EPRDF logo
EPRDF logo

ዋዜማ ራዲዮ- በኢትዮጵያ በተከታታይ ወራት የተነሳውን ሀዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ “ሀገር ዓቀፍ ፖለቲካዊ ድርድር ሊደረግ ታስቧል” የሚል ጭምጭምታ መሰማት ከጀመረ ስነባበተ፡፡ በአሜሪካ መንግስት አጋፋሪነት የአፍሪቃና የአውሮፓ ሀገራት የተካተቱበት አንድ ቡድን በቅንጅት አደራዳሪ ለመሆን እያሰቡ ስለመሆኑ ከዲፕሎማቶች የሚወጡ ፍንጮች ይጠቁማሉ፡፡

ርግጥ ነው፣ በአሁኑ ጊዜ ሀገሪቱን የገጠሟት ፈተናዎች ፖለቲካዊ በመሆናቸው መፈታት የሚችሉትም በፖለቲካዊ መንገድ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ አንዱ ሰላማዊ የፖለቲካ ቀውስ ማስወገጃ መንገገድ ደሞ በፖለቲካ ቡድኖች መካከል የሚካሄድ ብሄራዊ ወይይት እና ድርድር ነው፡፡ ስለሆነም ጥንስስ ሃሳቡ ተሳካም አልተሳካም ወቅታዊነቱ አያጠራጥርም፡፡

ተሳክቶ ድርድር ቢደረግ ሊታሰብባቸው የሚገቡና የሀገሪቱን የዴሞክራሲ ሽግ ግር እውን ሊያደርጉ በሚችሉ ነጥቦች ዙሪያ ቻላቸው ታደሰ ይህን ዘገባ አዘጋጅቷል

ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በርካታ ተቃዋሚ ቡድኖች እና ምሁራን ብሄራዊ ዕርቅ ወይም ሁሉንም አካታች የሆነ ሀገር ዓቀፍ ፖለቲካ ድርድር እንዲካሄድ ጥሪ አድርገዋል፡፡ ከኢህአዴግ ያገኙት ምላሽ ግን አንድ እና አንድ ብቻ ነው፡፡ “ድርድር ብሎ ነገር የለም፤ ሁሉም ነገር የሚወሰነው በምርጫ ነው፡፡ ህገ መንግስቱ የሀገሪቱን መሰረታዊ የዴሞክራሲ፣ ብሄር እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ላንዴና መጨረሻ ጊዜ ፈትቷል፡፡ ታዲያ ብሄራዊ ዕርቅ የምትሉት ምንድን ነው? እነማንስ ናቸው ዕርቅ የሚያደርጉት?” በማለት ጥሪዎቹን ሲያጣጥላቸው ኖሯል፡፡ በዚህ ግትር ባህሪውም ሀገሪቱን ወደ ምስቅልቅል እየገፋት መሆኑን በርካታ ታዛቢዎች ሲያስጠነቅቁ መኖራቸው ዕሙን ነው፡፡

አሁን የታሰበው ድርድር ገና ጥንስስ ሀሳብ በመሆኑ ዝርዝሩን ለማወቅ አዳጋች ቢሆንም ዕውነት ከሆነ ግን ሃሳቡ በሁለት መንገድ ጠረጴዛ ላይ ቀርቦ ሊሆን ይችላል፡፡ ባንድ በኩል የኢህአዴግ-መራሹ መንግስት አጋሮች በሆኑት ምዕራባዊያን መንግስታት በተለይም የአሜሪካ መንግስት ድርድር እንዲጀመር ሃሳብ አቅርቦ ሊሆን ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ግን በህዝባዊ ተቃውሞ እየተናጠ ያለው ኢህአዴግ ራሱ ምዕራባዊያን ዲፕሎማቶችን “አደራድሩኝ” የሚል ሃሳብ አቅርቦላቸው ይሆናል፡፡

ሃሳቡ በየትኛውም መንገድ ይምጣ ኢህአዴግ ለድርድር ፍቃደኝነት ካሳየ ሁለት ነገሮችን አስቧል ማለት ነው፡፡ አንደኛው ቀስ በቀስ ወደ ፖለቲካዊ ቀውስ እየገባ መሆኑን መረዳቱን እና በብቸኝነትም ሀገር ለማስተዳደር የሚያስችለው ቅቡልነት ማክተሙን መገንዘቡን ሊያመለክት ይችላል፡፡ ሌላኛው ደሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህዝባዊ ተቃውሞዎችና ግጭቶች በጅኦግራፊያዊ ሽፋናቸው፣ በተከታታይነታቸው እና በሚያነሱት ፖለቲካዊ አጀንዳ እየከበዱ በመሄዳቸው ጊዜ ለመግዛት እና መተንፈሻ ለማግኘት ሊጠቀምበት ፈልጎ ሊሆን ይችላል፡

ያም ሆነ ይህ ታስቧል የሚባለው ድርድር ዕውነት ከሆነ ኢህአዴግ ከ1983ቱ ሽግግር ቻርተር ጉባዔ በኋላ ከምርጫ ወይም ፓርላሜንታዊ ስርዓቱ ውጭ በሀገር ዓቀፍ ፖለቲካዊ ድርድር ሲቀመጥ የመጀመሪያው ይሆናል ማለት ነው፡፡

በፖለቲካዊ ድርድር ዙሪያ ግን ብዙ ከባድ እና አወዛጋቢ የሚሆኑ ጉዳዮችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ምን ዓይነት ፖለቲካዊ ድርድር ነው የሚካሄደው? በምን ማዕቀፍ ነው ድርድር የሚካሄደው? እነማን ናቸው ተደራዳሪዎቹ? በድርድሩ ለመሳተፍስ መስፈርቶቹ ምን ይሆናሉ? ምን አጀንዳዎችስ ናቸው ጠረጴዛው ላይ የሚቀርቡት? የድርድሩስ መጨረሻ ግብ ምንድን ነው? ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ ጥያቄዎቹ ብዙ የሆኑትን ያህል መልሶቹም ውስብስብ እና የተራራቁ እንደሚሆኑ መገመት አይከብድም፡፡

ኢህአዴግ ላለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ተከታታይ ፖለቲካዊ ድርድር ያደረገው ከኦጋዴን ነፃ አውጭ ግንባር (ኦብነግ) ጋር ነው፡፡ የሁለትዮሹን ድርድሩን ይዘት፣ ሂደት እና ውጤት ግን በይፋ ገልፆ አያውቅም፡፡ በተለይ በኳታር መንግስት አደራዳሪነት ከተካሄዱት ተከታታይ ድርድሮች አንዳችም ጠብ ያለ ውጤት የለም፡፡ ይልቁንስ መንግስት ለተወሰኑ የኦብነግ አመራሮች ምህረት በመስጠት የሸማቂው ድርጅት ህልውና አክትሟል እያለ ፕሮፓጋንዳ ለመንዛት ሲጠቀምበት ኖሯል፡፡ ኦብነግ ግን አለፍ ገደም እያለም ቢሆን መንግስትን በትጥቅ መፋለሙን አላቆመም፡፡ በጠቅላላው ከኦብነግ ጋር ያደረጋቸው ድርድሮች ጊዜ ከመግዛት ወይም በብልጣብልጥነት ሸማቂውን ድርጅት ከፋፍሎ ከማዳከም ያለፈ ዓላማ የነበራቸው አይመስልም፡፡

ODF Chairman Lencho Letta, PHOTO -ESAT
ODF Chairman Lencho Letta, PHOTO -ESAT

በሌላ በኩል በአቶ ሌንጮ ለታ የሚመራው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) ከኢህአዴግ-መራሹ መንግስት ጋር ለመደራደር ጥረቶች ሲያደርግ መቆየቱን ሲገልፅ ይሰማል፡፡ ተደራዳሪ ልዑካን ቡድንም ወደ አዲስ አበባ ልኮ በር ለማስከፈት መሞከሩን በተደጋጋሚ ገልጧል፡፡ ከኢህአዴግ በኩል ግን አንዳችም አወንታዊ መልስ አለማግኘቱን ይገልፃል፡፡

የሆነው ሆኖ ኢህአዴግም ሆነ ተቃዋሚዎች አሁን ድርድር ቢቀመጡ ተጠቃሚው ኢህአዴግ መሆኑ ግን አይካድም፡፡ ባንድ በኩል ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት የቆመበትን ብሄር-ተኮር ፌደራላዊ ስርዓት መሰረት የሚያናጋ ሀገር ዓቀፍ ከባድ የፖለቲካ ቀውስ ገና አልተገጠመውም፡፡ ምልክቶቹ ግን እየታዩ ነው፡፡ ስለዚህ ከኢህአዴግ ባህሪ አንፃር ሲታይ ለድርድር ዝግጁ የሚሆነው ሀገራዊ ቀውሱን በኃይል መፍታት የማይችልበት ደረጃ ላይ ሲደርስ ብቻ እንደሆነ በ1997ቱ ምርጫ ማግስት ታይቷል፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ በድርድሩ ለመሳተፍ የብሄር ፌደራሊዝሙንና ሀገ መንግስቱን መቀበልን እንደቅድመ ሁኔታ በማሰቀመጥ ድርድሩ በኢህዴግና በተቃዋሚዎች መካከል ብቻ ሳይሆን በራሳቸው በተቃዋሚዎች መካከል እንዲሆን በማድረግ ለመከፋፈል እንደሚሞክርም መገመት ይቻላል። በተለይ በዚህ ቅድመ ሁኔታ ህብረ-ብሄራዊ ድርጅቶችን ለማግለልና በሀገሪቱ ያለውን የአንድ ብሄር የበላይነት አስጠብቆ ለመቆየት ሊጠቀምበት ይችላል። ከሁሉ የከፋው ግን ገዥው ፓርቲ በድርድር ይህ ነው የሚባል ታሪክ የለውም። ድርድርን ለጊዜያዊ ተቃውሞ ማብረጃና ለይስሙላ ካልሆነ በቀር ከምር ሞክሮትም አያውቅም። አሁንም ቢሆን ከዚህ የተለየ አቋም ይኖረዋል ብሎ መገመት የዋህነት ይሆናል።

በሌላ በኩል ኢህአዴግ በቢሮክራሲያዊ እና ፓርቲ መዋቅሩ እንዲሁም በደህንነት እና መከላከያ ኃይሉ ላይ ያለው ቁጥጥር ገና አልላላም፡፡ ምንም እንኳ ከአቶ መለስ ህልፈት በኋላ በገዥው ግንባር የኃይል አሰላለፍ ሽግሽግ ይኖራል ተብሎ ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም መሰረታዊ ለውጥ ግን ሊታይ አልቻለም፡፡ ዛሬም ህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና ፀጥታ ኃይል መዘወሪያ የሆኑትን ምህዋሮች እንደያዘ ነው፡፡ በተለይ በቅርቡ ህወሃት ከአማራ ክልላዊ መንግስት ዕውቅና እና ፍቃድ ውጭ በሰሜን ጎንደር ዞን ሲወሰዱ የሰነበቱት ፀረ-ህገመንግስታዊ የኃይል ዕርምጃዎችም የኃይል ቁጥጥሩን መጠን እና ፖለቲካዊ በላይነቱን አመላካቺ ናቸው፡፡ በብዙ የሀገሪቱ ክፍሎች ኢህአዴግ መከላከያ ሰራዊቱን ለሰላማዊ ተቃውሞ መጨፍለቂያ መሳሪያነት መጠቀሙን የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ፡፡

አሁን ሀገሪቱ በተከታታይ ህዝባዊ አመፆች እየተናጠች ያለችው ተቃዋሚ ድርጅቶች በተዳከሙበት ጊዜ ነው፡፡ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ተደራዳሪ የሚሆኑ ጠንካራ ተቃዋሚ ቡድኖች የሉም፡፡ በስደት ያሉትም ቢሆኑ ህዝባዊ መሰረታቸው መሬት ላይ በተግባር አልተፈተነም፡፡ የኦሮሞን ህዝብ እወክላለሁ የሚለው ኦሮሞ ነፃነት ግንባርም (ኦነግ) ክፍፍል ከገጠመው ወዲህ ድምፁ እምብዛም አይሰማም፡፡ ህብረ ብሄራዊ የሆኑት ኢህአፓ እና መኢሶንም ደብዛቸው የለም፡፡

የሀገር ውስጥ ተቃዋሚ ድርጅቶች ደሞ በኢህአዴግ “ከፋፍለህ ግዛ” ፖሊሲ ክፉኛ ተዳክመዋል፡፡ ሁሉም ማለት ይቻላል በውስጣዊ ሽኩቻዎች ጭምር የተዳከሙ ናቸው፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት መጠነኛ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የሚታዩት የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ)፣ አንድነት፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ መድረክ እና ሰማያዊ ፓርቲ ናቸው፡፡ በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች በተከታታይ የተካሄዱትን ህዝባዊ ተቃውሞዎች ግን በየትኛው የሀገር ውስጥ ተቃዋሚ ድርጅት በኦፊሴል አልተጠሩም፡፡ በግብታዊነት ተቃውሞ የወጣውን ሰልፈኛንም መምራት አልቻሉም፡፡ ኢህአዴግ ያለፈውን ዓመት ብሄራዊ ምርጫ መቶ በመቶ አሸነፍኩ ካለ ወዲህ ከመድረክ፣ መኢአድ፣ አንድነት እና ሰማያዊ ፓርቲ ጋር የጋራ የፖለቲካ ድርድር መድረክ የለውም፡፡ የጋራ ፖለቲካ መድረኩ ኢህአዴግ እና በጣት የሚቆጠሩ እዚህ ግባ የማይባሉ ጥቃቅን ተቃዋሚ ድርጅቶች የሚናኙበት ሆኗል፡፡

በሌላ በኩል ኢህአዴግ ለድርድር ቢቀመጥም እንኳ ግዙፍ ቀውስ እስካልገጠመው ድረስ መሳሪያ ካነሱ ቡድኖች ጋር ለመደራደር ፍቃደኝነት የሚኖረው አይመስልም፡፡ ከሃያ አምስት ዓመታት በፊት እንዳደረገው ሁሉ ኦነግን፣ ኦጋዴን ነፃ አውጭ ግንባር እና አርበኞች ግንቦት ሰባት ግንባርን ከጨዋታው ውጭ ማድረግን እንደ ቅድመ ሁኔታ እንደሚያስቀምጥ መገመት አይከብድም፡፡ ለድርድር መጋበዝ ከፈለጉ ጠመንጃ ማስቀመጣቸውን ወይም መንግስትን በኃይል የመጣል አጀንዳቸውን በይፋ መተዋቸውን ማወጅ አለባቸው ሊል ይችላል፡፡ ህገ መንግስታዊ ስልጣን ከምርጫ ሳጥን ብቻ እንዲመጣ የሚሰብኩት ምዕራባዊያንም ከኢህአዴግ የተለየ አቋም ለመያዝ ሊቸገሩ ይችላሉ፡፡

ላለፉት 25 ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ መድረክ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑት ብሄር-ተኮር ፖለቲካ ድርጅች ናቸው፡፡ ለዚህም ነው አሁን ድርድር ቢታሰብ ህብረ-ብሄራዊ ድርጅቶች ሊሳተፉ ይችላሉ ወይ? የሚለው ጥያቄ አጠራጣሪ የሚሆነው፡፡ ራሱም የብሄር ድርጅቶች ግንባር ስለሆነ በ1983ቱ ሽግግር መንግስት ምስረታ ጉባዔ እንዳደረገው ሁሉ ዛሬም ህብረ-ብሄራዊ ድርጅቶችን ከድርድር ማዕቀፍ ለማግለል አያመነታም፡፡ ለነገሩ በሀገር ውስጥ ከመኢአድ፣ አንድነት እና ሰማያዊ ፓርቲ በስተቀር እዚህ ግባ የሚባል ህብረ ብሄረዊ ተቃዋሚ ድርጅት የለም፡፡

ODF logo
ODF logo

ከሃያ አምስት ዓመታት በፊት እንደነበረው ሁሉ ዛሬም ህብረ ብሄራዊ ፖለቲካ ድርጅቶችን ለማስተናገድ የሚችል ህገ መንግስታዊም ሆነ ፖለቲካዊ ማዕቀፍ የለም፡፡ በዚህ ሁኔታ ድርድር ቢካሄድ ራሱን በአንድ ወይም በሌላ መልኩ በብሄር ማዕቀፍ መመደብ የማይፈልገው ወይም የማይችለው በርካታ ህዝብ በድጋሚ የሀገሪቱን መፃዒ ዕጣ ፋንታ ሳይወከል የመቅረት ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ የሽግግር ቻርተሩን ለማፅደቅ በተጠራው ጉባዔ የተሰራውን ስህተት ግን በርካታ ምዕራባዊያን ምሁራን ሲተቹት ስለኖሩ አሁን ለማደራደር የሚፈልጉ ምዕራባዊያን ዲፕሎማቶች ድጋሚ ስህተት ላለመስራት መጠንቀቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡

እዚህ ላይ ግን ብሄር-ተኮር ከሆነው ህገ መንግስታዊ ፌደራላዊ ማዕቀፍ ውጭ ድርድር ለማድረግ ኢህአዴግ ፍቃደኛ ይሆናል ወይ? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ በርግጥ ፍቃደኛ ቢሆንም ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ዕምብዛም ተጎጂ ላይሆን ይችላል፡፡ የሆነው ሆኖ ኢህአዴግ ህብረ ብሄራዊ ድርጅቶችን ማግለሉ “ብሄር ተኮሩ ፌደራላዊ ስርዓት እንደገና ይከለስ ወይም ከመሰረቱ ይቀየር” የሚሉ ጥያቄዎችን ከሩቅ ለማስቀረት ይጠቅመዋል፡፡ ብሄር-ተኮር ተቃዋሚ ቡድኖች እንደሆኑ ከኢህአዴግ ጋር የስልጣን እና ሌሎች ጥቃቅን ጥያቄዎች ካልሆነ በስተቀር መሰረታዊ የአይዶሎጂ ቅራኔ እንደሌላቸው በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡

ሌላው ነጥብ ኢህአዴግ መንግስታዊ ስልጣን ይዞ መደራደሩ የተደራዳሪነት ጡንጫውን የሚያፈረጥምለት መሆኑ ነው፡፡ በዚህ ነባራዊ ፖለቲካዊ ሁኔታ ኢህአዴግ የራሱን ቅድመ ሁኔታዎች ማስቀመጥ ብቻ ሳይሆን የራሱን አጀንዳዎችም በተደራዳሪ ወገኖች ላይ ለመጫን ከፍተኛ ዕድል አለው፡፡ እንደሚታወቀው በሽግግር መንግስቱ ምስረታ ጉባዔ ኢህአዴግ የተወከለው በህወሃት እና ኢህዴን ብቻ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ኦህዴድን እና ደኢህዴንን ጨምሮ የአራት ብሄር-ተኮር ድርጅች ግንባር ሆኗል፡፡ ቅቡልነት ኖረውም አልኖረውም የብሄር ውክልናውን አስፍቷል፡፡ በመጠባበቂያነትም አናሳ ክልሎችን ከሚመሩ ፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ከአጋርነት የዘለለ ጥብቅ ትስስር አለው፡፡ ድርጅታዊ መዋቅሩን ከላይ እስከ ታች ዘርግቷል፡፡ ኢንዶውመንት በተሰኘ ስያሜ የንግድ ድርጅቶች ባለቤት ስለሆነ ሃብት አካብቷል፣ ኢኮኖሚያዊ ጡንጫውም ዳብሯል፡፡
በ1983 ዓ.ም የሀገሪቱን መፃዒ ዕጣ ፋንታ የተለመው ሽግግር ቻርተር ሲፀድቅ አብዛኛዎቹ ፖለቲካ ድርጅቶች የግለሰቦች ስብስብ እንጂ ከዚያ በፊት ህዝባዊ ውክልናም ሆነ ዕውቅና ያልነበራቸው ነበሩ፡፡ ያ ሁኔታ ግን ዛሬም ቢሆን እምብዛም የተቀየረ አይመስልም፡፡ ተቃዋሚ ድርጅቶች ጠረጴዛ ላይ የሚያቀርቡት የጋራ አጀንዳ የሌላቸው፣ የተበታተኑ እና ደካሞች መሆናቸው ለኢህአዴግ ሌላ ወርቃማ ዕድል ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት በኦሮሚያ ያለው የኦህዴድ መዋቅር እና ቅቡልነት ከጊዜ ወደጊዜ መሸርሸሩን የተረዳ ይመስላል፡፡ ካድሬዎቹም ላይ አመኔታ እንደሌለው በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ስለዚህ ክልሉ ከቁጥጥር ውጭ ከመሆኑ በፊት አንዱ መውጪያ መንገድ በአቶ ሌንጮ ከሚመራው ኦዴግ ጋር ተደራድሮ ኦህዴድን ከኦዴግ ጋር ማዳቀል ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ስልት በአዲስ ድርጅታዊ መዋቅር ግዙፉን ክልል በቁጥጥሩ ስር ለማቆየት ዕድል ይሰጠዋል፡፡ ኦዴግ ከኢህአዴግ ጋር ለመደራደር ፍቃደኝነት ማሳየቱ ደሞ ዕድሉን አስፍቶለታል ማለት ይቻላል፡፡ ድርድሩ ግን ኦዴግ ይዞት በሚመጣው ቅድመ ሀኔታ ላይ ይመሰረታል፡፡ ምናልባት ሀገር ዓቀፍ ድርድር ካልታሰበ ወይም ካልተቻለ አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ኢህአዴግ ቢያንስ ከኦዴግ ጋር መደራደሩ የሚቀር አይመስልም፡፡

የኢህአዴግ አጋር የሆኑ ምዕራባዊያን መንግስታት ፖለቲካ ኃይሎችን ለማደራደር ደፋ ቀና እያሉ ከሆነ ሁለት ኣላማ ሊኖራቸው እንደሚችል ታሳቢ ማድረግ ይችላል፡፡ ባንድ በኩል በተለይ የአሜሪካ መንግስት ህዝባዊ ተቃውሞውን በማረጋጋት የኢህአዴግ-መራሹን መንግስት ስልጣን ዕድሜ ለማራዘም አስቦ ሊሆን ይችላል፡፡ ኢትዮጵያ አሁንም በሱማሊያ (በዓለም ኣቀፉ ፀረ ሽብር ትግል) እና ደቡብ ሱዳን ባለው ቀውስ ሳቢያ የአሜሪካ ቁልፍ አጋር ተደርጋ መታየቷ እንደቀጠለ ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን የአሜሪካ መንግስት የሀገሪቱን ውስብስብ ችግሮች ገንፍለው ከወጡ የክፍለ አህጉሩን መረጋጋት ጭምር የሚያናጉ መሆናቸውን ተረድቶ ሁሉን አካታች እና ዘላቂ የሆነ መፍትሄ ለማስገኘት አስቦ ሊሆንም ይችላል፡፡ መንግስት እየወሰደ ባለው የኃይል ዕርምጃ ላይ የአሜሪካ መንግስት ለስላሳ አቋም ቢወስድም ውስጥ ለውስጥ ግን ምን እየሰራ እንደሆነ ለማወቅ በጥንቃቄ መከታተልን ይጠይቃል፡፡

Merera Gudina, OFCO Chair
Merera Gudina, OFCO Chair

በተለዋዋጩ የኢትዮዽያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተክለ ቁመና አመኔታ የሌላቸው ምዕራባውያን ዲፕሎማቶች በኢትዮዽያ ፖለቲካ ቁልፍ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉ ፓርቲዎችን ውስጥ ውስጡን እየገመገሙ መሆኑን የዋዜማ ምንጮች ይገልፃሉ። “የይስሙላ ድርድር የኢትዮዽያን ችግር አይፈታም፣ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የድርድር ሀሳብ ሲነሳለት በቅድመ ሁኔታ የድርድር ሀሳቦችን የሚያደናቅፈው ኢህአዴግ ዘንድሮ የተለየ አቋም ይኖረዋል ብዬ አልገምትም” ይላሉ በቅርቡ አዲስ አበባን ጎብኝተው የተመለሱ አንድ የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት አማካሪ።
በዚህም አለ በዚያ ኢህአዴግ ለፖለቲካዊ ድርድር ከተቀመጠ እየመጣበት ያለውን ፖለቲካዊ ቀውስ በማስታገስ ከድርድሩ በአሸናፊነት ለመውጣት አስልቷል መሆን አለበት፡፡ በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አማካኝነት ህልውና ይኑራቸው አይኑራቸውር የማይታወቁ ከስልሳ በላይ ተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶችን ህጋዊ ሰውነት ጠብቆ ማቆየቱ የሚጠቅመው ለዚህ ዓይነቱ ወሳኝ ጊዜ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የሚካሄድ ጠባብ ፖለቲካዊ ድርድር ዞሮ ዞሮ ስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ዕድሜ ከማራዘም ያለፈ ፋይዳ ላይኖረው ይችላል፡፡

በፖለቲካ ልሂቃን ድርድር ከማድረግ በፊት ግን ሁሉን ዓቀፍ የሆነ በተለይም ሲቪል ማህበረሰብ እና ኃይማኖት ተቋማት ጭምር የሚሳተፉበት ሀገር ዓቀፍ ውይይት አሁንም የሚዘነጋ ይመስላል፡፡ ላለፉት ሃያ ዓመታት በሀገሪቱ የብሄር ፖለቲካ ከታሰበው በላይ ስለጦዘ ህዝብ ለህዝብ ነፃ ውይይቶች አስፈላጊ መሆናቸውን ምሁራን አበክረው ይመክራሉ፡፡ ሆኖም ግን ከምሁራን በስተቀር አጀንዳውን የሚስተጋቡ ፖለቲካ ቡድኖች እምብዛም አይታዩም፡፡

አሁን ተቃውሞ አደባባይ እየወጣ ያለው ህዝብ በየትኛውም ፖለቲካ ድርጅት የሚወከል አይመስልም፡፡ ህዝቡ ኢህአዴግ የቆመበትን ብሄር-ተኮር ፌደራላዊ ስርዓት ቅቡልነት እና በፖለቲካ የበላይነት ላይ በተመሰረተው ሃብት ክፍልል ላይ መሰረታዊ ጥያቄዎች እያነሳ ነው፡፡ ለዚህም ነው ብዙ ታዛቢዎች ህገ መንግስቱን ጨምሮ ስርዓቱ የቆመባቸውን መርሆዎች በጠቅላላው ለነፃ ህዝባዊ ውይይት እና ውሳኔ ክፍት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን የሚመክሩት፡፡ ሁሉን ዓቀፍ ውይይትን ወደ ጎን መግፋት ካሁን በፊት ሀገሪቱን ቅርቃር ውስጥ ያስገባትን ከባድ ስህተት መድገም እና የሀገሪቱ መፃዒ ዕጣ ፋንታ የማይተነበይ እንዲሆን ማድረግ የሚሆነውም ለዚህ ነው፡፡