MIDROC Chairman – Mohamed Alamudin – FILE

ዋዜማ ራዲዮ- በአካባቢ ብክለት እና በነዋሪዎች ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል በሚል ውንጀላ ሳቢያ በተነሳ ህዝባዊ አመጽ ለሶስት አመታት ተዘግቶ የቆየው የሜድሮክ ወርቅ ማምረቻ እንደገና ምርት በጀመረ በአመት ውስጥ 132.77 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ምንዛሬን ማስገኘቱን ዋዜማ ከኩባንያው ምንጮቿ ሰምታለች።

በኦሮምያ ክልል በአዶ ሻኪሶ ወረዳ ለገደንቢ አካባቢ ሻኪሶ አቅራቢያ ያለው  ሜድሮክ ወርቅ ማእድን ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ከ132 ሚሊየን ዶላር በላይ የሆነ የውጭ ምንዛሬን በ2014 አ.ም የበጀት አመት ያስገኘው 2647 ኪሎ ግራም ወርቅን አምርቶ በመላክ መሆኑንም ተረድተናል።

 የዛሬ አራት አመት (በ2010 አ.ም) ነበር የሜድሮክ ወርቅ ማእድን ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በለገደንቢ ያለው የወርቅ ማምረቻ  “በአካባቢ ብክለት እና በነዋሪዎች ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል” በሚል  ፈቃዱ እንዲሰረዝ የተደረገው። 

የፈቃድ ስረዛውም በኩባንያው ላይ ከሚነሳው በሚለቀው ኬሚካል በሚደርስ የሰዎች ጤና ችግርና የአካባቢ ብክለት ይልቅ ፖለቲካዊ ይዘት ባለው ተቃውሞ መሆኑንም የሚያነሱ አሉ።

በወቅቱ የሜድሮክ ወርቅ በለገደንቢ የነበረውን የሀያ አመታት የወርቅ ማምረት ፈቃድን ጨርሶ ለተጨማሪ አስር አመታት የማምረት ፈቃድ እድሳትን ለማግኘት ከጫፍ የደረሰበት ጊዜ ነበር።

በወቅቱ የነበረው የመአድን ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴርም የራሱን እና የገለልተኛ አካላት ጥናትን አካትቼ በሰራሁት ጥናት ኩባንያው የተነሳበትን አይነት የአካባቢ ብክለት አያመጣም በሚል ለተጨማሪ አስር አመታት የወርቅ ማምረት ፈቃድን ለሜድሮክ ሰስጥቶት ነበር። 

ይሁንና በወቅቱ ከነበሩ የኦሮሞ አድማ አስተባባሪዎች ተቃውሞ በመነሳቱ ሚኒስቴሩ የአስር አመታት ተጨማሪ የወርቅ ማምረት ፈቃድን ለሜድሮክ ወርቅ በሰጠ በቀናት ውስጥ መልሶ አግዶታል። በወቅቱም ለፈቃዱ መታገድ በምክንያትነት የቀረበው የአካባቢ ብክለት ሳይሆን የህዝብ ጥያቄ ነው የሚል ነበር።

ሜድሮክ ወርቅ በወቅቱ ለወርቅ ማንጠሪያነት የምጠቀመው ሶዲየም ሳናይድ በአለም አቀፍ ደረጃ ለዘርፉ የተፈቀደ አጠቃቀሜም ደረጃውን የጠበቀ ነው በሚል ውሳኔው ፖለቲካዊ መሆኑን እንደሚያስብ የሚያሳዩ ተጨማሪ የሰነድ ማስረጃዎችን አካታ ዋዜማ ራዲዮ ተከታታይ ዘገባ መስራቷ ይታወሳል።

በኩባንያው መዘጋትም ኢትዮጵያ ከወርቅ በአመት በአማካይ እስከ 200 ሚሊየን ዶላርን አጥታለች።በሜድሮክ ወርቅ ማእድን የለገደንቢ ማምረቻ ላይ የፍቃድ ስረዛው ከተደረገ በኋላ በድጋሜ በተሰራ የአካባቢ ተጽእኖ ጥናት የኩባንያው በካይነት እስከ መዘጋት የሚደያደርስ ሳይሆን በቀላሉ የሚታረም መሆኑ ቢረጋገጥም በፍጥነት ስራ ሊጀምር አልቻለም።

ባለፈው አመት ምርት ከጀመረ ወዲህ ግን 133 ሚሊየን ዶላርን አስገኝቷል።

ኩባንያው በምን ስምምነት ተመልሶ ስራ እንደጀመረ ለሜድሮክ ምንጮቻችን ላነሳነው ጥያቄ ያገኘነው ምላሽ እንደሚያመለክተው  ለሚያመርትበት አካባቢ እና ለኦሮምያ ክልል ከገቢው በሚከፍለው ክፍያ ላይ በመስማማት እና በአካባቢው ላሉ ባህላዊ አምራቾች ሙያዊ እገዛ ለማድረግ በመስማማት መሆኑን ተረድተናል። የሚድሮክ ምንጮች ስለ ስምምነቱ ዝርዝር ከመናገር ተቆጥበዋል። [ዋዜማ ራዲዮ]