HMD EUዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ መንግስት ከአውሮፓ ህብረት ጋር ባደረገው የስደተኞችን ፍልሰት የመግታትና የማቆም ስምምነት መሰረት ከጎረቤት ሶማሊያ ተሰደው በዶሎ የሰደተኞች ካምፕ ለሚገኙ ዜጎች አስር ሺህ ሄክታር የእርሻ መሬት በመሰጠት ላይ መሆኑ ተሰማ።
የእርሻ መሬቱ እየተሰጠ ያለው የኦሮሚያና የሶማሌ ክልሎች በሚወዛገቡበት የሊበን ዞን ነው።
ስደተኞቹን ወደ እርሻ ስራ የማስገባቱ ስራ የኢትዮጵያ መንግስት ከአውሮፓ ህብረት ጋር ባደረገው ስምምነት የሚካሄድ ሲሆን በምላሹ የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ የኢንደስትሪ ፓርኮች ግንባታ ብድርና ድጋፍ ይሰጣል።
እስካሁን የተረጋገጠ 200 መቶ ሚሊያን ዩሮ ብድር ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ የተገኘ ሲሆን የአውሮፓ ህብረት ደግሞ የ50 ሚሊያን ዩሮ ድጋፍ አድርጓል።
ኢትዮጵያ 500 መቶ ሚሊየን ዶላር የሚጠይቅ ፕሮጀክት አዘጋጅታ ለለጋሾች ያቀረበች ሲሆን የአለም ባንክ በጉዳዩ ላይ እየመከረ መሆኑን ለመረዳት ችለናል።በተለይ ለጎረቤት ሀገር ስደተኞች የእርሻ መሬት መስጠት ከሀገሬው ነዋሪ ጋር ያልተፈለገ ግጭት ሊያስከትል ይችላል ሲል ስጋቱን ገልጿል።
በኢንደስትሪ ፓርኮች ውስጥ ቢያንስ 30 ሺህ የጎረቤት ሀገር ስደተኞች በተለይም ኤርትራውያንን የመቅጠር እቅድ መያዙም ታውቋል።

ስደተኞች ከካምፕ ወጥተው ከማህበረሰቡ ተቀላቅለው እንዲኖሩ ለመድረግም ስምምነት የተደረሰ ሲሆን የልደት ካርድ መታወቂያና የባንክ አገልግሎትን ከሀገሬው እኩል እንዲያገኙ የሚያስችል አሰራርም መቀየሱን ተረድተናል። በጋምቤላ ክልል ያሉ የደቡብ ሱዳን ስደተኞችም በዚሁ ፕሮግራም ውስጥ ተካተዋል። በጉዳዩ ላይ ዘርዘር ያለ መረጃ ከታች በተያያዘው የድምፅ ዘገባ ላይ ታገኛላችሁ