Chief Justice Meaza Ashenafi – PHOTO CREDIT PM Office

ዋዜማ ራዲዮ- በፌደራል ፍርድ ቤቶች ለሚደረግ የዳኝነት አገልግሎት ከፍ ያለ የዳኝነት ክፍያ ለማስከፈል ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔን እየጠበቀ መሆኑን ዋዜማ ለመረዳት ችላለች። 

አዲሱ ረቂቅ ደንብ ከ60 አመታት በላይ ሲያገለግል የነበረውን የክፍያ ተመን የሚቀይረው ሲሆን ተገልጋዮችንም ከፍ ያለ ገንዘብ ለፍርድ አገልግሎት የሚያስከፍል ይሆናል። 

ከፌደራል ፍርድ ቤቶች በተውጣጡ ባለሙያዎች እና በጠቅላይ ፍርድ ቤት አማካኝነት የተዘጋጀው ይህ አዲስ ደንብ ፍርድ ቤቶች ተወካዮች ምክር ቤት የሚያጸድቅላቸውን በጀት ብቻ ሳይጠብቁ በገንዘብ ራሳቸውን እንዲደግፉ የሚያግዛቸው ይሆናል። 

በ1945 ዓ.ም ወጥቶ የነበረውን እና ተገልጋዮችን ከ 50 ሳንቲም ጀምሮ እስከ 12,850 ብር ያስከፍል የነበረውን ተመን ደንብ አሁን በአዲስ የስሌት ቀመር ተግባራዊ የሚያደርግ ይሆናል። 

ይህ ረቂቅ መመርያ እስኪጸድቅ ድረስ ተገልጋዮች አሁን የሚከፍሉት ትንሹ የክፍያ መጠን የክስ መጠኑ እስከ 10 ብር ድረስ ለሆነ ክስ 50 ሳንቲም ሲሆን ሲሆን ይህም እንደየ ክሱ ገንዘብ መጠን ክፍያው በትንሹ እያደገ ይሄድና የመጨረሻው የክፍያ መጠን የክስ መጠኑ ከዘጠኝ መቶ ሺህ እስከ አንድ ሚልየን ብር ለደረስ ክስ 12,850  ይሆናል። 

ከአንድ ሚልየን ብር በላይ ላለ የክስ መጠን ፍርድ ቤት የሚያስከፍልበት ደንብ ባለመኖሩ የተለያየ አሰራር ነበረው። 

በአሁን ጊዜ ፍርድ ቤቶች እጅግ ከፍተኛ የገንዘብ መጠን ያላቸው እና በቢልየን ብር የሚተመኑ የፍርድ ጉዳዮችን የሚያይ ሲሆን ከነዚህም የሚፈለገውን ያህል የዳኝነት ክፍያ ሳያስከፍል ቆይቷል። 

አዲሱ የፌደራል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ክፍያ ደንብ” ክፍያዎችን በመቶኛ የአከፋፈል መጠን አርቆ ያዘጋጀ ሲሆን የመጀመያ ክፍያውም እስከ 20,000 ብር ድረስ የገንዘብ መጠን ላላቸው ፍርድ ጉዳዮች 8 በመቶ ያስከፍላል። 

ይህ ረቂቅ ደንብ ከፍተኛ የገንዘብ መጠን ላላቸውን የክስ ሂደቶች የገንዘብ አከፋፈል ስርዓት ያለው ሲሆን የክስ ገንዘቡ እያደገ በመጣ ቁጥር የመቶኛ መጠኑም ከ8 በመቶ እያነሰ የሚመጣ ይሆናል። 

የመጨረሻ ትንሹ የመቶኛም አከፋፈልም አንድ በመቶ ሲሆን ይህም የገንዘብ መጠናቸው ከ 200 ሚልዮን በላይ ላሉ ክሶች ይሆናል። 

በገንዘብ ሊተመኑ ለማይችሉ አቤቱታዎችም ፍርድ ቤቱ የክፍያ ገንዘብ ያወጣ ስሆን በዚህም መሰረት በፌደራል አንደኛ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ለሚቀርቡ አቤቱታዎች ተገልጋዮች አንድ ሺህ ብር መክፈል ይኖርባቸዋል። በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ለሚቀርቡ አቤቱታዎች ደግሞ ተገልጋዮች አንድ ሺህ አምስት መቶ ብር መክፈል ይኖርባቸዋል። 

ደንቡ ለዳኝነት አገልግሎት የማይከፈልባቸው የችሎት ጉዳዮችን ያስቀመጠ ሲሆን እነዚህም በህግ በደሃ ደንብ እንዲከራከር ለተፈረደለት ሰው እና የሰብዓዊ መብት ይከበርልኝ ለሚሉ አቤቱታዎች ነው። ሆኖም ግን የሰብዓዊ መብት ይከበርልኝ አቤቱታዎች ከንብረት ክርክር ጋር የተያያዘ ከሆነ ያለክፍያ አገልግሎቱ ተፈጻሚነት አይሆንም። 

የፈደራል ፍርድ ቤቶች ለዚህኛው በጀት አመት ወደ 300 ሚልየን ብር በተወካዮች ምክር ቤት የተመደበለት ሲሆን ይህም እንደሚያንሰውና ዘመኑን ባማከለ ክፍያ በዳኝነት አገልግሎት ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኝ እንዲያስችለው ይህን ደንብ እንዳዘጋጀ ዋዜማ ያናገረቻቸው የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሃላፊዎች ገልጸዋል። [ዋዜማ ራዲዮ]