Biruk 2ዋዜማ ራዲዮ -አወዛጋቢውን የድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን ቴዲ አፍሮ ቃለ መጠይቅ ያደረገው የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ጋዜጠኛ ስራውን ለቀቀ።
የመዝናኛ ክፍል ባልደረባና ያለፉትን አራት አመታት በድርጅቱ ያገለገለው ጋዜጠኛ ብሩክ እንዳለ ከቴዲ አፍሮ ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ እንደይተላለፍ መከልከሉን ተከትሎ ስራ መልቀቂያ ማቅረቡን ተናግሯል።
” ከኢቢሲ ጋር ደጉንም መልካሙን ግዜ ተካፍያለሁ ከሰሞኑ ከተከሰተው(የቴዲ አፍሮ) ጉዳይ ጋር ተያይዞ ግን ከህሊናዬ ጋር እየታገልኩ ልቀጥል አልችልም” ብሏል በፌስ ቡክ ገፁ ባሰፈረው አስተያየቱ።

“ጉዳዩ እንድን የኪነጥበብ ሰው ማቅረብና ያለመቅረብ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ጉዳዩ የጋዜጠኝነት ልዕልናንም የሚጋፋ ሆኖ ስላገኘሁትና ብዙዎች መሰዋት የከፈሉለትን ሙያ ክብር ለመስጠትም ጭምር ነው እዚህ ውሳኔ ለይ የደርስኩት” ይላል ብሩክ

የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ከቴዲ አፍሮ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ እንደሚያቀርብ ካስተዋወቀ በኋላ በድንገት ሀሳቡን ቀይሮ ቃለምልልሱን አግዶታል።
በጉዳዩ ላይ የተጋጋለ ክርክር ሲካሄድ ቢቆይም የድርጅቱ የበላይ ሀላፊዎች በሶስተኛ ወገን ጫና ፕሮግራሙን እስከወዲያኛው አግደውታል።