Jano singers Hailu and Hewan
Jano singers Hailu and Hewan

በጥቅምት አጋማሽ በኢትዮጵያ ከነበራቸው  ዝግጅት ለጥቆ ጃኖዎች አውሮፓ ነበሩ። ጣሊያን—  ሚላኖ እና ሮም፣
ስዊዘርላንድ—  ጄኔቭ እነ  ባዜል፣ ኖርዌይ— ኦስሎን አካልለዋል። “ላልተወሰነ ጊዜ አስተላልፈነዋል” ብለው
ባይሰርዙት ኖሮ ስዊድንም ከሳምንት በፊት ቀጠሮ ይዘው ነበር። ከአውሮፓ መልስ በቅጡ ትንፋሻቸውን እንኳ
ሳይሰበስቡ ነው በሸገር ሁነኛ የምሽት ክለብ በሆነው ክለብ ኤች ቱ ኦ (H2O) ዝግጅታቸውን እንደሚያቀርቡ የተሰማው።

ለሁለት አርቦች ብቻ ከተዘጋጀው የሙዚቃ ድግሳቸው የመጨረሻው ትናንት ለሊት(አርብ የካቲት ፪፭) ተካሂዷል። ከ15 ቀን በፊት የልጅ ሚካኤልን የሂፕ ሆፕ አልበም ምረቃ በተመሳሳይ ቦታ ያዘጋጀው ጆርካ ኤቬንትስ ከጃኖዎች ዝግጅት ጀርባ ነበር።

ሶስት ሰዓት ይጀምራል ተብሎ የታወጀለት ዝግጅት ሁለት ሰዓት ያህል ቢዘገይም ከጥቂት ደቂቃዎች ዕረፍት ውጭ
ለሶስት ሰዓት ያህል ላብ እየተንቆረቆረ፣ መድረኩ እያረገረገ እና የባንዱ አባላት ጨፍረው እያስጨፈሩ የተመልካችን
ቀልብ ገዝተው የቆዩበት ነበር።

የቴዲ አፍሮ ስራ አስኪያጅ የነበረው እና የባንዱን አባላት ከማሰባሰብ እስከ ዕውቅናው ከፍታ አብሯቸው ከተጓዘው አዲስ ገሰሰ ጋር ከተለያዩ በኋላ ስለ ጃኖዎች ገንኖ የሚወራው ሁለተኛ አልበማቸውን ሰርተው ማጠናቀቃቸው ነበር። ከዛሬ ነገ አልበማቸውን አድማጭ ጆሮ ያደርሳሉተብሎ ሲጠበቅ በአቋራጭ ሁለት ነጠላ ዜማዎችን ብቻ የያዘ ሲዲ ለአድናቂዎቻቸው በነፃ ማደል መረጡ።

“ዳሪኝ” እና “ይነጋል” የተሰኙት ነጠላ ዜማዎች በህዝብ ዘንድ ተወዳጅ ለመሆን እምብዛም ጊዜ አልወሰደባቸውም። በጃኖዋ እንስት ፈርጥ ድምፃዊት ሃሌ ሉያ  የተቀነቀነው “ዳሪኝ” በተለይ የሰርግ ማድመቂያ ዘፈኖችን ዝርዝር የተቀላቀለው በፍጥነት ነው። ኦፌሴሊያዊ የሙዚቃ ቪዲዬ ተሰርቶለት በቅርቡ ለዕይታ የበቃለት የኃይሉ አመርጋ “ይነጋልም” የጃኖ አድናቂዎችን ቀልብ እንደያዘ ምስክሩ የአርብ ምሽቱ ዝግጅት ነው። ኃይሉ ይህን ነጠላ ዜማ ሁለት ጊዜ በመድረክ ተጫውቶታል።

ከወራት በፊት በክለብ ኤች ቱ ኦ በነበራቸው ዝግጅት እነዚህ ሁለት ነጠላ ዜማዎች ለማስተዋወቅ በመድረክ በቀጥታ መጫወታቸውን የተመለከተ እንዳስለመዱት ከመጪው አልበማቸው የሚጨልፉት አይጠፋም የሚል ተስፋ ቢያሳድር አይገርምም። ሆኖም ጃኖዎች እንደተጠበቁት አዲስ ነገር ይዘው ከመምጣት ይልቅ የሀገራችን ተወዳጅ ድምጻውያን የተጫወቷቸውን ዜማዎች የሮክ ቀለም በማስያዝ ማቅረቡን ይሁነኝ ብለው ተያይዘውታል። ወደ 25 ከሚጠጉት እና በመድረክ ከቀረቡት ስራዎች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የሌሎች ድምጻውያን ዘፈኖች ነበሩ።

ከጥላሁን ገሰሰ እስከ ጌታቸው ካሳ፣ ከአስቴር አወቀ እስከ እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ)፣ ከተክሌ ተስፋእዝጊ እስከ
ሙሉቀን መለሰ ቀደምት ተወዳጅ ዘፈኖቻቸው በጃኖዎች ዘይቤ ለተመልካች ቀርበዋል። ከአፍ እስከ ገደፉ ጢም ባለው ኤች ቱ ኦ የነበረው ተመልካች የአንዳንዶቹን ዘፈኖች የመወደድ ልክ እንደ ብሔራዊ መዝሙር አብሮ በመዝፈን አሳይቷል። ኃይሉ እና ዲበኩሉ እየተቀባበሉ ያዜሙት የኢዮብ “ትወደኛለች”ም በብዙዎች የተጨበጨበለት ነበር። ጃኖዎች ከሀገራችንም ተሻግረው የቦብ ማርሌይን፣ ስቲቪ ወንደርን እንደዚሁም የሬጌ ባንድ የሆነውን ማጂክ ዘፈኖች ተጫውተዋል።

የትናንት ምሽት አያያዛቸውን አይቶ “አዲስ ነገር አጥተዋል” ለሚላቸው ተቺ ለበዓለ ፋሲካ ለመለቀቅ ቀነ ቀጠሮ
የተያዘለትን ሁለተኛ አልበም እንዲያደምጥ የባንዱ አባላት ያሳስባሉ። አስራ ስድስት ዘፈኖች የሚይዘው አልበም
በሙሉ በኦሪጅናሌ ስራ የተሞላ እንደሆነ አንዱ የባንዱ የሙዚቃ ተጨዋቾች ይናገራል። በእርግጥ አስቀድመው ሙዚቃ አፍቃሪዎች ጋር የደረሱት ሁለቱ ነጠላ ዜማዎች ይካተቱበታል።

ከአራት አመት በፊት የተለቀቀው የጃኖዎች የመጀመሪያ አልበም “ኤርታሌ” የሚሰኝ ሲሆን አርብ ምሽት ያቀረቡት
የሙዚቃ ድግስ የዚህ አልበም የመጨረሻ ዝግጅት እንደሆነ ከባንዱ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።  እነሆ የሀሌሉያን ዳሪኝ ተጋበዙልን