ዋዜማ ራዲዮ- በአዲስ አበባ ዳርቻ በተለያየ ጊዜ በልማት ምክንያት ከቀያቸውና ከይዞታቸው በልማትና በተለያዪ ምክንያቶች ተነሱ ለተባሉ አርሶአደሮችና ልጆቻቸው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተሰሩ የጋራ መኖርያ ቤቶች (ኮንደሚኒየም) ላይ ያሉ የንግድ ቤቶች ሊሰጣቸው እንደሆነ ዋዜማ ራዲዮ ማረጋገጥ ችላለች።


የንግድ ቤቶቹም በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የጋራ መኖርያ ቤቶች ላይ ያሉትን የሚጨምር ሲሆን : የልማት ተነሽ አርሶ አደሮችን እና ቤተሰቦቻቸው ለአምስት እየተደራጁ አንድ የንግድ ቤት እንደሚሰጣቸው መረዳት ችለናል። ተደራጅቶ የጋራ መኖርያ ቤት ማግኘቱ ከዚህ ቀደም 22, 915 የጋራ መኖርያ ቤቶች የተሰጣቸው ግለሰቦችንም የሚመለከት ነው።


ከዚህ ቀደም በነበረ አሰራር የጋራ መኖርያ ቤት ላይ ያሉ የንግድ ቤቶች የከተማ አስተዳደሩ በጨረታ በውድ ዋጋ ሲሸጣቸው እንደቆየ የሚታወቅ ነው።
     የጋራ መኖርያ ኮንደሚኒየም ህንጻዎች ላይ ያሉ የንግድና መኖርያ ቤቶች ለተፈናቃይ አርሶአደሮች የመስጠቱ ነገር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ግብርና እና የአርሶአደር ልማት ኮሚሽን የ2012 አ.ም የልማት ተነሽ አርሶ አደሮችን መልሶ ለማቋቋም ካወጣው እቅድ አንዱ ነው።


ለዚህም ሲባል በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ፣ የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ለከተማ አስተዳደሩ የከተማ ግብርና እና የአርሶ አደር ልማት ኮሚሽን የኮንደሚኒየም የንግድ ቤቶችን ለይቶ እየላከለት መሆኑን መረዳት ችለናል።
በከተማ አስተዳደሩ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ የቤቶች ኮርፖሬሽን ባለፈው አመት ታህሳስ ወር የልማት ተነሽ አርሶአደሮችን ለማቋቋም የኮንዶሚኒየም የንግድ ቤቶች እንዲሰጡ በተወሰነው መሰረት ይሄንን ለማስፈጸምም አንድ መቶ የንግድ ቤቶችን ዝርዝር እንደላከለት መረጃ አግኝተናል።


ቤቶቹም 50 ሚሊየን ብር የሚያወጡ ሲሆኑ ኮዬ ፈጩ ፣ ቂሊንጦ፣ ገላን ፣ገነት መናፈሻ ፣ ቱሉዲምቱ ፣ ቦሌ አራብሳ ፣ ቦሌ አያትና ቦሌ ቡልቡላ ሳይት የሚገኙ የጋራ መኖርያ ቤቶች ላይ ያሉ ናቸው።
ለነዚህ ቤቶችም የአዲስ አበባ ከተማ የከተማ ግብርና እና የአርሶአደር ልማት ኮሚሽን ለቤቶች ኮርፖሬሽን 50.4 ሚሊየን ብር ከፍሎ ለተነሽ አርሶ አደሮችና ቤተሰቦቻቸው የሚያስረክብ ይሆናል። እነዚህ አንድ መቶ የኮንደሚኒየም የንግድ ቤቶች አሁን ላይ እየተኖረባቸው ካሉ ሳይቶች የተለዩ ሲሆን እጣ ወጥቶባቸው እስካሁን እድለኞ ያልገቡባቸው ሳይቶች ላይ ካሉ የንግድ ቤቶች መካከልም የንግድ ቤቶቹ ለልማት ተነሺዎች ይሰጣልም ተብሏል። ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከተከፋፈሉት 22, 915 የጋራ መኖርያ ቤት ውስጥ እድለኛ ከሆኑት መካከል የንግድ ሱቅ ይሰጣቸዋል ተብለው እየጠበቁ እንደሆነም ለዋዜማ ራዲዮ የተናገሩም አሉ።


     እንዲሁም የልማት ተነሽ አርሶ አደር ሆነው እንደገና ይቋቋማሉ ተብለው የተለዩ ከ26 ሺህ በላይ አርሶ አደርና ቤተሰቦቻቸው የተለያዩ የመቋቋሚያ ማእቀፎች እንደተዘጋጁላቸው መረዳት ችለናል። የማቋቋሚያ ማእቀፉም የተነሽ አርሶአደሮችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታን ማስተካከልን አላማው ያደረገ ነውም ተብሏል።


     ነገር ግን የዚህ አተገባበር ላይም ከጅምሩ ለከፍተኛ ክፍተትና ስህተት የተጋለጠ መሆኑም ከወዲሁ እየተነሳ ነው። ሲጀመር የጋራ መኖርያ ሱቆችም ሆነ የሌሎች ማቋቋሚያ ማእቀፎች ተጠቃሚ የሚሆኑት ከዚህ ቀደም የልማት ተነሽ አርሶ አደርና ቤተሰቦቻቸው በሚል የጋራ መኖርያ ቤት የተሰጣቸው ናቸው። ነገር ግን የጋራ መኖርያ ቤቱ ከተሰጣቸው 22, 915ቱ ውስጥ በርካታ በመልሶ ማቋቋሚያ ውስጥ መካተት የማይገባቸው ግለሰቦች መኖራቸው የሚታወቅ ነው።


የልማት ተነሽ አርሶ አደር ልጅና የልጅ ልጅ ተብለው የጋራ መኖርያ ቤት ለማግኘት የተለያየ ህገ ወጥ ሰነድ ለማሰራት እስከ 30 ሺህ ብር የከፈሉ በርካቶች እንዳሉ ሰምተናል። የጋራ መኖርያ ቤቱ ተጠቃሚ ለመሆን ከአዲስ አበባ ዳርቻ የተነሳ አርሶ አደር ወይንም ቤተሰብ መሆን ያስፈልጋል በተባለበት ሁኔታም ከሌላ ስፍራም መጥተው የቤቱ ተጠቃሚ የሆኑ አሉ።


በከተማው ያሉ አንዳንድ ባለስልጣናትም በጥቅምም ሆነ በሌላ ለሚቀርቧቸው ግለሰቦችም ቤቶችን አሰጥተዋል።በዚህ መሀል ደግሞ የልማት ተነሽ አርሶ አደር ሆነን ሳለ የጋራ መኖርያ ቤት እየተገባን አልተሰጠንም በሚል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተቋማትን ደጅ የሚጠኑ በርካታ ግለሰቦች ባለፉት ሳምንታት በይፋ ታይተዋል።
የጋራ መኖርያ ቤቶቹን ያገኙት ግለሰቦች የከተማ አስተዳደሩ ቤቶቹን በራሱ የማያጠናቅቅ ከሆነ የበጀተውን ሁለት ቢሊየን ብር ራሳቸው እንዲያከናውኑ ሊያከፋፍላቸው ይችላል። [ዋዜማ ራዲዮ]