ዋዜማ ራዲዮ- የደህንነት ሰራተኝነቱን እንደ ሽፋን በመጠቀም የሙስና ወንጀል ፈጽሟል በሚል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ውሎ የነበረው የቀድሞ የብሄራዊ የመረጃና የደህንነት አገልግሎት ባልደረባ ጌታቸው ዋለልኝ የዋስትና መብት ተፈቀደለት።
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 18ኛ የወንጀል ችሎት ነው በዛሬው ውሎው ለጌታቸው ዋስትናውን የፈቀደለት።
በደህንነት መስሪያ ቤት ውስጥ ለ10 አመት ያህል በኢኮኖሚ ደህንነት ባለሙያነት የሰራው ጌታቸው ዋለልኝ ፤ ከደህንነት መስሪያ ቤት የበላይ አመራሮች ጋር የነበረው አለመግባባት ለእስር እንደዳረገው ዋዜማ ራዲዮ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሰራችው ዘገባ ጠቁማ ነበር።በተለይ በደህንነት መስሪያ ቤቱ ውስጥ በህወሀት የመጨረሻ ጊዜያት የነበሩ መከፋፈሎችና የመስሪያ ቤቱ የበላይ አመራሮች ለግል ጥቅማቸው በደህንነት ሽፋን የሚያስገቡትን እቃ ጌታቸው መያዙ ለእስር እንዳበቃው ባልደረቦቹ ይመሰክሩለታል።
የዛሬ አመት አካባቢ የተያዘው ጌታቸው ዋለልኝ ከበርካታ መጉላላት በሁዋላ ክስ ቢመሰረትበትም አቃቤ ህግ ያቀረባቸው ምስክሮች እንደማያውቁት ገልጸዋል።ስለዚህም ፍርድ ቤቱ ጌታቸው ከቀረቡበት የሙስና ክሶች የተወሰኑትን ከማረሚያ ቤት ውጭ ሆኖ እንዲከላከል የዋስትና መብት ፈቅዶለታል።አብሮት ለእስር የተዳረገው ፍሰሀ ጸጋዬ ግን በማረሚያ ሆኖ እንዲከላከል ነው ፍርድ ቤቱ የበየነው። ስለ ጌታቸው ዋለልኝ በቅርብ ሳምንታት አቅርበነው የነበረውን የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ

https://youtu.be/9ZGoqYoKjmc