Gonder Protest July 31
Gonder Protest July 31, 2016

ዋዜማ ራዲዮ- የመንግስት ሀይሎች በጎንደር የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎችን ትጥቅ ለማስፈታት መንቀሳቀሳቸውን ተከትሎ በአካባቢው ግጭት መከሰቱንና ውጥረት መንገሱን ከየአካባቢው ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ለዋዜማ ገልፀዋል።
ህብረተሰቡ በመንግሥት የወጣበትን መሳሪያ የማስረከብና ትጥቅ የመፍታት ትዕዛዝን ባለመቀበሉ በተለይም በሁመራና በወገራ ነዋሪዎች ላይ ሀይል የተቀላቀለበት እርምጃዎች በመንግስት ሀይሎች እየተወሰደበት መሆኑን ታማኝ የዋዜማ ምንጮች ገልፀዋል ። በርካታ ስዎችም ተይዘው ታስረዋል።
ከወራት በፊት በጎንደር አካባቢዎች በተነሳው የመብት ጥያቄዎች እና በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ ጉዳዩን አባብሰዋል የተባሉ ግለሰቦች በእስር የሚገኙ ሲሆን በተለይም በወቅቱ በተነሳው አመፅ ምክንያት በትግራይ ተወላጆች ህይወት እና ንብረት ላይ የተለየ ጥቃት ተፈፅሟል በሚል የትግራይ ክልልና የማዕከላዊ መንግስቱ ፓለቲከኞች በአደባባይ መናገራቸውን ተከትሎ በጎንደር ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር በመደረግ ላይ ነው።
በሁመራ፣ በወልቃይትና በጎርጎራ ነዋሪዎች ላይ ከሰኞ ዕለት ጀምሮ በመንግሥት የፀጥታ ሀይሎች የተጀመረው ትጥቅ የማስፈታት ዘመቻው ከሌሎቹ የጎንደር አካባቢዎች የከፋ መሆኑን ምንጮቹ ቢናገሩም ፍተሻውና ማስፈራሪያው በሁሉም የጎንደር ወረዳዎች እና ዞኖች ተግባራዊ እየተደረገ ነው ሲሉ ገልፀዋል ።
በጎንደር የተለያዩ አካባቢዎች ህብረተሰቡን ትጥቅ የማስፈታት ዘመቻው የሚመራው በማዕከላዊ መንግሥቱ በተላኩ የመከላከያ ሀይሎች መሆኑን የጠቀሱት የዋዜማ ምንጮች የክልሉ ታጣቂ ሀይል በስራው ላይ አለመሰማራቱንና ምንም አይነት ሚና እንደሌለው ጠቅሰዋል ።
ከቀናት በፊት በአካባቢው በተጀመረው በዚህ የትጥቅ ማስፈታት ዘመቻ ከህብረተሰቡ የእምቢታ የአፀፋ ጥቃት በአንዳንድ አካባቢዎች መፈፀሙን እማኞች ሲናገሩ፣ ስለደረሰው ጉዳት ዝርዝር መረጃ አላገኘንም።