ዋዜማ ራዲዮ- በተያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ዉጥረት ነግሷል። በተለያዩ ከተሞች ተቃውሞና ግጭት እየተሰማ ነው። መንግስት በሰውና በንብረት ላይ ጉዳይ ለማድረስ ተንቀሳቅሰዋል ባላቸው ላይ የሀይል እርምጃ ወስዷል። የሰው ሕይወትም ጠፍቷል። በተወዳጁ ድምፃዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ሞት የተቀሰቀሰው ቁጣ ሀገሪቱን ለከፋ የፀጥታና መረጋጋት ፈተና ዳርጓታል።

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል የድምፃዊ ሐጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በተመለከተ የኢትዮጲያ መንግስት ነፃ ገለልተኛ እና ውጤታማ የሆነ ምርመራ በማከናወን አጥፊዎችን ህግ ፊት እንዲያቀርብ ጠይቋል ።

ማክሰኞ ምሽት ባወጣው መግጫ የድርጅቱ የምስራቅ አፍሪካ ክልል ምክትል ዳይሬክተር ሳራ ጃክሰን ለሐጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ፍትህ ግዴታ ነው ብለዋል። የኢትዮጲያ መንግስት የጀመረውን ምርመራ አፍጥኖ ነፃ ገለልተኛ እና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ጥፋተኞችን ለፍትህ እንዲያቀርብ የጠየቁት ዳይሬክተሯ በአገርቷ በጠቅላላ የኢንተርኔት አገልግሎት ላይ የተጣለው እገዳም ይነሳ ብለዋል። የፀጥታ ሃሎችን በተመለከተም አምነስቲ ጉዳት ከማድረስ እንዲቆጠቡ እና አላስፈላጊ የሆነ ሃይል ተቃዋሚዎች ላይ እንዳይጠቀሙ ጠይቋል።

በተያያዘ ዜና የአርቲስት ሐጫሉ ግድያ የእርስ በእርስ ግጭት ለመፍጠር ሆን ተብሎ የተፈፀመ ግድያ ስለመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ ለኢቢሲ ማክስኞ ምሽት በአማርኛ እና በኦሮምኛ ቋንቋ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

የውጪ እና የውስጥ ጠላት በመቀናጀት ታዋቂ የኦሮሞ ሰዎችን ለመግደል የታለመ ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ማን ይህንን ግድያ እንዳቀነባበረ ግን አልተናገሩም። አብይ ግድያው የጀመርነውን ጉዞ እንዲደናቀፍ ገዳይ ቡድኖች በማሰማራት የተስራ ሴራ ነው ሲሉ የተናገሩ ሲሆን የሃጫሉንም ግድያ ተከትሎ በተነሳው ረብሻ ንፁሃን ህይወታቸውን ሰለማጣታቸው ተናግረዋል። ሐጫሉ በቅርበት የማውቀው የቅርብ ወዳጄ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስተሩ የጠላት አላማ እንዳይሳካ ጉዳዩተጣርቶ ለፍትህ እንዲቀርብ መላው የኢትዮጲያ ህዝብን ትብብር ጠይቀዋል።


በሌላ ዜና የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሣህለውርቅ ዘውዴ በአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳ ግድያ የተሰማቸውን ከፍተኛ ሃዘን ገልፀዋል። ማክስኞ ምሽት ሶስት ሰዓት ላይ ፕሬዝዳንቷ በቲውተር ገፃቸው ባሰተላለፉት መልዕክት ግድያው በማንኛውም መስፈርት በሁላችንም ሊወገዝ የሚገባው ኢሰብዓዊ ድርጊት ነው ብለዋል። ለአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳ ቤተሰቦች እና አድናቂዎች እንዲሁም ለመላው የኢትዮጲያ ህዝብ መፅናናትን የተመኙት ፕሬዝዳንቷ ህዝቡ የራሱን እና የአካባቢውን ሠላም በመጠበቅ አንድነቱን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግሬስ (ኦፌኮ) አባል እና የኦሮሞ ብሄር መብት ተሟጋቹ ጃዋር ሞሐመድ እና የኦፌኮ ም/ሊቀመንበር በቀለ ገርባ መታሰራቸውን በመቃወም በሜኒሶታ የሚኖሩ ኢትዮጲያውያን እና ትወልደ ኢትጲያውያን ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተው ተቃውሞ አሰምተዋል። ሰልፈኞቹ ፍትህ ይሰጠን ግድያ ይቁም ሲሉ ጠይቀዋል።

ከድምፃዊ ሀጫሉ ግድያ ጋር የተያያዙ ሌሎች መረጃዎች ከታች በተያያዘው የድምፅ ዘገባ ያገኛሉ