Mengistu Hailemariam 1986-FILE

ዋዜማ ራዲዮ- የዚምባብዌ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አምባሳደር ፍሬድሪክ ሻቫ አገራቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ከጠየቀ የቀድሞውን የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃ/ማርያምን አሳልፋ ለመስጠት ፈቃደኛ ልትሆን እንደምትችል ፍንጭ እንደሰጡ ቪኦኤ ዘግቧል። 

የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር የኢትዮጵያ መንግሥት ለዚምባብዌ ኮሎኔል መንግሥቱ ተላልፈው እንዲሰጡት ከጠየቀ፣ ዚምባብዌ ትክክለኛውን አካሄድ ተከትላ ምላሽ ትሰጣለች በማለት ከዜና አውታሩ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል። 

በቀድሞው ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ ሥልጣን ዘመን ግን የዚምባብዌ ባለሥልጣናት አገራቸው ለኮሎኔል መንግሥቱ በዓለማቀፍ ሕግ መሠረት ጥገኝነት መስጠቷን በመግለጽ፣ ለኢትዮጵያ አሳልፋ እንደማትሰጣቸው መግለጣቸው ይታወሳል።

ኢሕአዴግ-መራሹ መንግሥት በ1980ዎቹ የቀይ ሽብር ወንጀሎችን ለመመርመር ያቋቋመው ልዩ ዓቃቤ ሕግ በቀድሞው ፕሬዝዳንት ኮሎኔል መንግሥቱ ላይ የዘር ማጥፋት ክስ መስርቶባቸው፣ ከ14 ዓመት በፊት በሌሉበት የሞት ፍርድ እንደፈረደባቸው ይታወሳል። 

ከእሳቸው ጋር ተከሰው የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው የቀድሞው መንግሥት ከፍተኛ ሲቪል እና ወታደራዊ ባለሥልጣናት ግን የሞት ፍርዱ ወደ እድሜ ልክ እስራት ከተቀየረላቸው እና 20 ዓመታት ከታሰሩ በኋላ፣ በመንግሥት ውሳኔ ከእስር መፈታታቸው ይታወሳል።

የዚምባቢዌ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፍሬድሪክ ሻቫ ለቪኦኤ ይህን የተናገሩት፣ በሩዋንዳው የዘር ማጥፋት ወንጀል ዓለማቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት የፈረደበት አንድ ሩዋንዳዊ ግለሰብ፣ ለበርካታ ዓመታት በዚምባብዌ ከኖረ በኋላ፣ ከ16 ዓመታት በፊት እዚያው ሕይወቱ እንዳለፈ የተመድ መርማሪዎች ማረጋገጣቸውን ተከትሎ ነው። 

ሆኖም የኢትዮጵያው የቀድሞ ፕሬዝዳንት መንግሥቱ በግልጽ ማንም በሚያውቀው ሁኔታ ወደ ዚምባብዌ የመግባታቸው ጉዳይ ፈጽሞ ከሩዋንዳዊው ወንጀለኛ ጋር እንደማይገናኝ ሚንስትሩ ገልጸዋል። ሚንስትሩ ጨምረውም፣ ኮሎኔል መንግሥቱ በዚምባብዌ መኖራቸው ከጀርባው አንዳችም ሴራ የለበትም ብለዋል። [ዋዜማ ራዲዮ]