ዋዜማ ራዲዮ- የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በኢትዮጵያ መድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ የቀድሞ ሀላፊዎች እና ሰራተኞች ላይ ክስ መስርቷል፡፡
አቃቤ ህግ ሁለት የክስ መዝገቦችን ትናንት ግንቦት 12 ከሰዓት በኋላ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት የከፈተ ቢሆንም መደበኛ የስራ ሰዓት መገባደድን እና ተከሳሾ ያለ ጠበቃ መቅረባቸውን ተከትሎ ችሎቱ ጉዳዩን ለዛሬ ግንቦት 13 አሳድሮት ነበር፡፡


ዛሬ ግንቦት 13 ከሰዓት በኋላ ተሰይሞም የክሱን ዝርዝር በቁጥጥር ስር ውለው ችሎት ለቀረቡት ተከሳሾች አንብቦላቸዋል፡፡


አቃቤ ህግ በመጀመርያው መዝገብ
1ኛ ኃይለስላሴ ቢሆን – የኤጀንሲው ቀድሞ ዋና ዳይሬክተር
2ኛ የማነብርሃን ታደሰ – የኤጀንሲውም/ዋና ዳይሬክተር
3ኛ ሙከሚል አብደላ – የኤጀንሲው የግዥ ዳይሬክተር
4ኛ ኢንጅነር አሸናፊ ሁሴን – በመድኃኒትና የህክምና መገልገያዎች ግዥ ዳይሬክቶሬት የህክምና መሣሪያዎችና መገልገያዎች የግዥ አስተባባሪ የነበሩ
5ኛ ያሬድ ይገዙ- የኤጀንሲው የግዥ ትንበያና ግንባታ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የነበሩ
6ኛ እንዳርጋቸው ሞግሪያ – በመድኃኒትና የህክምና መገልገያዎችና ስርጭት ዳይሬክቶሬት ውስጥ የግዥ አስተባባሪ እና
7ኛ ያለው ሞላ -የኤጀንሲው የመድኃኒትና መገልገያዎች ግዥ አስተባባሪ የነበሩትን ሀላፊዎች እና የግዥ ኮሚቴ አባላትን ነው ያካተተው፡፡


ከዚህ ውስጥም 4ኛ እና 6ኛ ተከሳሾ እስካሁን በቁጥጥር ስር ያልዋሉ ናቸው፡፡
ክሱ በመሀል ዳኛው ሲነበብም በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፊ.ዲ.ሪ ወንጀል ህግ አንቀፅ 32/1/ሀ እና 411/1/ ሐ እና 2 ላይ የተመለከተውን ስለመተላለፋቸው ተገልጿል፡፡


ተከሳሾቹ በኤጀንሲው ውስጥ በተለያየ የስራ ሀላፊነት ላይ ሆነው በሚሰሩበት ወቅት የማይገባቸውን ጥቅም ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ ሁሉም በዋና ወንጀል አድራጊነት የመንግስትን ስራ በማያመች አኳኋን መርተዋልም ይላል፡፡


እንደ ክሱ አገላለፅ የፌደራል መንግስት ግዥ አስተዳደር አዋጅ፣የፌደራል መንግስት የግዥ አፈፃፀም መመሪያ እንዲሁም የኤጀንሲው የግዥ መመሪያ በቀጥታ ግዥ ለመፈጸም ዕቃው ከአንድ ዕጩ ተወዳዳሪ ብቻ የሚገኝ ከሆነ አልያም በጣም አስቸኳይ ከመሆኑ የተነሳ ከባድ ችግር የሚፈጥር ከሆነ ብቻ ነው የሚፈቅዱት፡፡


ይሁን እንጂ ተከሳሾቹ ይህን በመተላለፍ ለኢትዮጲያ ሀገር መከላከያ ሚኒስቴር Aqua tab 67mg of 3200 strips xena Aqua tab 8.5mg of 5000 የሚባል መድኃኒትን ያለምንም ጨረታ ሲትረስ ኢንተርናሽናል ከሚባል አቅራቢ እንዲገዛ አድርገዋል መባሉን የተነበበው ክስ ያስረዳል፡፡


እናም ታህሳስ 01 ቀን 2006 ዓ.ም በተላለፈ ውሳኔ ያለ ውድድር ከመሆኑ በተጨማሪ ምንም አይነት የዋጋ ድርድር ሳይደረግ በ13,449,110 ብር ግዥ ተፈፅሟል ብሏል አቃቤ ህግ፡፡


ተመሳሳይ የህግ ድንጋጌ የቀረበበት 2ኛ ክስ ደግሞ ለመድሀኒት ግዥ ጨረታ ከወጣ በኋላ ከመሀከል አቅራቢ ያልተገኘለት Atropine sulphate 1% eye drop የተባለውን የአይን ጠብታ መድኃኒት በቀጥታ አልኮን ከተባለ አቅራቢ እንዲገዛ አድርገዋል ሲል በ2ኛ፤3ኛ፤5ኛ እና 7ኛ ተከሳሾች ላይ ክሱን መስርቷል፡፡


በዚህም መሰረት የ74,470.00 ዶላር ወይም በብር 1,406,281.37 የግዥ ስምምነት በመፈረም ግዥው ህግን ባልተከተለ መልኩ እንዲፈፀም አድርገዋል በማለትም አክሏል፡፡
አቃቤ ህግ በዚህ ክስ ላይም ስምንት የሰው ምስክሮች እና የሰነድ ማስረጃዎች እንዳሉት ተጠቅሷል፡፡


የተከሳሾች ጠበቆች በበኩላቸው ክሱ ከተነበበ በኋላ መቃወምያ ካላቸው እንዲያቀርቡ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው የጠየቁ ሲሆን ደምበኞቻቸው ደግሞ የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅ ጠይቀዋል፡፡


አቃቤ ህግ በበኩሉ ተከሳሾቹ የቀረበባቸው ክስ በተለይም የወንጀል ህጉ 411/1/ ሐ እና 2 ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው በወንጀሉ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ከ 7 አመት እስከ 15 አመት የሚያስቀጣ መሆኑን ገልፅዋል፡፡


ይህን መሰረት አድርጎም ልዩ የሙስና ወንጀል አዋጅ 882/2007 ከ10 ዓመት በላይ የሚያስቀጣ የሙስና ወንጀል ዋስትናን አያስፈቅድም ይላል በማለት ጥያቄያቸውን ተቃውሟል፡፡
አቃቤህግ ባቀረበው 2ኛ የክስ መዝገብ ደግሞ በመጀመርያው መዝገብ ከ1-3 ያሉትን ተከሳሾች ጨምሮ ወ/ሮ ሳፍያ ኑር እና አቶ ማስረሻ አሰፋ የተባሉ የቀድሞ የኤጀንሲው የግዥ አፅዳቂ ኮሚቴዎችን አካቷል፡፡


በዝርዝሩም አምስቱ ተከሳሾች በመድሃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ሰራተኛ ሆነው ሲሰሩ በነበሩበት ወቅት ውስን ጨረታ በማድረግ ኤፒኤፍ ላይፍ የተባለ አቅራቢ በጨረታው ዝቅተኛ ዋጋ አቅርቦ አሸናፊ ሆኖ እያለ 500ሺህ ከረጢት መድሀኒት ብቻ ከእሱ እንዲገዛ ያደረጉ ሲሆን 50ሺህ ከረጢት ደግሞ በጨረታው ተሸናፊ ከነበረ ፋርማኪዩር በአንድ ከረጢት 23.45 ብር እንዲገዛ አድርገዋል ይላል፡፡


ቀሪ 400ሺህ ከረጢት ደግሞ የቸረታ ማስከበርያ ውል ባለማምጣቱ ከጨረታው ውጪ ተደርጎ ከነበረ ኢፋርም የተባለ ድርጅት እንዲገዛ አድርገዋል ይላል፡፡
የተለያዩ መድሀኒቶችን እንዲህ ከመመርያ ውጪ በ104 ሚልዮን ብር ግዥ እንደተፈፀመ የአቃቤ ህግ ክስ የዘረዘረ ሲሆን በአጠቃላይ በመንግስት ላይ ከ313ሺህ ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል ብሏል፡፡


የተከሳሾች ጠበቆች በበኩላቸው ይህ ከባድ ጉዳት ሊያስብል የሚችል አይደለምና የዋስትና መብት ሊከበርላቸው ይገባል በማለት ተከራክረዋል፡፡
የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎትም በሁለቱም መዝገብ ላይ የቀረበው ክስ እና የተጠቀሰው ድንጋጌ ዋስትናን የማያስፈቅድ ሆኖ አግኝቼዋለው በማለት የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ አድርጓል፡፡


እንዲሁም በቁጥጥር ስር ያልዋሉትን ሁለት ተከሳሾች የፌደራል ፖሊስ በአድራሻቸው አፈላልጎ መጥሪያ እንዲያደርስ በማለት ችሎቱ ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን ተከሳሾች የሚኖራቸውን የክስ መቃወምያ ለመቀበል ለግንቦት 19 ቀን 2011 ዓም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡