ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከአመታት ወዲህ በገባበት ያልተመለሰ ብድር ቀውስ ሳቢያ ከፍተኛ የካፒታል ማሽቆልቆል ውስጥ በመግባቱ እንደከዚህ ቀደሙ ብድር እያቀረበ መቀጠል እየተቸገረ እንደሆነ ምንጮቻችን ነግረውናል።

የባንኩ ያልተመለሰ ብድር ራሱ ባመነው ደረጃ እንኳ ከአጠቃይ ከሰጠው ብድር 40 በመቶ ደርሷል።በቅርቡ ባንኩ ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው በጥቅሉ የሰጠው ብድር 46.17 ቢሊየን ብር ነው።ይህ ማለት ባንኩ ባመነው ደረጃ እንኳ 18 ቢሊየን ብር ገደማ የሚሆነው ብድሩ የተበላሸ ሆኗል ማለት ነው።

     የልማት ባንኩ የተበላሸ ብድር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣትም ያሳሰበው መንግስት በባንኩ ላይ ጠንካራ አቋም ይዞበታል።ልማት ባንኩ መሰረታዊ ማሻሻያዎችን ካልወሰደ ከመንግስት የሚደረግለት ድጋፍ እንደማይኖርም ከብሄራዊ ባንክ በኩልም በተደጋጋሚም ሲሰማም ነበር።

 ዋዜማ ራዲዮ ከባንኩ ምንጮቿ እንደሰማችው ከሆነ ግን ልማት ባንኩ አሁን ላይ መንግስት የካፒታል ድጋፍ እንዲያደርግለት ጥያቄውን ለማቅረብ እየተሰናዳ ነው። የካፒታል ጥያቄውን ሊያቀርብ የፈለገውም ባልተመለሰ ብድር ምክንያት ያጋጠመውን የካፒታል መመናመን ለማካካስ መሆኑን ነው የሰማነው። አሁን ባለበት ሁኔታ ከቀጠለም ባንኩ አይደለም እንደስሙ ልማት እየደገፈ መቀጠል እንደባንክ መቀጠልም ሊቸገር ይችላል።

ሆኖም ባንኩ ከመንግስት የሚፈለግበትን ማሻሻያዎች በሚታይ መልኩ መተግበሩን ካላሳየ የገንዘብ ድጋፉን እንዴት ሊያገኝ ይችላል የሚለው ነገር አጠያያቂ ሆኗል።
     

ልማት ባንክ ብድሩን ያልመለሱለትን በቢሊየን የሚቆጠር ብር የተበደሩትን ጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎችን እየወረሰ መሆኑ ይታወቃል። ሆኖም ሊሸጣቸው ለጨረታ ያቀረባቸው ግን ገዥ እንዳጡም በተደጋጋሚ ሲነገር የቆየ ነው።

በሌላ በኩል በጋምቤላ ክልል ለሰፋፊ እርሻ ተበድረው ብድር ያልመለሱ እና የጠፉ ባለሀብቶችም አሉ።አሁን ላይም በክልሉ እርሻ ለማልማት ብድር ወስደው የብድር ማስያዣ ንብረቶችን የሚያሸሹ ተበዳሪዎች በስፋት በመኖራቸው ባንኩ ከጋምቤላ ክልል መንግስት ጋር በመነጋገር ያለ ልማት ባንኩ እውቅናና ፍቃድ ከክልሉ በተለይ የእርሻ ማሽኖች እንዳይወጡ የማሳገድ ስራን እየሰራ እንደሆነም ይገልጻል።

እነዚህ ሁሉ ጥረቶቹ ግን ለባንኩ የተወሰነ መጠን ያለው ገንዘብ ያስመልስለት ይሆናል እንጂ ከደረሰበት ኪሳራ አያድነውም።ከዚህ ማጥ ውስጥ ለመውጣትም ባንኩ አሁን የመንግስት እርዳታ ያስፈልገኛል ብሏል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከሶስት አመት በፊት አስራሩን እንዲያሻሽል ተነግሮች 2.5 ቢሊየን ብር ድጋፍ ከመንግስት ተደርጎለት የነበረ ቢሆንም ብልሹ አሰራሩን እስካሁን መቀየር ሳይችል ቀርቷል። ዝርዝር የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ

https://youtu.be/U3_yRuhNAwc