addis-ababa-streetዋዜማ ራዲዮ- የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እድሜያቸው ከ18 እስከ 25 የሚኾኑ ሥራ አጥ ወጣቶችን በተጠባባቂ ፖሊስ አባልነት ለመመልመል ያወጣው ማስታወቂያ በርካታ ቁጥር ያላቸው ወጣቶችን ትኩረት ስቧል፡፡ በወረዳና ክፍለ ከተማ ማዕከሎች፣ በወጣት ማዕከላት ቢሮዎችና በከተማዋ ቅርንጫፍ የፖሊስ ጽሕፈት ቤቶች ምዝገባ የተጀመረ ሲሆን  በሂደቱ ቁጥራቸው በሺ የሚቆጠሩ ተመልማዮችን ለማቀፍ እቅድ እንዳለ ተሰምቷል፡፡

እጩ የመኾን ፍላጎት ያላቸው ወጣቶች በየትኛውም ከአቅራቢያቸው የሚገኙ የፖሊስ ንዑስ ጣቢያዎች እንዲመዘገቡ ሁኔታዎች እንደተመቻቹላቸው ተነግሯል፡፡ መንግሥት ከስድስት ወራት በኋላ እንደገና አዲስ የፖሊስ ምልመላ መጀመሩ አገሪቱ ያለችበትን መልካም ያልሆነ ድባብ አመላካች ነው ያሉ አልጠፉም፡፡ አዲሱ ምልመላ በፍጥነት እንዲካሄድ መወሰኑ በከተሞች አካባቢ ከሥራ አጥ ወጣቶች መብዛትና ከተቃውሞ ድምጾች መበራከት ጋር ተያይዞ ወደፊት ሊከሰት የሚችል የጸጥታ ችግር ስጋት መኖሩን አመላካች  ነው ተብሏል፡፡

ዋዜማ በትክክል ምን ያህል ቁጥር ያላቸው እጩ የፖሊስ መኮንኖችን ለመመልመል እንደተፈለገ ለመረዳት ያደረገችው ሙከራ ባይሳካም አንድ ነባር የአራዳ ክፍለ ከተማ የፖሊስ አባል በዚህ ዙር ከሁለት እስከ ሦስት ሺ አዳዲስ ፖሊሶች ሊቀጠሩ እንደሚችሉ ከባልደቦቻቸው መስማታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ 

ከሚያዚያ 22 ጀምሮ እስከ ግንቦት 6፣ 2009 ዓ.ም የሚቆየው የምዝገባ ሰሌዳ ተመዝጋቢዎቹ ቢያንስ 10ኛ ክፍል ማጠናቀቅ እንዳለባቸው ያሳስባል፡፡ የተመልማዮቹ ቁመት ለወንድ 1.65 ሲሆን ለሴቶች 1.60፣ እንዲሁም ክብደት ለወንድ ከ50-70፣ ለሴቶች ደግሞ ከ48-65 ኪሎ ግራም እንደሆነ መመዘኛው አስቀምጧል፡፡

ተመልማዮቹ ተመዝግበው ለምልመላ ብቁ ከሆኑበት ሰዓት ጀምሮ የኪስ ገንዘብ እንደሚሰጣቸው ቃል የተገባ ሲሆን ነገር ግን አንዴ ከተመዘገቡ በኋላ በማሰልጠኛ ትምህርት ቤቱ የሚቀርብላቸውን ምግብ ላለመመገብ አሻፈረኝ ማለት እንደማይችሉ ቅድመ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል፡፡

የምልመላ ማስታወቂያው በግልጽ እንዳስቀመጠው እጩ ተመልማዮች ከዚህ ቀደም በነበረ ማንኛውም የአመጽ/ተቃውሞ ዉስጥ እጃቸውን ያላስገቡ እንደሆኑ ማጣራት ይደረግባቸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በፖሊስ ወይም በመከላከያ ሠራዊት ዉስጥ ተሳትፎ የነበራቸው ኾነው በተለያየ ምክንያት ሠራዊቱን የተሰናበቱም ደግሞው መመዝገብ እንደማይችሉ ተደንግጓል፡፡

ማንኛውም ለፖሊስነት የሚመዘገቡ ወጣቶች ተጠባባቂ የፖሊስ ሠራዊቱን በመቀላቀላቸው በርከት ያሉ ጥቅማ ጥቅሞችን የሚጠበቁላቸው እንደሆነ የተዘረዘረ ሲሆን በስልጠና ላይ እያሉ ነጻ ሕክምና ለራሳቸው እንደሚያገኙና ሥልጠናውን በብቃት ሲያጠናቅቁ ደግሞ ሙሉ ቤተሰባቸው የነጻ ሕክምና ተጠቃሚ እንደሚሆን ቃል ተገብቶላቸዋል፡፡

ከነዚህ ጥቅማ ጥቅሞች ባሻገር ብርድልብስ፣ አንሶላ፣ ካፖርት፣ ጫማ፣ የዝናብ ልብስና የደንብ ልብስ በየጊዜው እንደሚያገኙ ለተመልማዮች ተገልጾላቸዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር እጩዎቹ ከስልጠና ቤት ከወጡ በኋላ ራሳቸውም ሆኑ ቤተሰባቸው የፖሊስ መረዳጃ እድር አባል የመሆን ሙሉ መብት እንዳላቸው ተመልክቷል፡፡

በሥራ ላይ እየሉ በሚደርስ ድንገተኛ አደጋና የሕግ መጠየቅ ቢያጋጥም ፖሊስ ኮሚሽን በራሱ ወጪ ጠበቃ እንደሚያቆምላቸውም ተብራርቶላቸዋል፡፡

ስልጠናውን በብቃት ለሚያጠናቅቁ እጩዎች በየወሩ የኢትዮጵያ ብር 1583 (አንድ ሺ አምስት መቶ ሰማንያ ሦስት ብር) እንደሚሰጣቸውና ከዚህም አልፎ በየወሩ 450 ብር የቀለብ አበል እንደሚለገሳቸው ተመልክቷል፡፡

ተመዝጋቢዎች ለምዝገባ በሚቀርቡባቸው ጣቢያዎች ፎርጅድ ያልሆኑ የ8ኛና የ10ኛ ክፍል የትምህርት ማስረጃዎችን እንዲያመጡም አደራ ተብለዋል፡፡

እጩዎች በምዝገባ ሂደት እስከዛሬ ሕገ መንግሥቱን በመናድ እንቅስቃሴ ያልተሳተፉ ብቻም ሳይሆን የማይጠረጠሩ ስለመሆናቸው ጠበቅ ያለ ምርመራ እንደሚደረግባቸው ታውቋል፡፡ የማንኛውም ፖለቲካ ድርጅት አባል እንዳልሆኑ ማረጋገጫ ማጻፍ የሚኖርባቸው ሲሆን ይህ ግን የተቃዋሚ ፓርቲዎችን እንጂ በአራቱ የኢህአዴግ አጋር ድርጅቶች ዉስጥ አባል መሆንን አይጨምርም፡፡ አባል መሆን በምዝገባው ላይ የሚፈጥረው ምንም ችግር እንደሌለ ታውቋል፡፡

መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያየለ የመጣውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ለፖሊስ ሠራዊቱ ተከታታይ እውቅናና እንክብካቤ መስጠት ጀምሯል ይላሉ ታዛቢዎች፡፡ ፌዴራል ፖሊስ ከቅርብ ወራት በፊት ባካሄዳቸው የእውቅናና የምስጋና መርሐግብሮች  በሠራዊቱ የረዥም ጊዜ አገልግሎት ሽልማቶችና የማዕረግ እድገቶችን ማድረጉ አይዘነጋም፡፡ በፖሊስ ሠራዊቱ ዉስጥ የላቀ የሥራ አፈጻጸም አሳይተዋል ለተባሉና በቁጥር 2575 ለሚሆኑ ፖሊሶች የሜዳይ፣ የሪቫን፣ የገንዘብና የእውቅና ሠርተፍኬት፣ ለአራት አባላቱ ደግሞ ከኮማንደርነት ወደ ረዳት ኮሚሽነርነት እድገት የሰጠው ከጥቂት ወራት በፊት በሚሊንየም አዳራሽ ነበር፡፡