላላፊዎች ፕላትፎርሞች በኩል ወደ ኢትዮጵያ መላኩን ዋዜማ ከሪፖርቱ ተመልከታለች፡፡

የውጭ ምንዛሬ ፍሰት እንዲጨምር ዳያስፖራው ገንዘቡን  በሕጋዊ መንገድ ወደ አገር ቤት እንዲልክ ክትትልና ድጋፍና ክትትል በማድረግ በዘጠኝ ወር 3 ቢሊዮን ዶላር ለማስገባት ታቅዶ፣ 3.8 ቢሊዮን ዶላር ወደ አገር ቤት መላኩን ከብሔራዊ ባንክ መረጃ ማግኘቱን ለቋሚቴው በላከው ሪፖርት ጠቅሷል፡፡

ዳያስፖራው የውጭ ምንዛሬ አካውንት እንዲከፍት ማድረግ በኩል፣ ከሀምሌ 1 ቀን 2013 እስከ መጋቢት 30 ቀን 2014 ዓ.ም 5 ሺህ 250 የዳያስፖራ አባላት በአገር ውስጥ ባሉ ባንኮች የውጭ ምንዛሬ አካውንት እንዲከፍቱ በማስቻል 6.3 ሚሊዮን ዶላር ተቀማጭ እንዲያደርጉ ታቅዶ 5 ሺህ 965 የዳያስፖራ አባላት የውጭ ምንዛሬ አካውንት ከፍተው 5 ሚሊዮን ዶላር ተቀማጭ አድርገዋል፡፡ አፈጻጸሙ ሲታይ አካውንት ከከፈቱ የዳያስፖራ አባላት 114 በመቶ ሲሆን፣ ተቀማጭ ከሆነው ዶላር አንጻር 79 በመቶ ነው፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]